የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ዳንኤል 10

10
1በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በሦስተኛው ዓመት ብልጣሶር ለተባለው ለዳንኤል ነገር ተገለጠለት፥ ነገሩም እውነት ነበረ፥ እርሱም ታላቅ ጦርነት ነው፥ ነገሩንም አስተዋለ፥ በራእዩም ውስጥ ማስተዋል ተሰጠው። 2በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ። 3ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፥ ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም፥ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም። 4ከመጀመሪያውም ወር በሀያ አራተኛው ቀን ጤግሮስ በተባለው በታላቁ ወንዝ አጠገብ ሳለሁ፥ ዓይኔን አነሣሁ፥ 5እነሆም፥ በፍታ የለበሰውን ጥሩም የአፌዝን ወርቅ በወገቡ ላይ የታጠቀውን ሰው አየሁ። 6አካሉም እንደ ቢረሌ ይመስል ነበር፥ ፊቱም እንደ መብረቅ ምስያ ነበረ፥ ዓይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና፥ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፥ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበረ። 7እኔም ዳንኤል ብቻዬን ራእዩን አየሁ፥ ከእኔ ጋር የነበሩ ሰዎች ግን ራእዩን አላዩም፥ ነገር ግን ጽኑ መንቀጥቀጥ ወደቀባቸው፥ ሊሸሸጉም ሸሹ። 8እኔም ብቻዬን ቀረሁ ይህንም ታላቅ ራእይ አየሁ፥ ኃይልም አልቀረልኝም፥ ደም ግባቴም ወደ ማሸብሸብ ተለወጠብኝ፥ ኃይልም አጣሁ። 9የቃሉንም ድምፅ ሰማሁ፥ የቃሉንም ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምድር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ።
10እነሆም፥ አንዲት እጅ ዳሰሰችኝ፥ በጕልበቴና በእጄም አቆመችኝ። 11እርሱም፦ እጅግ የተወደድህ ሰው ዳንኤል ሆይ፥ እኔ ዛሬ ወደ አንተ ተልኬአለሁና የምነግርህን ቃል አስተውል፥ ቀጥ ብለህም ቁም አለኝ። ይህንም ቃል ባለኝ ጊዜ እየተንቀጠቀጥሁ ቆምሁ። 12እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ዳንኤል ሆይ፥ አትፍራ፥ ልብህ ያስተውል ዘንድ፥ ሰውነትህም በአምላክህ ፊት ይዋረድ ዘንድ ካደረግህበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቶአል፥ እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ። 13የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሀያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፥ እነሆም፥ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፥ እኔም ከፋርስ ነገሥታት ጋር በዚያ ተውሁት። 14ራእዩም ገና ለብዙ ዘመን ነውና በኋለኛው ዘመን ለሕዝብህ የሚሆነውን አስታውቅህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ። 15ይህንም ቃል በተናገረኝ ጊዜ ፊቴን ወደ ምድር አቀረቀርሁ፥ ዲዳም ሆንሁ። 16እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከንፈሬን ዳሰሰኝ፥ የዚያን ጊዜም አፌን ከፍቼ ተናገርሁ በፊቴም ቆሞ የነበረውን፦ ጌታዬ ሆይ፥ ከራእዩ የተነሣ ሕመሜ መጣብኝ፥ ኃይልም አጣሁ። 17ይህ የጌታዬ ባሪያ ከዚህ ከጌታዬ ጋር ይናገር ዘንድ እንዴት ይችላል? አሁንም ኃይል አጣሁ፥ እስትንፋስም አልቀረልኝም አልሁት።
18ደግሞ ሰው የሚመስል ዳሰሰኝ፥ አበረታኝም። 19እርሱም፦ እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ፥ አትፍራ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን፥ በርታ፥ ጽና አለኝ። በተናገረኝም ጊዜ በረታሁና፦ አበርትተኸኛልና ጌታዬ ይናገር አልሁ። 20እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ወደ አንተ የመጣሁት ስለ ምን እንደ ሆነ፥ ታውቃለህን? አሁንም ከፋርስ አለቃ ጋር እዋጋ ዘንድ እመለሳለሁ፥ እኔም ስወጣ፥ እነሆ፥ የግሪክ አለቃ ይመጣል። 21ነገር ግን በእውነት ጽሑፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፥ በዚህም ነገር ከአለቃችሁ ከሚካኤል በቀር ማንም የሚያጸናኝ የለም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ