ትንቢተ ዳንኤል 12
12
1በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል፥ ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል፥ በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል። 2በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ፥ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና። 3ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ። 4ዳንኤል ሆይ፥ አንተ ግን እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ቃሉን ዝጋ፥ መጽሐፉንም አትም፥ ብዙ ሰዎች ይመረምራሉ፥ እውቀትም ይበዛል።
5እኔም ዳንኤል አየሁ፥ እነሆም፥ ሁለት ሌሎች ቆመው ነበር፥ አንዱ በዚህ በወንዙ ዳር፥ ሌላውም በዚያ በወንዙ ዳር። 6አንዱም ከወንዙ ውኃ በላይ የነበረውን በፍታም የለበሰውን፦ የዚህ ድንቅ ፍጻሜ እስከ መቼ ነው? አለው። 7ከወንዙም ውኃ በላይ የነበረው በፍታም የለበሰው ሰው ቀኝና ግራ እጁን ወደ ሰማይ አንሥቶ፦ ለዘመንና ለዘመናት ለዘመንም እኵሌታ ነው፥ የተቀደሰውም ሕዝብ ኃይል መበተን በተጨረሰ ጊዜ ይህ ሁሉ ይፈጸማል ብሎ ለዘላለም ሕያው ሆኖ በሚኖረው ሲምል ሰማሁ። 8ሰማሁም ነገር ግን አላስተዋልሁም፥ የዚያን ጊዜም፦ ጌታዬ ሆይ፥ የዚህ ሁሉ ፍጻሜ ምንድር ነው? አልሁ። 9እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ዳንኤል ሆይ፥ ቃሉ እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ የተዘጋና የታተመ ነውና ሂድ፥ 10ብዙ ሰዎች ሰውነታቸውን ያጠራሉ ያነጡማል ይነጥሩማል፥ ክፉዎች ግን ክፋትን ያደርጋሉ፥ ክፉዎችም ሁሉ አያስተውሉም፥ ጥበበኞች ግን ያስተውላሉ። 11የዘወትሩም መሥዋዕት ከቀረ ጀምሮ፥ የጥፋትም ርኵሰት ከቆመ ጀምሮ ሺህ ሁለት መቶ ዘጠና ቀን ይሆናል። 12የሚታገሥ፥ እስከ ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ አምስት ቀንም የሚደርስ ምስጉን ነው። 13አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ፥ አንተም ታርፋለህ፥ በቀኑም መጨረሻ በዕጣ ክፍልህ ትቆማለህ።
Currently Selected:
ትንቢተ ዳንኤል 12: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ