የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ዳንኤል 2

2
1ናቡከደነፆርም በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ናቡከደነፆር ሕልም አለመ፥ መንፈሱም ታወከ፥ እንቅልፉም ከእርሱ ራቀ። 2ለንጉሡም ሕልሙን እንዲነግሩት ንጉሡ የሕልም ተርጓሚዎቹንና አስማተኞቹን መተተኞቹንና ከለዳውያኑንም ይጠሩ ዘንድ አዘዘ፥ እነርሱም ገብተው በንጉሡ ፊት ቆሙ። 3ንጉሡም፦ ሕልም አልሜአለሁ፥ ሕልሙንም ለማወቅ መንፈሴ ታውኮአል አላቸው። 4ከለዳውያኑም ንጉሡን በሶርያ ቋንቋ፦ ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ፥ ለባሪያዎችህ ሕልምህን ንገር፥ እኛም ፍቺውን እናሳይሃለን ብለው ተናገሩት። 5ንጉሡም መለሰ ከለዳውያኑንም፦ ነገሩ ከእኔ ዘንድ ርቆአል፥ ሕልሙንና ፍቺውን ባታስታውቁኝ፥ ትቈረጣላችሁ ቤቶቻችሁም የጕድፍ መጣያ ይደረጋሉ። 6ሕልሙንና ፍቺውን ግን ብታሳዩ፥ ከእኔ ዘንድ ስጦታና ዋጋ ብዙ ክብርም ትቀበላላችሁ፥ ስለዚህም ሕልሙንና ፍቺውን አሳዩኝ አላቸው። 7ሁለተኛም ጊዜ መልሰው፦ ንጉሡ ለባሪያዎቹ ሕልሙን ይንገር፥ እኛም ፍቺውን እናሳያለን አሉት። 8ንጉሡ መልሶ፦ ነገሩ ከእኔ ዘንድ እንደ ራቀ ታውቃላችሁና ጊዜውን እንድታስረዝሙ እኔ አውቃለሁ። 9ሕልሙንም ባታስታውቁኝ አንድ ፍርድ አለባችሁ፥ ጊዜውን ለማሳለፍ የሐሰትንና የተንኰልን ቃል ልትነግሩኝ አዘጋጅታችኋል፥ ስለዚህ ሕልሙን ንገሩኝ፥ ፍቺውንም ማሳየት እንድትችሉ አውቃለሁ አለ። 10ከለዳውያኑም በንጉሡ ፊት መልሰው፦ የንጉሡን ነገር ያሳይ ዘንድ የሚችል ሰው በምድር ላይ የለም፥ ከነገሥታትም ታላቅና ኃይለኛ የሆነ እንደዚህ ያለ ነገር የሕልም ተርጓሚንና አስማተኛን ከለዳዊውንም አልጠየቀም። 11ንጉሡም የሚጠይቀው ነገር የቸገረ ነው፥ መኖሪያቸው ከሰው ጋር ካልሆነ ከአማልክት በቀር በንጉሡ ፊት የሚያሳየው ማንም የለም አሉ። 12ስለዚህም ንጉሡ ተበሳጨ እጅግም ተቈጣ፥ የባቢሎንንም ጠቢባን ሁሉ ያጠፉ ዘንድ አዘዘ። 13ትእዛዝም ወጣ፥ ጠቢባንንም ይገድሉ ዘንድ ጀመሩ፥ ዳንኤልንና ባልንጀሮቹንም ይገድሉ ዘንድ ፈለጉአቸው።
14የዚያን ጊዜም ዳንኤል የባቢሎንን ጠቢባን ይገድል ዘንድ የወጣውን የንጉሡን የዘበኞቹ አለቃ አርዮክን በፈሊጥና በማስተዋል ተናገረ፥ 15ለንጉሡም አለቃ ለአርዮክ መልሶ፦ የንጉሡ ትእዛዝ ስለ ምን ቸኰለ? አለው። አርዮክም ነገሩን ለዳንኤል አስታወቀው። 16ዳንኤልም ገብቶ ፍቺውን ለንጉሡ የሚያስታውቅበት ጊዜ ይሰጠው ዘንድ ንጉሡን ለመነ።
17-18የዚያን ጊዜም ዳንኤል ወደ ቤቱ ሄደ። ዳንኤልም ባልንጀሮቹም ከቀሩት ከባቢሎን ጠቢባን ጋር እንዳይሞቱ ስለዚህ ምሥጢር ምሕረትን ከሰማይ አምላክ ይለምኑ ዘንድ ነገሩን ለባልንጀሮቹ ለአናንያና ለሚሳኤል ለአዛርያ አስታወቃቸው።
19የዚያን ጊዜም ምሥጢሩ በሌሊት ራእይ ለዳንኤል ተገለጠለት፥ ዳንኤልም የሰማይን አምላክ አመሰገነ። 20ዳንኤልም ተናገረ እንዲህም አለ፦ ጥበብና ኃይል ለእርሱ ነውና የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ፥ 21ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል፥ ነገሥታትን ያፈልሳል፥ ነገሥታትንም ያስነሣል፥ ጥበብን ለጠቢባን እውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል። 22የጠለቀውንና የተሠወረውን ይገልጣል፥ በጨለማ ያለውን ያውቃል፥ ብርሃንም ከእርሱ ጋር ነው። 23ጥበብንና ኃይልን የሰጠኸኝ፥ እኛም የለመንንህን ነገር አሁን ያስታወቅኸኝ፥ አንተ የአባቶቼ አምላክ ሆይ፥ የንጉሡን ነገር አስታውቀኸኛልና እገዛልሃለሁ አመሰግንህማለሁ። 24ከዚህም በኋላ ዳንኤል ንጉሡ የባቢሎን ጠቢባን ያጠፋ ዘንድ ወዳዘዘው ወደ አርዮክ ገባ፥ በገባም ጊዜ፦ የባቢሎንን ጠቢባን አታጥፋ፥ ወደ ንጉሡ አስገባኝ፥ እኔም ፍቺውን ለንጉሡ አሳያለሁ አለው።
25የዚያን ጊዜም አርዮክ ዳንኤልን ፈጥኖ ወደ ንጉሡ አስገባውና፦ ከይሁዳ ምርኮኞች ያለውን ለንጉሡ ፍቺውን የሚያስታውቀውን ሰው አግኝቼአለሁ አለው። 26ንጉሡም መለሰ ብልጣሶርም የሚባለውን ዳንኤልን፦ ያየሁትን ሕልምና ፍቺውን ታስታውቀኝ ዘንድ ትችላለህን? አለው። 27ዳንኤልም በንጉሡ ፊት መልሶ እንዲህ አለ፦ ንጉሡ የጠየቀውን ምሥጢር ጠቢባንና አስማተኞች የሕልም ተርጓሚዎችና ቃላተኞች ለንጉሡ ያሳዩ ዘንድ አይችሉም፥ 28ነገር ግን ምሥጢር የሚገልጥ አምላክ በሰማይ ውስጥ አለ፥ እርሱም በኋለኛው ዘመን የሚሆነውን ለንጉሡ ለናብከደነፆር አስታውቆታል። በአልጋህ ላይ የሆነውን ሕልምና የራስህ ራእይ ይህ ነው። 29አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በኋላ የሚሆነው ምን እንደ ሆነ በአልጋህ ላይ ታስብ ነበር፥ ምሥጢርንም የሚገልጠው የሚሆነውን ነገር አስታውቆሃል። 30ነገር ግን ይህ ምሥጢር ለእኔ መገለጡ ፍቺው ለንጉሡ ይታወቅ ዘንድ፥ አንተም የልብህን አሳብ ታውቅ ዘንድ ነው እንጂ በዚህ ዓለም ካሉ ሰዎች ይልቅ በጥበብ ስለ በለጥሁ አይደለም።
31አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ ታላቅ ምስል አየህ፥ ይህም ምስል ታላቅና ብልጭልጭታው የበዛ ነበረ፥ በፊትህም ቆሞ ነበር፥ መልኩም ግሩም ነበረ። 32የዚህም ምስል ራስ ጥሩ ወርቅ፥ ደረቱና ክንዶቹም ብር፥ ሆዱና ወገቡም ናስ፥ 33ጭኖቹም ብረት፥ እግሮቹም እኩሉ ብረት እኩሉም ሸክላ ነበረ። 34እጅም ሳይነካው ድንጋይ ከተራራው ተፈንቅሎ ከብረትና ከሸክላ የሆነውን የምስሉን እግሮች ሲመታና ሲፈጭ አየህ። 35የዚያን ጊዜም ብረቱና ሸክላው፥ ናሱና ብሩ ወርቁም በአንድነት ተፈጨ፥ በመከርም ጊዜ በአውድማ ላይ እንዳለ እብቅ ሆነ፥ ነፋስም ወሰደው፥ ቦታውም አልታወቀም፥ ምስሉንም የመታ ድንጋይ ታላቅ ተራራ ሆነ ምድርንም ፈጽሞ ሞላ።
36ሕልሙ ይህ ነው፥ አሁንም ፍቺውን በንጉሡ ፊት እንናገራለን። 37አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ኃይልን፥ ብርታትንና ክብርን የሰጠህ የነገሥታት ንጉሥ አንተ ነህ። 38በሚቀመጡበትም ስፍራ ሁሉ የሰው ልጆችንና የምድር አራዊትን የሰማይ ወፎችንም በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል፥ ለሁሉም ገዥ አድርጎሃል አንተ የወርቁ ራስ ነህ። 39ከአንተም በኋላ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሣል፥ ከዚያም በኋላ በምድር ሁሉ ላይ የሚገዛ ሌላ ሦስተኛ የናስ መንግሥት ይነሣል። 40አራተኛውም መንግሥት ሁሉን እንደሚቀጠቅጥና እንደሚያደቅቅ ብረት ይበረታል፥ እነዚህንም ሁሉ እንደሚፈጭ ብረት ይቀጠቅጣል ይፈጭማል። 41እግሮቹና ጣቶቹም እኩሉ ሸክላ እኩሉም ብረት ሆኖ እንዳየህ፥ እንዲሁ የተከፋፈለ መንግሥት ይሆናል፥ ብረቱም ከሸክላው ጋር ተደባልቆ እንዳየሁ፥ የብረት ብርታት ለእርሱ ይሆናል። 42የእግሮቹም ጣቶች እኩሉ ብረት እኩሉም ሸክላ እንደ ነበሩ፥ እንዲሁም መንግሥቱ እኩሉ ብርቱ እኩሉ ደካማ ይሆናል። 43ብረቱም ከሸክላው ጋር ተደባልቆ እንዳየህ፥ እንዲሁ ከሰው ዘር ጋር ይደባለቃሉ፥ ነገር ግን ብረት ከሸክላ ጋር እንደማይጣበቅ፥ እንዲሁ እርስ በርሳቸው አይጣበቁም። 44በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፥ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፥ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፥ ለዘላለምም ትቆማለች። 45ድንጋዩም እጅ ሳይነካው ከተራራ ተፈንቅሎ ብረቱንና ናሱን ሸክላውንና ብሩን ወርቁንም ሲፈጨው እንዳየህ፥ እንዲሁ ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ታላቁ አምላክ ለንጉሡ አስታውቆታል፥ ሕልሙም እውነተኛ ፍቺውም የታመነ ነው።
46የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር በግምባሩ ተደፍቶ ለዳንኤል ሰገደለት፥ የእህሉንም ቁርባን ዕጣኑንም ያቀርቡለት ዘንድ አዘዘ። 47ንጉሡም ዳንኤልን፦ ይህን ምሥጢር ትገልጥ ዘንድ ተችሎሃልና በእውነት አምላካችሁ የአማልክት አምላክ፥ የነገሥታትም ጌታ፥ ምሥጢርም ገላጭ ነው ብሎ ተናገረው። 48ንጉሡም ዳንኤልን ከፍ ከፍ አደርገው፥ ብዙም ታላቅ ስጦታ ሰጠው፥ በባቢሎንም አውራጃ ሁሉ ላይ ሾመው፥ በባቢሎንም ጠቢባን ሁሉ ላይ ዋነኛ አለቃ አደረገው። 49ዳንኤልም ንጉሡን ለመነ፥ እርሱም ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎምን በባቢሎን አውራጃ ሥራ ላይ ሾማቸው፥ ዳንኤል ግን በንጉሡ በር ነበረ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ