የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘዳግም 6

6
1-2አንተ ልጅህም የልጅ ልጅህም በዕድሜአችሁ ሁሉ ልትወርሱአት በምትገቡባት ምድር ታደርጉአት ዘንድ፥ አምላክህን እግዚአብሔርን ፈርተህ እኔ ለአንተ ያዘዝሁትን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ ትጠብቅ ዘንድ፥ ዕድሜህም ይረዝም ዘንድ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንዳስተምራችሁ ያዘዛት ትእዛዝና ሥርዓት ፍርድም ይህች ናት። 3እንግዲህ፥ እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ መልካም እንዲሆንልህ፥ የአባቶችህም አምላክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ወተትና ማር በምታፈስሰው ምድር እጅግ እንድትበዛ፥ ታደርጋት ዘንድ ጠብቅ። 4እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ 5አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ። 6እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። 7ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው። 8በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው፤ በዓይኖችህም መካከል እንደክታብ ይሁንልህ። 9በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው። 10አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተ ሊሰጣት ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ባገባህ ጊዜ፤ ያልሠራሃቸውንም ታላቅና መልካም ከተሞች፥ 11ያልሞላሃቸውንም ሀብትን የሞሉ ቤቶች፥ ያልማስሃቸውንም የተማሱ ጉድጉዶች፥ ያልተከልሃቸውንም ወይንና ወይራ በሰጠህ ጊዜ፥ በበላህና በጠገብህም ጊዜ፤ 12በዚያን ጊዜ ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ። 13አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም አምልክ፤ በስሙም ማል። 14-15በመካከልህ ያለው አምላክህ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነውና የአምላክህ የእግዚአብሔር ቁጣ እንዳይነድድብህ ከምድርም ፊት እንዳያጠፋህ፥ በዙሪያችሁ ያሉት አሕዛብ የሚያመልኩአቸውን ሌሎችን አማልክት አትከተሉ። 16በማሳህ እንደ ፈተናችሁት አምላካችሁን እግዚአብሔርን አትፈታተኑት። 17ለእናንተ ያዘዘውን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ምስክሩንም ሥርዓቱንም አጥብቃችሁ ጠብቁ። 18-19መልካምም ይሆንልህ ዘንድ፥ እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ወደ ማለላቸው ወደ መልካሚቱ ምድር ገብተህ እርስዋን ትወርስ ዘንድ፥ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ ጠላቶችህን ሁሉ ከፊትህ ያወጣልህ ዘንድ፥ በእግዚአብሔር ፊት ቅኑንና መልካሙን አድርግ። 20በኋለኛው ዘመንም ልጅህ፦ አምላካችን እግዚአብሔር ያዘዛችሁ ምስክርና ሥርዓት ፍርድስ ምንድር ነው? ብሎ በጠየቀህ ጊዜ፥ 21አንተ ልጅህን በለው፦ በግብፅ የፈርዖን ባሪያዎች ነበርን፤ እግዚአብሔርም በጽኑ እጅ ከግብፅ አወጣን፤ 22እግዚአብሔርም በግብፅና በፈርዖን በቤቱም ሁሉ ላይ እኛ እያየን ታላቅና ክፋ ምልክት ተአምራትም አደረገ። 23ለአባቶቻችን ወደ ማለላቸው ምድር አግብቶ እርስዋን ይሰጠን ዘንድ ከዚያ አወጣን። 24እንደ ዛሬም በሕይወት እንዲያኖረን፥ ሁልጊዜም መልካም እንዲሆንልን፥ አምላካችንን እግዚአብሔርን እንፈራ ዘንድ፥ ይህችንም ሥርዓት ሁሉ እናደርግ ዘንድ እግዚአብሔር አዘዘን። 25እርሱም እንዳዘዘን በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት እናደርጋት ዘንድ ይህችን ትእዛዝ ሁሉ ብንጠብቅ ለእኛ ጽድቅ ይሆንልናል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ