የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘዳግም 8

8
1በሕይወት እንድትኖሩ፥ እንድትበዙም፥ እግዚአብሔርም ለአባቶቻችሁ ወደ ማለላቸው ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱአት፥ ዛሬ ለአንተ የማዝዘውን ትእዛዝ ሁሉ ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ። 2አምላክህ እግዚአብሔር ይፈትንህ ዘንድ፥ በልብህም ያለውን ትእዛዙን ትጠብቅ ወይም አትጠብቅ እንደሆነ ያውቅ ዘንድ፥ ሊያስጨንቅህ በእነዚህ በአርባ ዓመታት በምድረ በዳ የመራህን መንገድ ሁሉ አስብ። 3ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ በሕይወት እንዳይኖር ያስታውቅህ ዘንድ አስጨነቀህ፥ አስራበህም፥ አንተም ያላወቅኸውን አባቶችህም ያላወቁትን መና አበላህ። 4በእነዚህ አርባ ዓመታት የለበስኸው ልብስ አላረጀም፥ እግርህም አላበጠም። 5ሰውም ልጁን እንደሚገሥፅ እንዲሁም አምላክህ እግዚአብሔር አንተን እንዲገሥጽ በልብህ አስተውል። 6በመንገዱም እንድትሄድ እርሱንም እንድትፈራ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ። 7አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መልካም ምድር፥ ከሸለቆና ከኮረብታ የሚመነጩ የውኃ ጅረቶችና ፈሳሾች ምንጮችም ወዳሉባት ምድር፥ 8ስንዴ ገብስም ወይንም በለስም ሮማንም ወይራም ማርም ወደ ሞሉባት ምድር፥ 9ሳይጎድልህ እንጀራን ወደምትበላባት አንዳችም ወደማታጣባት ምድር፥ ድንጋይዋ ብረት ወደ ሆነ፥ ከተራራዋም መዳብ ወደሚማስባት ምድር ያገባሃል። 10ትበላማለህ፥ ትጠግብማለህ፥ ስለሰጠህም ስለመልካሚቱ ምድር አምላክህን እግዚአብሔርን ትባርካለህ። 11ዛሬ እኔ አንተን የማዝዘውን ትእዛዙንና ፍርዱን ሥርዓቱንም ባለመጠበቅ አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ፤ 12ከበላህና ከጠገብህ በኋላ፥ መልካምም ቤት ሠርተህ ከተቀመጥህበት በኋላ፥ 13የላምና የበግ መንጋ ከበዛልህ በኋላ፥ ብርህና ወርቅህም ያለህም ሁሉ ከበዛልህ በኋላ፥ ልብህ እንዳይጓደድ፤ 14ከግብፅም ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን፥ 15እባብና ጊንጥ ጥማትም ባለባት፥ ውኃም በሌለባት፥ በታላቂቱና በምታስፈራው ምድረ በዳ የመራህን፥ ከጭንጫ ድንጋይም ውኃን ያወጣልህን፥ 16በመጨረሻም ዘመን መልካም ያደርግልህ ዘንድ ሊፈትንህ ሊያዋርድህም አባቶችህ ያላወቁትን መና በምድረ በዳ ያበላህን አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ፤ 17በልብህም፦ ጉልበቴ የእጄም ብርታት ይህን ሀብት አመጣልኝ እንዳትል። 18ነገር ግን ዛሬ እንደ ሆነ ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳን ያጸና ዘንድ፥ ሀብት ለማከማቸት እርሱ ጉልበት ሰጥቶሃልና አምላክህን እግዚአብሔርን አስብ። 19አምላክህንም እግዚአብሔርን ብትረሳ፥ ሌሎችንም አማልክት ብትከተል ብታመልካቸውም ብትሰግድላቸውም፥ ፈጽሞ እንድትጠፉ እኔ ዛሬውኑ እመሰክርባችኋለሁ። 20የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልሰማችሁ እግዚአብሔር ከፊታችሁ እንደሚያጠፋቸው እንደ አሕዛብ እንዲሁ እናንተ ትጠፋላችሁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ