መጽሐፈ አስቴር 1
1
1በአርጤክስስም ዘመን እንዲህ ሆነ፥ ይህም አርጤክስስ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሀያ ሰባት አገሮች ላይ ነገሠ። 2በዚያም ዘመን ንጉሡ አርጤክስስ በሱሳ ግንብ በነበረው በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ሳለ፥ 3በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ለባለምዋሎቹና ለአገልጋዮቹ ሁሉ ግብዣ አደረገ፥ የፋርስና የሜዶን ታላላቆች ሁሉ፥ የየአገሩ አዛውንትና ሹማምት፥ በፊቱ ነበሩ፥ 4የከበረውንም የመንግሥቱን ሀብት፥ የታላቁንም የግርማዊነቱን ክብር መቶ ሰማንያ ቀን ያህል አሳያቸው። 5ይህም ቀን በተፈጸመ ጊዜ በሱሳ ግንብ ውስጥ ለተገኙት ሕዝብ ሁሉ ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ንጉሡ በንጉሡ ቤት አታክልት ውስጥ ባለው አደባባይ ሰባት ቀን ግብዣ አደረገ። 6ነጭ፥ አርንጓዴ፥ ሰማያዊም መጋረጆች ከጥሩ በፍታና ከሐምራዊ ግምጃ በተሠራ ገመድ፥ በብር ቀለበትና በዕብነ በረድ አዕማድ ላይ ተዘርግተው ነበር፥ አልጋዎቹም ከወርቅና ከብር ተሠርተው በቀይና በነጭ በብጫና በጥቁር ዕብነ በረድ ወለል ላይ ነበሩ። 7መጠጡም በልዩ ልዩ በወርቅ ዕቃ ይታደል ነበር፥ የንጉሡም የወይን ጠጅ እንደ ንጉሡ ለጋስነት መጠን እጅግ ብዙ ነበረ። 8ንጉሡም እንደ ሰው ሁሉ ፈቃድ ያደርጉ ዘንድ ለቤቱ አዛዦች ሁሉ አዝዞ ነበርና መጠጡ እንደ ወግ አልነበረም። 9ንግሥቲቱም አስጢን በንጉሡ በአርጤክስስ ቤተ መንግሥት ለሴቶች ግብዣ አደረገች።
10-11በሰባተኛውም ቀን ንጉሡ አርጤክስስ የወይን ጠጅ ጠጥቶ ደስ ባለው ጊዜ፥ ንግሥቲቱ አስጢን መልከ መልካም ነበረችና ውበትዋ ለአሕዛብና ለአለቆች እንዲታይ የመንግሥቱን ዘውድ ጭነው ወደ ንጉሡ ፊት ያመጡአት ዘንድ በፊቱ የሚያገለግሉትን ሰባቱን ጃንደረቦች ምሁማንን፥ ባዛንን፥ ሐርቦናን፥ ገበታን፥ ዘቶልታን፥ ዜታርን፥ ከርከስን አዘዛቸው። 12ነገር ግን ንግሥቲቱ አስጢን በጃንደረቦቹ እጅ በላከው በንጉሡ ትእዛዝ ትመጣ ዘንድ እንቢ አለች፥ ንጉሡም እጅግ ተቈጣ፥ በቍጣውም ተናደደ።
13ሕግንና ፍርድን በሚያውቁ ሁሉ ፊት የንጉሡ ወግ እንዲህ ነበረና ንጉሡ የዘመኑን ነገር የሚያውቁትን ጥበበኞችን፥ 14በመንግሥቱም ቀዳሚዎች ሆነው የሚቀመጡ የንጉሡ ባለምዋሎች ሰባቱ የፋርስና የሜዶን መሳፍንት አርቄስዮስ፥ ሼታር፥ አድማታ፥ ተርሺሽ፥ ሜሬስ፥ ማሌሴዓር፥ 15ምሙካን በአጠገቡ ሳሉ፦ በጃንደረቦች እጅ የተላከባትን የንጉሡን የአርጤክስስን ትእዛዝ ስላላደረገች በንግሥቲቱ በአስጢን ላይ እንደ ሕጉ የምናደርገው ምንድር ነው? አላቸው።
16ምሙካንም በንጉሡና በአዛውንቱ ፊት እንዲህ አለ፦ ንግሥቲቱ አስጢን አዛውንቱን ሁሉና በንጉሡ በአርጤክስስ አገር ያሉትን አሕዛብ ሁሉ በድላለች እንጂ ንጉሡን ብቻ የበደለች አይደለችም። 17ይህ የንግሥቲቱ ነገር ወደ ሴቶች ሁሉ ይደርሳልና፦ ንጉሡ አርጤክስስ ንግሥቲቱ አስጢን ወደ እርሱ ትገባ ዘንድ አዘዘ፥ እርስዋ ግን አልገባችም ተብሎ በተነገረ ጊዜ ባሎቻቸው በዓይናቸው ዘንድ የተናቁ ይሆናሉ። 18ዛሬም የንግሥቲቱን ነገር የሰሙት የፋርስና የሜዶን ወይዛዝር እንዲህና እንዲህ ብለው ለንጉሡ አዛውንት ሁሉ ይናገራሉ፥ ንቀትና ቍጣም ይበዛል። 19ንጉሡም ቢፈቅድ፥ አስጢን ወደ ንጉሡ ወደ አርጤክስስ ፊት ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትገባ የንጉሡ ትእዛዝ ከእርሱ ይውጣ፥ እንዳይፈርስም በፋርስና በሜዶን ሕግ ይጻፍ፥ ንጉሡም ንግሥትነትዋን ከእርስዋ ለተሻለችው ለሌላይቱ ይስጥ። 20የንጉሡም ትእዛዝ በሰፊው መንግሥቱ ሁሉ በተነገረ ጊዜ ሴቶች ሁሉ ባሎቻቸውን ታላቁንም ታናሹንም ያከብራሉ። 21ይህም ምክር ንጉሡንና አዛውንቱን ደስ አሰኛቸው፥ ንጉሡም እንደ ምሙካን ቃል አደረገ። 22ሰው ሁሉ በቤቱ አለቃ ይሁን፥ በሕዝቡም ቋንቋ ይናገር ብሎ ለአገሩ ሁሉ እንደ ጽሕፈቱ ለሕዝቡም ሁሉ እንደ ቋንቋው ደብዳቤዎችን ወደ ንጉሡ አገሮች ሁሉ ሰደደ።
Currently Selected:
መጽሐፈ አስቴር 1: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ