መጽሐፈ አስቴር 6
6
1በዚያም ሌሊት እንቅልፍ ከንጉሡ ሸሸ፥ የዘመኑንም ታሪክ መጽሐፍ ያመጡ ዘንድ አዘዘ፥ በንጉሡም ፊት ተነበበ። 2ደጁንም ከሚጠብቁት ከንጉሡ ጃንደረቦች ሁለቱ ገበታና ታራ እጃቸውን በንጉሡ በአርጤክስስ ላይ ያነሡ ዘንድ እንደ ፈለጉ፥ መርዶክዮስ እንደ ነገረው ተጽፎ ተገኘ። 3ንጉሡም፦ ስለዚህ ነገር ለመርዶክዮስ ምን ክብርና በጎነት ተደረገለት? አለ። ንጉሡንም የሚያገለግሉ ብላቴኖች፦ ምንም አልተደረገለትም አሉት። 4ንጉሡም፦ በአዳራሹ ማን አለ? አለ። ሐማም ባዘጋጀው ግንድ ላይ መርዶክዮስን ለማሰቀል ለንጉሡ ይናገር ዘንድ ወደ ንጉሡ ቤት ወደ ውጭው አዳራሽ ገብቶ ነበር። 5የንጉሡም ብላቴኖች፦ እነሆ ሐማ በአዳራሹ ቆሞአል አሉት። ንጉሡም፦ ይግባ አለ። 6ሐማም ገባ፥ ንጉሡም፦ ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወድደው ሰው ምን ይደረግለታል? አለው። ሐማም በልቡ፦ ንጉሡ ከእኔ ይልቅ ማንን ያከብር ዘንድ ይወድዳል? አለ። 7ሐማም ንጉሡን እንዲህ አለው፦ ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግ፥ 8ንጉሡ የለበሰው የክብር ልብስ፥ ንጉሡም የተቀመጠበት ፈረስ ይምጣለት፥ የንጉሡም ዘውድ በራሱ ላይ ይደረግ፥ 9ልብሱንና ፈረሱንም ከንጉሡ አዛውንት በዋነኛው እጅ ያስረክቡት፥ ንጉሡም ያከብረው ዘንድ የሚወድደውን ሰው ያልብሱት፥ በፈረሱም ላይ አስቀምጠውት በከተማይቱ አደባባይ ያሳልፉት፥ በፊቱም፦ ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግለታል ተብሎ አዋጅ ይነገር።
10ንጉሡም ሐማን፦ ፍጠን፥ እንደ ተናገርኸውም ልብሱንና ፈረሱን ውሰድ፥ በንጉሡም በር ለሚቀመጠው አይሁዳዊ ለመርዶክዮስ እንዲሁ አድርግለት፥ ከተናገርኸውም ሁሉ ምንም አይቅር አለው። 11ሐማም ልብሱንና ፈረሱን ወሰደ፥ መርዶክዮስንም አለበሰው፥ በፈረሱም ላይ አስቀመጠው፥ በከተማይቱም አደባባይ በፊቱ አሳለፈው። በፊቱም፦ ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግለታል ብሎ አዋጅ ነገረ። 12መርዶክዮስም ወደ ንጉሡ በር ተመለሰ። ሐማ ግን አዝኖና ራሱን ተከናንቦ ቸኵሎ ወደ ቤቱ ሄደ። 13ሐማም ለሚስቱ ለዞሳራና ለወዳጆቹ ሁሉ ያገኘውን ሁሉ አጫወታቸው። ጥበበኞቹና ሚስቱ ዞሳራም፦ በፊቱ መውደቅ የጀመርህለት መርዶክዮስ ከአይሁድ ወገን የሆነ እንደ ሆነ በፊቱ ፈጽሞ ትወድቃለህ እንጂ አታሸንፈውም አሉት። 14እነርሱም ሲናገሩት ሳሉ እነሆ የንጉሡ ጃንደረቦች መጡ፥ አስቴርም ወዳዘጋጀችው ግብዣ ይመጣ ዘንድ ሐማን አስቸኰሉት።
Currently Selected:
መጽሐፈ አስቴር 6: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ