ኦሪት ዘጸአት 13
13
በኵር ጁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ ስለመሆኑ
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገርው፦ 2“በእስራኤል ልጆች ዘንድ ከሰውም ከእንስሳም ማሕፀንን የሚከፍት በኵርን ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ፤ የእኔ ነው።”
የቂጣ በዓል
3ሙሴም ሕዝቡን አለ፥ “ከባርነት ቤት ከግብፅ የወጣችሁበትን ይህን ቀን አስቡ፤ እግዚአብሔር ከዚህ ቦታ በብርቱ እጅ አውጥቶአችኋልና፤ ስለዚህ የቦካ እንጀራ አትብሉ። 4እናንተ ዛሬ በአቢብ ወር ወጥታችኋል። 5እግዚአብሔርም ለአንተ ይሰጣት ዘንድ ለአባቶችህ ወደ ማለላቸው፥ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር፥ ወደ ከነዓናውያን ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ምድር ባገባህ ጊዜ ይህችን አምልኮ በዚህ ወር ታደርጋለህ። 6ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላለህ፤ በሰባተኛውም ቀን ለእግዚአብሔር በዓል ይሆናል። 7ሰባት ቀንም ሙሉ ቂጣ እንጀራ ትበላለህ፤ በአንተም ዘንድ እርሾ ያለበት እንጀራ አይታይ፤ በድንበርህም ሁሉ እርሾ አይታይ። 8በዚያም ቀን፦ ‘ከግብፅ በወጣሁ ጊዜ እግዚአብሔር ስላደረገልኝ ነው’ ስትል ለልጅህ ትነግረዋለህ። 9እግዚአብሔር በብርቱ እጅ ከግብፅ አውጥቶሃልና የእግዚአብሔር ሕግ በአፍህ ይሆን ዘንድ በእጅህ እንደ ምልክት በዓይኖችህም መካከል እንደ መታሰቢያ ይሁንልህ። 10በዓመት በዓመት በወራቱ ይህችን ሥርዓት ጠብቃት። 11እግዚአብሔርም ለአንተ፥ ለአባቶችህም እንደ ማለ ወደ ከነዓናውያን ምድር ባገባህ ጊዜ፥ እርስዋንም በሰጠህ ጊዜ፦
በኵር ሁሉ የእግዚአብሔር ስለመሆኑ
12ማሕፀንን የሚከፍተውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ለይ፤ ከሚሆንልህ ከብት ሁሉ ተባት ሆኖ አስቀድሞ የተወለደው ለእግዚአብሔር ይሆናል። 13የአህያውን በኵር በጠቦት ትዋጀዋለህ፤ ባትዋጀውም አንገቱን ትሰብረዋለህ፤ የሰውንም በኵር ሁሉ ከልጆችህ መካከል ትዋጀዋለህ። 14እንዲህም ይሆናል፤ በሚመጣው ጊዜ ልጅህ፥ ‘ይህ ምንድር ነው?’ ብሎ በጠየቀህ ጊዜ እንዲህ ትለዋለህ፦ እግዚአብሔር በብርቱ እጅ ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር አወጣን፤ 15ፈርዖንም እንዳይሰድደን ልቡን ባጸና ጊዜ እግዚአብሔር ከሰው በኵር ጀምሮ እስከ እንስሳ በኵር ድረስ በግብፅ ምድር ያለውን በኵር ሁሉ ገደለ፤ ስለዚህ ወንድ ሆኖ ማሕፀንን የከፈተውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሠዋለሁ፤ ነገር ግን የልጆቼን በኵር ሁሉ እዋጃለሁ። 16እግዚአብሔርም በብርቱ እጅ ከግብፅ አውጥቶናልና በእጅህ እንደ ምልክት፥ በዓይኖችህም መካከል እንደ ተንጠለጠለ ነገር ይሁንልህ።’”
የእሳትና የደመና ዓምድ
17እንዲህም ሆነ፤ ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ፥ ምንም ቅርብ ቢሆን እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ምድር መንገድ አልመራቸውም፤ እግዚአብሔር፥ “ሕዝቡ ሰልፉን ባየ ጊዜ እንዳይጸጽተው ወደ ግብፅም እንዳይመለስ” ብሎአልና። 18ነገር ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን በዙሪያ መንገድ በኤርትራ ባሕር ባለችው ምድረ በዳ መራቸው። የእስራኤልም ልጆች ከግብፅ ምድር ተሰልፈው ወጡ። 19ዮሴፍም፥ “እግዚአብሔር ሳይጎበኛችሁ አይቀርም፤ አፅሜን ከዚህ ከእናንተ ጋር ታወጣላችሁ” ብሎ የእስራኤልን ልጆች አምሎአቸው ነበርና ሙሴ የእርሱን አፅም ከእርሱ ጋር ወሰደ። 20ከሱኮትም ተጓዙ፤ በምድረ በዳውም ዳር በኤታም ሰፈሩ። 21በቀንና በሌሊትም ይሄዱ ዘንድ፥ መንገድ ሊያሳያቸው ቀን በደመና ዓምድ፥ ሊያበራላቸውም ሌሊት በእሳት ዓምድ እግዚአብሔር በፊታቸው ሄደ። 22የደመና ዓምድ በቀን፥ የእሳት ዓምድ በሌሊት ከሕዝቡ ፊት ከቶ ፈቀቅ አላለም።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 13: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ