የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 30

30
1የዕጣን መሠዊያውን ሥራ፤ ከግራር እንጨት አድርገው። 2ርዝመቱ አንድ ክንድ፥ ስፋቱም አንድ ክንድ፥ አራት ማዕዘን ይሁን፤ ከፍታውም ሁለት ክንድ ይሆናል፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድነት የተሠሩ ይሁኑ። 3ላይኛውንና የግድግዳውንም ዙሪያ ቀንዶቹንም በጥሩ ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ ታደርግለታለህ። 4ከክፈፉም በታች ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አድርግለት። በዚህና በዚያ በሁለቱ ጎን ታደርጋቸዋለህ፤ ለመሸከምም የመሎጊያዎች ስፍራ ይሁኑ። 5መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት አድርግ፥ በወርቅም ለብጣቸው። 6በምስክሩ ታቦት አጠገብም ካለው መጋረጃ በፊት ታኖረዋለህ ይህንም አንተን በምገናኝበት ከምስክሩ በላይ ባለው በስርየት መክደኛ ፊት ታኖረዋለህ። 7አሮንም የጣፋጭ ሽቱ እጣን ይጠንበት፤ በማለዳ በማለዳ መብራቶቹን ሲያዘጋጅ ይጠነው። 8ይህን በእግዚአብሔር ፊት ለልጅ ልጃችሁ የዘውትር ዕጣን ይሆን ዘንድ አሮን በማታ ጊዜ መብራቶቹን ሲያበራ ያጥነዋል። 9ሌላም ዕጣን፥ የሚቃጠለውንም መስዋዕት፥ የእህሉንም ቍርባን አታቀርብበትም፤ የመጠጥም ቍርባን አታፈስስበትም። 10አሮንም በአመት አንድ ጊዜ በቀንዶቹ ላይ ማስተስረያ ያደርጋል፤ በአመት አንድ ጊዜ ለልጅ ልጃችሁ ማስተስረያ በሚሆን በኃጢአት መሥዋዕት ደም ማስተስረያ ያደርግበታል። ለእግዚአብሔር ቅድስተ ቅዱሳን ናት። 11እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 12አንተ የእስራኤልን ልጆች ቍጥር ተቀብለህ፥ በቆጠርሃቸው ጊዜ መቅሰፍት እንዳይሆንባቸው፥ በቆጠርሃቸው ጊዜ ከእነርሱ ሰው ሁሉ እንደ ቍጥራቸው መጠን የነፍሱን ቤዛ ለእግዚአብሔር ይስጥ። 13አልፎ የሚቆጠር ሁሉ ግማሽ ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ይሰጣል፤ የሰቅል ግማሽ ለእግዚአብሔር ያነሣል። 14ሰቅሉ ሀያ ኦቦሊ ነው። አልፎ የተቆጠረ ሁሉ፥ ከሀያ አመት ጀምሮ ከዚያም ከፍ ያለ፥ የእግዚአብሔርን ስጦታ ይሰጣል። 15ለነፍሳችሁ ማስተስረያ የእግዚአብሔርን ስጦታ ስትሰጡ ባለ ጠጋው ከሰቅል ግማሽ አይጨምር፥ ደሀውም አያጉድል። 16የማስተስረያውንም ገንዘብ ከእስራኤል ልጆች ወስደህ ለመገናኛው ድንኳን ማገልገያ ታደርገዋለህ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ለነፍሳችሁ ቤዛ እንዲሆን ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ይሁን። 17እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 18የመታጠቢያ ሰንና መቀመጫውን ከናስ ሥራ፤ በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል እርሱን አድርገህ ውኃን ትጨምርበታለህ። 19አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠቡበታል። 20ወደ መገናኛው ድንኳን በገቡ ጊዜ፥ ለእግዚአብሔርም የእሳት መስዋዕት ያቃጥሉ ዘንድ ወደ መሠዊያው ሊያገለግሉ በቀረቡ ጊዜ፥ እንዳይሞቱ ይታጠቡበታል። 21እንዳይሞቱም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠቡ፤ ይህም ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ የዘላለም ሥርዓት ይሆንላቸዋል። 22እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 23አንተም ክቡሩን ሽቱ ውሰድ፤ የተመረጠ ከርቤ አምስት መቶ ሰቅል፥ ግማሽም ጣፋጭ ቀረፋ ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል፥ የጠጅ ሣርም እንዲሁ ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል፥ 24ብርጕድም አምስት መቶ ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ የወይራ ዘይትም አንድ የኢን መሥፈሪያ ትወስዳለህ። 25በቀማሚም ብልሃት እንደ ተሠራ ቅመም፥ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ታደርገዋለህ፤ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ይሆናል። 26የመገናኛውንም ድንኳን፥ የምሥክሩንም ታቦት፥ 27ገበታውንም ዕቃውንም ሁሉ፥ መቅረዙንም ዕቃውንም፥ የዕጣን መሰዊያውንም፥ 28ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም ትቀባበታለህ። 29ሁሉንም ትቀድሳቸዋለህ፥ ቅድስተ ቅዱሳንም ይሆናሉ፤ የሚነካቸውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። 30በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን ቅባቸው፥ ቀድሳቸውም። 31አንተም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ይህ ለልጅ ልጃችሁ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ይሁንልኝ። 32በሰው ሥጋ ላይ አይፍሰስ፤ እንደ እርሱም የተሰራ ሌላ ቅብዓት አታድርጉ፤ ቅዱስ ነው፥ ለእናንተም ቅዱስ ይሁን። 33እንደ እርሱ ያለውን የሚያደርግ ሰው፥ በሌላም ሰው ላይ የሚያፈስሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 34እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ ጣፋጭ ሽቱ ውሰድ፤ የሚንጠባጠብ ሙጫ፥ በዛጎል ውስጥ የሚገኝ ሽቱ፥ የሚሸትትም ሙጫ፥ ጥሩም እጣን ውሰድ፤ የሁሉም መጠን ግን ትክክል ይሁን። 35በቀማሚ ብልሃት እንደ ተሠራ፥ በጨው የተቀመመ ንጹሕና ቅዱስ ዕጣን አድርገው። 36ከእርሱም ጥቂት ትወቅጣለህ፥ ታልመውማለህ፤ ከዚያም ወስደህ አንተን በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ፊት ታኖረዋለህ። እርሱም የቅዱሳን ቅዱስ ይሁንላችሁ። 37እንደ እርሱ የተሠራ ዕጣን ለእናንተ አታድርጉ፤ በእናንተ ዘንድም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን። 38ሊያሸትተውም እንደ እርሱ የሚያደርግ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ