ኦሪት ዘጸአት 5
5
ሙሴና አሮን በግብፅ ንጉሥ ፊት እንደቀረቡ
1ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን ሄደው ፈርዖንን እንዲህ አሉት፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘በምድረ በዳ በዓል ያደርግልኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።”’ 2ፈርዖንም፦ “ቃሉን እሰማ ዘንድ እስራኤልንስ እለቅቅ ዘንድ እግዚአብሔር ማን ነው? እግዚአብሔርን አላውቅም፤ እስራኤልንም ደግሞ አልለቅቅም፤” አለ። 3እነርሱም፦ “የዕብራውያን አምላክ ተገናኘን፤ ቸነፈር ወይም ሰይፍ እንዳይጥልብን የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ እንድንሄድ፥ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እንድንሠዋ እንለምንሃለን፤” አሉት። 4የግብፅ ንጉሥም፦ “አንተ ሙሴ! አንተም አሮን! ሕዝቡን ለምን ሥራቸውን ታስተዋላችሁ? ወደ ተግባራችሁ ሂዱ!” አላቸው። 5ፈርዖንም፦ “እነሆ የምድሩ ሕዝብ አሁን በዝቶአል፤ እናንተም ሥራቸውን ታስፈቱአቸዋላችሁ” አለ። 6ፈርዖንም በዚያን ቀን የሕዝቡን አስገባሪዎች ሹማምቶቹንም እንዲህ ሲል አዘዘ፤ 7እንደ ወትሮው ለጡብ ሥራ ደግሞ ገለባ ለሕዝቡ አትስጡ፤ ነገር ግን እነርሱ ሄደው ገለባ ይሰብስቡ። 8ቀድሞ ያደርጉት የነበረውን የጡብ ቁጥር በእነርሱ ላይ አድርጉት፤ ምንም ከእርሱ አታጉድሉ፤ ሥራ ሰልችተዋልና ስለዚህ፥ ‘ለአምላካችን እንድንሰዋ እንሂድ’ እያሉ ይጮኻሉ። 9እርሱንም ያደርጉ ዘንድ በሰዎች ላይ ሥራው ይክበድባቸው፤ ከንቱ ቃልም አያስቡ።” 10የሕዝቡም አስገባሪዎች ሹማምቶቹም ወጡ፤ ሕዝቡንም፥ “ፈርዖን እንዲህ ይላል፦ ‘ገለባ አልሰጣችሁም። 11እናንተ ሂዱ፤ ከምታገኙበትም ስፍራ ገለባ ሰብስቡ፤ ከሥራችሁ ግን ምንም አይጎድልም፤”’ አሉአቸው። 12ሕዝቡም ስለ ገለባ እብቅ ሊሰበስቡ በግብፅ ምድር ሁሉ ተበተኑ። 13አስገባሪዎቹም፥ “ገለባ ትቀበሉበት እንደ ነበረ ጊዜ የቀን ሥራችሁን ጨርሱ፤” እያሉ አስቸኮሉአቸው። 14የፈርዖንም አስገባሪዎች፦ “ቀድሞ ታደርጉ እንደ ነበራችሁ ትናንትናና ዛሬ የተቆጠረውን ጡብ ስለ ምን አትጨርሱም?” እያሉ በእስራኤል ልጆች ላይ የተሾሙትን አለቆቹን ገረፉ። 15የእስራኤል ልጆች አለቆችም ወደ ፈርዖን መጡ፤ “ለምን በባሪያዎችህ እንዲህ ታደርጋለህ? 16ገለባ አይሰጡንም፤ የጡቡንም ሥራ እንድንሠራ ያዝዙናል፤ እነሆም ባሪያዎችህን ይገርፉናል፤ ግድፈቱ ግን በአንተ ሕዝብ ላይ ነው” ብለው ጮሁ። 17እርሱ ግን፦ “ሰልችታችኋል፤ ሰልችታችኋል፤ ስለዚህም፦ ‘እንሂድ ለእግዚአብሔርም እንሠዋ’ ትላላችሁ። 18አሁንም ሂዱ፤ ሥሩ፤ ገለባ አይሰጡአችሁም፤ የጡቡን ቁጥር ግን ታመጣላችሁ፤” አላቸው። 19የእስራኤልም ልጆች አለቆች፦ “ዕለት ዕለት ከምትሰሩት ከጡቡ ቁጥር ምንም አታጕድሉ!” ባሉአቸው ጊዜ ነገሩ እንደ ከፋባቸው አዩ። 20ከፈርዖንም ዘንድ ሲወጡ ሙሴንና አሮንን በፊታቸው ቆመው ተገናኙአቸው። 21እነርሱም፦ “በፈርዖንና በባሪያዎቹ ፊት ሽታችንን አግምታችሁታልና፥ ይገድሉንም ዘንድ ሰይፍን በእጃቸው ሰጥታችኋቸዋልና እግዚአብሔር ይመልከታችሁ፤ ይፍረድባችሁም፤” አሉአቸው። 22ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመለሰና፦ “ጌታ ሆይ! ስለ ምን ይህን ሕዝብ አስከፋህ? ስለ ምንስ ላክኸኝ? 23በስምህ እናገር ዘንድ ወደ ፈርዖን ከገባሁ ወዲህ ይህን ሕዝብ አስከፍቶታልና፤ አንተም ሕዝብህን ከቶ አላዳንኸውም፤” አለ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 5: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ