የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 25

25
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ አሞን ልጆች አቅንተህ ትንቢት ተናገርባቸው። 3ለአሞንም ልጆች እንዲህ በል፦ የጌታን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ መቅደሴ በረከሰ ጊዜ የእስራኤልም ምድር ባድማ በሆነች ጊዜ የይሁዳም ቤት በተማረኩ ጊዜ ስለ እነርሱ እሰይ ብለሃልና 4ስለዚህ፥ እነሆ፥ ርስት አድርጌ ለምሥራቅ ልጆች አሳልፌ አሰጥሃለሁ፥ እነርሱም በአንተ ውስጥ ይሰፍራሉ፥ ማደሪያዎቻቸውንም በአንተ ዘንድ ይሠራሉ፥ ፍሬህን ይበላሉ ወተትህንም ይጠጣሉ፥ 5የአሞንን ከተማ ለግመሎች ማሰማርያ፥ የአሞንንም ልጆች ለመንጋ መመሰጊያ አደርጋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 6ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በእጅህ አጨብጭበሃልና፥ በእግርህም አሸብሽበሃልና፥ በእስራኤልም ምድር ላይ በነፍስህ ንቀት ሁሉ ደስ ብሎሃልና 7ስለዚህ፥ እነሆ፥ እጄን ዘርግቼብሃለህ፥ ለአሕዛብም አስበዘብዝሃለሁ፥ ከአሕዛብም ለይቼ እቈርጥሃለሁ፥ ከአገሮችም አጠፋሃለሁ እፈጅህማለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ።
8ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሞዓብና ሴይር፦ እነሆ፥ የይሁዳ ቤት እንደ አሕዛብ ሁሉ ነው ብለዋልና 9ስለዚህ፥ እነሆ፥ የሞዓብን ጫንቃ ከከተሞቹ፥ በዳርቻው ካሉት የምድሩ ትምክሕት ከሆኑት ከተሞቹ፥ ከቤትየሺሞት፥ ከበኣልሜዎን፥ 10ከቂርያታይም፥ ከአሞን ልጆች ጋር ለምሥራቅ ልጆች እከፍታለሁ። የአሞን ልጆች በአሕዛብ መካከል ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይታሰቡ ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ። 11በሞዓብም ላይ ፍርድን አደርጋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
12ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ኤዶምያስ በይሁዳ ቤት ላይ በቀል አድርጎአልና፥ ቂም ይዞአልና፥ ብድራትንም አስከፍሎአልና፥ 13ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እጄን በኤዶምያስ ላይ እዘረጋለሁ ከእርስዋም ዘንድ ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፥ ከቴማንም ጀምሮ ባድማ አደርጋታለሁ፥ እስከ ድዳንም ድረስ በሰይፍ ይወድቃሉ። 14በሕዝቤ በእስራኤል እጅ ኤዶምያስን እበቀላለሁ፥ እንደ ቍጣዬና እንደ መዓቴም መጠን በኤዶምያስ ያደርጋሉ፥ በቀሌንም ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
15ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ፍልስጥኤማውያን በቀልን አድርገዋልና፥ በዘወትርም ጠላትነት ያጠፉ ዘንድ በነፍሳቸው ንቀት ተበቅለዋልና 16ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እጄን በፍልስጥኤማውያን ላይ እዘረጋለሁ፥ ከሊታውያንንም እቈርጣለሁ፥ የባሕሩንም ዳር ቅሬታ አጠፋለሁ። 17በመዓት መቅሠፍትም ታላቅ በቀል አደርግባቸዋለሁ፥ በቀሌንም በላያቸው ባደረግሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ