ትንቢተ ሕዝቅኤል 30
30
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ዋይ! በሉ፥ ለቀኑ ወዮ! ቀኑ ቅርብ ነው፥ 3የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፥ የደመና ቀን፥ የአሕዛብ ጊዜ ይሆናል። 4ሰይፍ በግብጽ ላይ ይመጣል፥ ሁከትም በኢትዮጵያ ይሆናል፥ የተገደሉትም በግብጽ ውስጥ ይወድቃሉ፥ ብዛትዋንም ይወስዳሉ፥ መሠረትዋም ይፈርሳል። 5ኢትዮጵያና ፉጥ ሉድም የተደባለቀም ሕዝብ ሁሉ ኩብም ቃል ኪዳንም የገባችው ምድር ልጆች ከእነርሱ ጋር በሰይፍ ይወድቃሉ።
6እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ግብጽን የሚደግፉ ይወድቃሉ፥ የኃይልዋም ትዕቢት ይወርዳል፥ ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴዌኔ ድረስ በእርስዋ ውስጥ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 7ባድማም በሆኑ አገሮች መካከል ባድማ ይሆናሉ፥ ከተሞችዋም በፈረሱ ከተሞች መካከል ይሆናሉ። 8እሳትንም በግብጽ ባነደድሁ ጊዜ ረዳቶችዋም ሁሉ በተሰበሩ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 9በዚያ ቀን መልእክተኞች ተዘልለው የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያንን ለማስፈራት ከፊቴ በመርከብ ይወጣሉ፥ እንደ ግብጽም ቀን ሁከት ይሆንባቸዋል፥ እነሆ፥ ይመጣልና።
10ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የግብጽን ብዛት በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ እሽራለሁ። 11እርሱና የአሕዛብ ጨካኞች ሕዝቡ ምድሪቱን ለማጥፋት ይመጣሉ፥ ሰይፋቸውንም በግብጽ ላይ ይመዝዛሉ ምድሪቱንም በተገደሉት ይሞላሉ። 12ወንዞችንም ምድረ በዳ አደርጋለሁ ምድሪቱንም በክፉ ሰዎች እጅ እሸጣለሁ፥ ምድሪቱንና ሙላዋንም በእንግዶች እጅ ባድማ አደርጋለሁ፥ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬያለሁ።
13ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጣዖቶቹን አጠፋለሁ ምስሎችንም ከሜምፎስ እሽራለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲያ በግብጽ ምድር አለቃ አይሆንም፥ በግብጽም ምድር ላይ ፍርሃትን አደርጋለሁ። 14ጳትሮስንም አፈርሳለሁ፥ በጣኔዎስም እሳትን አነድዳለሁ፥ በኖእ ላይም ፍርድን አደርጋለሁ። 15በግብጽም ምሽግ በሲን ላይ መዓቴን አፈስሳለሁ፥ የኖእንም ብዛት አጠፋለሁ። 16በግብጽም እሳትን አነድዳለሁ፥ ሲንም ትጨነቃለች ኖእም ትሰበራለች፥ በሜምፎስም በየቀኑ ጠላቶች ይሆኑባታል። 17የሄልዮቱ ከተማና የቡባስቱም ጕልማሶች በሰይፍ ይወድቃሉ ሴቶችም ይማረካሉ። 18የግብጽን ቀንበር በዚያ በሰበርሁ ጊዜ በጣፍናስ ቀኑ ይጨልማል የኃይልዋም ትዕቢት ይጠፋባታል፥ ደመናም ይጋርዳታል፥ ሴቶች ልጆችዋም ይማረካሉ። 19እንዲሁ በግብጽ ላይ ፍርድን አደርጋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
20እንዲህም ሆነ፥ በአሥራ አንደኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 21የሰው ልጅ ሆይ፥ የግብጽን ንጉሥ የፈርዖንን ክንድ ሰብሬያለሁ፥ እነሆም፥ በጨርቅ በመጠቅለል ይፈወስ ዘንድ ሰይፉንም ለመያዝ እንዲበረታ አልታሰረም። 22ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እኔ በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ላይ ነኝ፥ የጸናችውንና የተሰበረችውንም ክንዱን እሰብራለሁ፥ ሰይፉንም ከእጁ አስረግፈዋለሁ። 23ግብጻውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናለሁ ወደ አገሮችም እዘራቸዋለሁ። 24የባቢሎንንም ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ ሰይፌንም በእጁ እሰጣለሁ፥ የፈርዖንን ክንድ ግን እሰብራለሁ፥ ተወግቶም በሚሞተው እንጕርጕሮ በፊቱ ያንጐራጕራል። 25የባቢሎንንም ንጉሥ ክንድ አጸናለሁ የፈርዖንም ክንድ ይወድቃል፥ ሰይፌንም በባቢሎን ንጉሥ እጅ በሰጠሁ ጊዜ እርሱም በግብጽ ምድር ላይ በዘረጋው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 26ግብጻውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናለሁ ወደ አገሮችም እዘራቸዋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 30: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ