ትንቢተ ሕዝቅኤል 37
37
1የእግዚአብሔርም እጅ በላዬ ነበረ እግዚአብሔርም በመንፈሱ አወጣኝ አጥንቶችም በሞሉባት ሸለቆ መካከል አኖረኝ። 2በእነርሱም አንጻር በዙሪያቸው አሳለፈኝ፥ እነሆም፥ በሸለቆው ፊት እጅግ ብዙ ነበሩ፥ እነሆም፥ እጅግ ደርቀው ነበር። 3እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች በሕይወት ይኖራሉን? አለኝ። እኔም፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ አልሁ። 4እርሱም እንዲህ አለኝ፦ በእነዚህ አጥንቶች ላይ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፦ እናንተ የደረቃችሁ አጥንቶች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ሰሙ። 5ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ትንፋሽን አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላላችሁ። 6ጅማትም እሰጣችኋለሁ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ በእናንተም ላይ ቁርበትን እዘረጋለሁ ትንፋሽንም አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
7እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፥ ስናገርም ድምፅ ሆነ፥ እነሆም፥ መናወጥ ሆነ፥ አጥንቶችም አጥንት ከአጥንት ጋር ተቀራረቡ። 8እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ጅማት ነበረባቸው ሥጋም ወጣ ቁርበትም በላያቸው ተዘረጋ፥ ትንፋሽ ግን አልነበረባቸውም። 9እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስም፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፋስ ሆይ፥ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፥ እነዚህም የተገደሉት በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እፍ በልባቸው በል አለኝ። 10እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፥ ትንፋሽም ገባባቸው ሕያዋንም ሆኑ፥ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ።
11እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች የእስራኤል ቤት ሁሉ ናቸው፥ እነሆ፦ አጥንቶቻችን ደርቀዋል ተስፋችንም ጠፍቶአል ፈጽመንም ተቈርጠናል ብለዋል። 12ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሕዝቤ ሆይ፥ እነሆ፥ መቃብራችሁን እከፍታለሁ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ፥ ወደ እስራኤልም ምድር አገባችኋለሁ። 13ሕዝቤ ሆይ፥ መቃብራችሁን በከፈትሁ ጊዜ ከመቃብራችሁም ባወጣኋችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 14መንፈሴንም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፥ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፥ በገዛ ምድራችሁም አኖራችኋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ እንዳደረግሁም ታውቃላችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
15የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 16አንተ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ አንድ በትር ውሰድና፦ ለይሁዳና ለባንጀሮቹ ለእስራኤል ልጆች ብለህ በላዩ ጻፍ፥ ሌላም በትር ውሰድና፦ የኤፍሬም በትር ለዮሴፍና ለባልንጀሮቹ ለእስራኤል ቤት ሁሉ ብለህ በላዩ ጻፍ። 17አንድ በትርም እንዲሆኑ አንዱን ከሁለተኛው ጋር ለአንተ አጋጥም፥ በእጅህም ውስጥ አንድ ይሁኑ። 18የሕዝብህም ልጆች፦ ይህ የምታደርገው ነገር ምን ማለት እንደሆነ አትነግረንምን? ብለው በተናገሩህ ጊዜ፥ አንተ፦ 19ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በኤፍሬም እጅ ያለውን የዮሴፍን በትር ባልንጀሮቹንም የእስራኤልን ነገዶች እወስዳለሁ፥ ከእርሱም ከይሁዳ በትር ጋር አጋጥማቸዋለሁ አንድ በትርም አደርጋቸዋለሁ፥ በእጄም ውስጥ አንድ ይሆናሉ በላቸው። 20የምትጽፍባቸውም በትሮች በዓይናቸው ፊት በእጅህ ውስጥ ይሆናሉ። 21አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የእስራኤልን ልጆች ከሄዱባቸው ከአሕዛብ መካከል እወስዳለሁ ከስፍራም ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ፥ 22በምድርም ላይ በእስራኤል ተራሮች ላይ አንድ ሕዝብ አደርጋቸዋለሁ፥ አንድ ንጉሥም በሁላቸው ላይ ይነግሣል፥ ከዚያ ወዲያ ሁለት ሕዝብ አይሆኑም፥ ከዚያ ወዲያም ሁለት መንግሥቶች ሆነው አይለዩም። 23ከዚያ ወዲያም በጣዖቶቻቸውና በርኵሰታቸው በመተላለፋቸውም ሁሉ አይረክሱም፥ ኃጢአትም ከሠሩባት ዓመፅ ሁሉ አድናቸዋለሁ አነጻቸውማለሁ፥ ሕዝብም ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
24ባሪያዬም ዳዊት ንጉሥ ይሆናቸዋል፥ ለሁሉም አንድ እረኛ ይሆንላቸዋል፥ በፍርዴም ይሄዳሉ ትእዛዜንም ይጠብቃሉ ያደርጓትማል። 25አባቶቻችሁም በኖሩባት ለባሪያዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት ምድር ይኖራሉ፥ እነርሱና ልጆቻቸው የልጅ ልጆቻቸውም ለዘላለም ይኖሩባታል፥ ባሪያዬም ዳዊት ለዘላለም አለቃ ይሆናቸዋል። 26የሰላምም ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደርጋለሁ፥ የዘላለምም ቃል ኪዳን ይሆንላቸዋል፥ እኔም እባርካቸዋለሁ አበዛቸውማለሁ መቅደሴንም ለዘላለም በመካከላቸው አኖራለሁ። 27ማደሪያዬም በላያቸው ላይ ይሆናል፥ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። 28መቅደሴም ለዘላለም በመካከላቸው በሆነ ጊዜ፥ እኔ እስራኤልን የምቀድሰው እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 37: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ