የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 38

38
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን በጎግ ላይና በማጎግ ምድር ላይ፥ በሞሳሕና በቶቤል ዋነኛ አለቃ ላይ አቅናበት፥ ትንቢትም ተናገርበት፥ 3እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሞሳሕና የቶቤል ዋነኛ አለቃ ጎግ ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ። 4እመልስህማለሁ በመንጋጋህም ልጓም አገባብሃለሁ፥ አንተንና ሠራዊትህንም ሁሉ፥ ፈረሶችንና ፈረሰኞችን የጦር ልብስ የለበሱትን ሁሉ፥ ጋሻና ራስ ቍርን ሰይፍንም ያያዙትን ሁሉ፥ ታላቁን ወገን አወጣለሁ፥ 5ፋርስንና ኢትዮጵያን ፉጥንም ከእነርሱ ጋር ጋሻና የራስ ቍርን የለበሱትን ሁሉ፥ 6ጋሜርንና ጭፍሮቹን ሁሉ፥ በሰሜን ዳርቻም ያለውን የቴርጋማን ቤትና ጭፍሮቹን ሁሉ፥ ብዙዎችንም ሕዝቦች ከአንተ ጋር አወጣለሁ።
7አንተና ወደ አንተ የተሰበሰቡ ወገኖችህ ሁሉ ተዘጋጁ፥ አንተም ራስህን አዘጋጅተህ አለቃ ሁናቸው። 8ከብዙ ዘመንም በኋላ ትፈለጋለህ፥ በኋለኛውም ዘመን፥ የዘላለም ባድማ በነበሩ በእስራኤል ተራሮች ላይ ከብዙ ሕዝብ ውስጥ ወደ ተሰበሰበች፥ ከሰይፍ ወደ ተመለሰች ምድር ትገባለህ፥ እርስዋም ከሕዝብ ውስጥ ወጥታለች ሁሉም ሳይፈሩ ይቀመጡባታል። 9አንተም ትወጣለህ፥ እንደ ዐወሎ ነፋስም ትመጣለህ፥ አንተና ጭፍሮችህ ሁሉ ከአንተም ጋር ብዙ ሕዝብ ምድርን እንደ ደመና ትሸፍናላችሁ።
10ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚያ ቀን ነገር ወደ ልብህ ይገባል፥ ክፉ አሳብንም ታስባለህ፥ 11እንዲህም ትላለህ፦ ቅጥርን ወደሌላቸው መንደሮች እወጣለሁ፥ ተዘልለው ወደሚኖሩ፥ ሁላቸው ሳይፈሩ ያለ ቅጥርና ያለ መወርወሪያ ያለ መዝጊያም ወደሚቀመጡ እገባለሁ፥ 12ምርኮን ትማርክ ዘንድ ብዝበዛንም ትበዘብዝ ዘንድ፥ ባድማም በነበሩ አሁንም ሰዎች በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ላይ፥ ከአሕዛብም በተሰበሰበ፥ ከብትና ዕቃንም ባገኘ፥ በምድርም መካከል በተቀመጠ ሕዝብ ላይ እጅህን ትዘረጋ ዘንድ። 13ሳባና ድዳን የተርሴስም ነጋዴዎች መንገዶችዋም ሁሉ፦ ምርኮን ትማርክ ዘንድ መጥተሃልን? ብዝበዛንስ ትበዘብዝ ዘንድ ብርንና ወርቅንስ ትወስድ ዘንድ ከብትንና ዕቃንስ ትወስድ ዘንድ እጅግስ ብዙ ምርኮ ትማርክ ዘንድ ወገንህን ሰብስበሃልን? ይሉሃል።
14አንተ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለዚህ ትንቢት ተናገር ጎግንም እንዲህ በለው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚያ ቀን ሕዝቤ እስራኤል ሳይፈራ በተቀመጠ ጊዜ አንተ አታውቀውምን? 15አንተም፥ ከአንተም ጋር ብዙ ሕዝብ ሁላቸው በፈረሶች ላይ የተቀመጡ ታላቅ ወገንና ብርቱ ሠራዊት፥ ከሰሜን ዳርቻ ከስፍራችሁ ትመጣላችሁ። 16ምድርንም ትሸፍን ዘንድ እንደ ደመና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። በኋለኛው ዘመን ይሆናል፥ ጎግ ሆይ፥ በዓይናቸው ፊት በተቀደስሁብህ ጊዜ አሕዛብ ያውቁኝ ዘንድ በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ።
17ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእነርሱ ላይ እንደማመጣህ በዚያች ዘመን ብዙ ዓመት ትንቢት በተናገሩ በባሪያዎቼ በእስራኤል ነቢያቶች በቀደመው ዘመን ስለ እርሱ የተናገርሁ አንተ ነህን? 18በዚያም ቀን ጎግ በእስራኤል ምድር ላይ በመጣ ጊዜ መቅሠፍቴ በመዓቴ ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 19በቅንዓቴና በመዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ፦ በእርግጥ በዚያ ቀን በእስራኤል ምድር ጽኑ መናወጥ ይሆናል፥ 20ከፊቴም የተነሣ የባሕር ዓሣዎችና የሰማይ ወፎች የምድረ በዳም አራዊት በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ በምድርም ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ፥ ተራሮችም ይገለባበጣሉ ገደላገደሎችም ይወድቃሉ ቅጥርም ሁሉ ወደ ምድር ይወድቃል። 21በተራሮቼም ሁሉ በእርሱ ላይ ሰይፍን እጠራለሁ፥ የሰውም ሁሉ ሰይፍ በወንድሙ ላይ ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 22በቸነፈርና በደም እፈርድበታለሁ፥ ዶፍም የበረዶም ድንጋይ እሳትና ድኝም በእርሱና በጭፍሮቹ ከእርሱም ጋር ባሉ በብዙ ሕዝብ ላይ አዘንባለሁ። 23ታላቅ እሆናለሁ እቀደስማለሁ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ