የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 6

6
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ እስራኤል ተራሮች አቅና ትንቢትም ተናገርባቸው። 3እንዲህም በል፦ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የጌታን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኮረብቶች ለምንጮችና ለሸለቆች እንዲህ ይላል፦ እኔ፥ እነሆ፥ እኔ ሰይፍን አመጣባችኋለሁ የኮረብታው መስገጃዎቻችሁንም አጠፋለሁ። 4መሠዊያዎቻችሁም ይፈርሳሉ፥ የፀሐይም ምስሎቻችሁ ይሠበራሉ፥ ተወግተውም የሞቱትን ሰዎቻችሁን በጣዖቶቻችሁ ፊት እጥላለሁ። 5የእስራኤልንም ልጆች ሬሳዎች በጣዖቶቻቸው ፊት አኖራለሁ፥ አጥንቶቻችሁንም በመሠዊያዎቻችሁ ዙሪያ እበትናለሁ። 6በምትኖሩበትም ስፍራ ሁሉ ከተሞቹ ይፈርሳሉ፥ የኮረብታው መስገጃዎችም ሁሉ ውድማ ይሆናሉ፥ መሠዊያዎቻችሁ ይፈርሳሉ ባድማም ይሆናሉ፥ ጣዖቶቻችሁም ይሰበራሉ ያልቃሉም፥ የፀሐይም ምስሎቻችሁ ይቈረጣሉ፥ ሥራችሁም ይሻራል። 7ተወግተውም የሞቱት በመካከላችሁ ይወድቃሉ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
8ነገር ግን በአገሮች በተበተናችሁ ጊዜ ከሰይፍ ያመለጡትን ቅሬታ በአሕዛብ መካከል አስቀርላችኋለሁ። 9ከእናንተም የዳኑት ከእኔ በራቀው በአመንዝራ ልባቸውና ጣዖቶቻቸውን በተከተሉ በአመንዝራ ዓይኖቻቸው የተሰበርሁትን እኔን ወደ እነርሱ በተማረኩት አሕዛብ መካከል ሆነው ያስቡኛል፥ በርኵሰታቸውም ሁሉ ስላደረጉት ክፋት ራሳቸውን ይጸየፋሉ። 10እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ ይህን ክፉ ነገር አደርግባቸው ዘንድ መናገሬ በከንቱ አይደለም።
11ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእጅህ አጨብጭብ በእግርህም አሸብሽብ እንዲህም በል፦ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይወድቃሉና ስለ እስራኤል ቤት ስለ አስጸያፊ ሥራዎቻቸው ሁሉ ወዮ! 12በሩቅ ያለው በቸነፈር ይሞታል፥ በቅርብም ያለው በሰይፍ ይወድቃል፥ የቀረውና የዳነውም በራብ ይሞታል፥ እንዲሁ መዓቴን እፈጽምባቸዋለሁ። 13ተወግተውም የሞቱ ሰዎቻቸው በጣዖቶቻቸው መካከልና በመሠዊያዎቻቸው ዙሪያ፥ ለጣዖቶቻቸው ጣፋጭ ሽታ ባቀረቡበት ስፍራ፥ ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ በተራሮችም ራስ ሁሉ ላይ፥ ከለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ቅጠሉም ከበዛ ከአድባር ዛፍ ሁሉ በታች በሆኑ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 14እጄንም እዘረጋባቸዋለሁ፥ በሚኖሩበትም ስፍራ ሁሉ ምድሪቱን ከዴብላታ ምድረ በዳ ይልቅ ውድማና በረሃ አደርጋታለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ