ትንቢተ ሆሴዕ 4
4
1እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እውነትና ምሕረት እግዚአብሔርንም ማወቅ በምድር ስለሌለ እግዚአብሔር በምድሩ ላይ ከሚኖሩ ጋር ክርክር አለውና የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 2እርግማንና ሐሰት ግዳይና ስርቆት ምንዝርናም ወጥተዋል፥ ደምም ወደ ደም ደርሶአል። 3ስለዚህ ምድሪቱ ታለቅሳለች፥ በእርስዋም የሚቀመጡ ሁሉ ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ጋር ይደክማሉ፥ የባሕሩም ዓሦች ያልቃሉ። 4ነገር ግን ሕዝብህ ከካህን ጋር እንደሚከራከሩ ናቸውና ማንም አይከራከር፥ ማንም አይዝለፍ። 5በቀንም ትሰናከላለህ፥ ነቢዩም ከአንተ ጋር በሌሊት ይሰናከላል፥ እናትህንም አጠፋታለሁ።
6ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፥ አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ፥ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ። 7እንደ ብዛታቸው መጠን ኃጢአት ሠሩብኝ፥ እኔም ክብራቸውን ወደ ነውር እለውጣለሁ። 8የሕዝቤም ኃጢአት መብል ሆኖላቸዋል፥ ልባቸውንም ወደ በደላቸው አድርገዋል። 9እንደ ሕዝቡም እንዲሁ ካህኑ ይሆናል፥ በመንገዳቸውም እበቀላቸዋለሁ፥ ሥራቸውንም እመልስባቸዋለሁ። 10እግዚአብሔርንም መጠበቅ ትተዋልና ሲበሉ አይጠግቡም፥ ሲያመነዝሩም አይበዙም።
11ግልሙትናና የወይን ጠጅ ስካርም አእምሮን ያጠፋል። 12የግልሙትና መንፈስ ሕዝቤን አስቶአቸዋልና፥ እነርሱም ከአምላካቸው ርቀው አመንዝረዋልና በትራቸውን ይጠይቃሉ፥ ዘንጋቸውም ይመልስላቸዋል። 13በተራሮችም ራስ ላይ ይሠዋሉ፥ ጥላውም መልካም ነውና ከኮምበልና ከልብን ከአሆማም ዛፍ በታች በኮረብቶች ላይ ያጥናሉ፥ ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁ ይገለሙታሉ፥ ሙሽሮቻችሁም ያመነዝራሉ። 14ወንዶችም ደግሞ ከጋለሞቶች ጋር ይጫወታሉና፥ ከጋለሞቶችም ጋር ይሠዋሉና ሴቶች ልጆቻችሁ በገለሞቱ ጊዜ፥ ሙሽሮቻችሁም ባመነዘሩ ጊዜ አልቀጣቸውም፥ የማያስተውልም ሕዝብ ይገለበጣል።
15እስራኤል ሆይ፥ አንተ ብታመነዝር ይሁዳ አይበድል፥ እናንተም ወደ ጌልገላ አትግቡ፥ ወደ ቤትአዌንም አትውጡ፥ ወይም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ብላችሁ አትማሉ። 16እስራኤል እንደ እልከኛ ጊደር እንቢ ብሎአል፥ እግዚአብሔርስ በሰፊው ቦታ እንደ ጠቦት ያሰማራዋልን? 17ኤፍሬም ከጣዖታት ጋር ተጋጠመ፥ ተወው። 18ስካርን ፈጽመዋል፥ ግልሙትናንም አብዝተዋል፥ አለቆችዋም ነውርን እጅግ ወደዱ። 19ነፋስ በክንፍዋ አስሮአታል፥ ከመሥዋዕታቸውም የተነሣ ያፍራሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 4: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ