የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 36

36
1እንዲህም ሆነ፥ በንጉሡ በሕዝቅያስ በአሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ይሁዳ ወደ ተመሸጉት ከተሞች ሁሉ ወጥቶ ወሰዳቸው። 2የአሦርም ንጉሥ ራፋስቂስን ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም ላከ፥ እርሱም በአጣቢው እርሻ መንገድ ባለችው በላይኛይቱ ኵሬ መስኖ አጠገብ ቆመ። 3የቤቱም አዛዥ የኤልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እርሱ ወጡ። 4ራፋስቂስም አላቸው፦ ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ይህ የሚትታመንበት መተማመኛ ምንድር ነው? 5እኔ፦ ለሰልፍ የሆነው ምክርህና ኃይልህ ከንቱ ነገር ነው አልሁ፥ አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው? 6እነሆ፥ በዚህ በተቀጠቀጠ በሸንበቆ በትር በግብጽ ትታመናለህ፥ ሰው ቢመረኰዘው ተሰብሮ በእጁ ይገባል ያቈስለውማል፥ የግብጽ ንጉሥ ፈርኦን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው። 7አንተም፦ በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን ብትለኝ፥ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን፦ በዚህ መሠዊያ ፊት ስገዱ ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያዎቹን ያስፈረሰ ይህ አይደለምን? 8አሁን እንግዲህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተወራረድ፥ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ብቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ። 9ስለ ሰረገሎችና ስለ ፈረሰኞች በግብጽ ስትታመን፥ ከጌታዬ ባሪያዎች የሚያንሰውን የአንዱን አለቃ ፊት ትቃወም ዘንድ እንዴት ይቻልሃል? 10አሁንም በውኑ ያለ እግዚአብሔር ይህን አገር አጠፋ ዘንድ ወጥቻለሁን? እግዚአብሔር፦ ወደዚህ አገር ወጥተህ አጥፋው አለኝ። 11ኤልያቄምና ሳምናስ ዮአስም ራፋስቂስን፦ እኛ እንሰማለንና እባክህ፥ በሶርያ ቋንቋ ለባርያዎችህ ተናገር፥ በቅጥርም ላይ ባለው ሕዝብ ጆሮ በአይሁድ ቋንቋ አትናገረን አሉት። 12ራፋስቂስ ግን፦ ጌታዬ ይህን ቃል እናገር ዘንድ ወደ አንተና ወደ ጌታህ ልኮኛልን? ከእናንተ ጋር ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥር ላይ ወደ ተቀመጡ ሰዎች አይደለምን? አላቸው። 13ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በአይሁድ ቋንቋ እንዲህ ብሎ ጮኸ፦ የታላቁን የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ። 14ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ ያድናችሁ ዘንድ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፥ 15ሕዝቅያስም፦ እግዚአብሔር በእርግጥ ያድነናል ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ። 16ሕዝቅያስንም አትስሙ፥ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ከእኔ ጋር ታረቁ ወደ እኔም ውጡ፥ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ብሉ፥ ከጕድጓዳችሁም ውኃ ጠጡ፥ 17ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን ወዳለባት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ ነው። 18ሕዝቅያስም፦ እግዚአብሔር ያድነናል ብሎ እንዳያታልላችሁ ተጠንቀቁ። በውኑ የአሕዛብ አማልክት አገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን? 19የሐማትና የአልፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይም አማልክት ወዴት አሉ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን? 20እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ አገሩን ከእጄ ያዳነ ማን ነው? 21እነርሱም ዝም አሉ፥ አንዳችም አልመለሱለትም፥ ንጉሡ እንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና። 22የቤቱ አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፥ የራፋስቂስንም ቃል ነገሩት።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ