ትንቢተ ኢሳይያስ 49

49
1ደሴቶች ሆይ፥ ስሙኝ፥ እናንተም በሩቅ ያላችሁ አሕዛብ፥ አድምጡ፥ እግዚአብሔር ከማኅፀን ጠርቶኛል፥ ከእናቴም ሆድ ጀምሮ ስሜን አንስቶአል፥ 2አፌንም እንደ ተሳለ ሰይፍ አድርጎአል፥ በእጁ ጥላ ሰውሮኛል፥ እንደ ተሳለ ፍላጻም አድርጎኛል፥ በሰገባውም ውስጥ ሸሽጎኛል። 3እርሱም፦ እስራኤል ሆይ፥ አንተ ባሪያዬ ነህ በአንተም እከበራለሁ አለኝ። 4እኔ ግን፦ በከንቱ ደከምሁ፥ ምንም ጥቅም ለሌለውና ለከንቱ ጕልበቴን ፈጀሁ፥ ፍርዴ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ፥ ዋጋዬም በአምላኬ ዘንድ ነው አልሁ። 5አሁንም በእግዚአብሔር ዓይን ከብሬአለሁና፥ አምላኬም ጕልበት ሆኖኛልና ያዕቆብን ወደ እርሱ እንድመልስ እስራኤልንም ወደ እርሱ እንድሰበስብ ባሪያ እሆነው ዘንድ ከማኅፀን ጀምሮ የሠራኝ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። 6እርሱም፦ የያዕቆብን ነገዶች እንድታስነሣ ከእስራኤልም የዳኑትን እንድትመልስ ባሪያዬ ትሆን ዘንድ እጅግ ቀላል ነገር ነውና እስከ ምድር ዳር ድረስ መድኃኒት ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ ይላል። 7የእስራኤል ታዳጊ ቅዱሱም፥ እግዚአብሔር፥ ሰዎች በሚንቁት ሕዝብም ለሚጠላው ለገዢዎች ባሪያ እንዲህ ይላል፦ ስለ ታማኙ ስለ እግዚአብሔር ስለ መረጠህም ስለ እስራኤል ቅዱስ ነገሥታት አይተው ይነሣሉ፥ መሳፍንትም አይተው ይሰግዳሉ። 8እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በተወደደ ጊዜ ሰምቼሃለሁ፥ በመድኃኒትም ቀን ረድቼሃለሁ፥ እጠብቅህማለሁ፥ ምድርንም ታቀና ዘንድ፥ ውድማ የሆኑትንም ርስቶች ታወርስ ዘንድ፥ 9የተጋዙትንም፦ ውጡ በጨለማም የተቀመጡትን፦ ተገለጡ ትል ዘንድ ቃል ኪዳን አድርጌ ለሕዝቡ ሰጥቼሃለሁ። በመንገድም ላይ ይሰማራሉ፥ ማሰማርያቸውም በወና ኮረብታ ሁሉ ላይ ይሆናል። 10የሚራራላቸውም ይመራቸዋልና፥ በውኃም ምንጮች በኩል ይነዳቸዋልና አይራቡም፥ አይጠሙም፥ ትኩሳት ወይም ፀሐይ አይጐዳቸውም። 11ተራሮቼንም ሁሉ መንገድ አደርጋለሁ፥ 12ጎዳኖቼም ከፍ ከፍ ይላሉ። እነሆ፥ እነዚህ ከሩቅ፥ እነሆም፥ እነዚህ ከሰሜንና ከምዕራብ፥ እነዚህም ከሲኒም አገር ይመጣሉ። 13እግዚአብሔር ሕዝቡን አጽናንቶአልና፥ ለችግረኞቹም ራርቶአልና ሰማያት ሆይ፥ ዘምሩ፥ ምድር ሆይ፥ ደስ ይበልሽ ተራሮችም ሆይ፥ እልል በሉ። 14ጽዮን ግን፦ እግዚአብሔር ትቶኛል ጌታም ረስቶኛል አለች። 15በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን? አዎን፥ እርስዋ ትረሳ ይሆናል፥ እኔ ግን አልረሳሽም። 16እነሆ፥ እኔ በእጄ መጻፍ ቀርጬሻለሁ፥ ቅጥሮችሽም ሁል ጊዜ በፊቴ አሉ። 17ልጆችሽ ይፈጥናሉ፥ ያፈረሱሽና ያወደሙሽ ከአንቺ ዘንድ ይወጣሉ። 18ዓይንሽን አንስተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፥ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ። እኔ ሕያው ነኝና እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፥ እንደ ሙሽራም ትጎናጸፊአቸዋለሽ፥ ይላል እግዚአብሔር። 19ባድማሽና ውድማሽ ወናም የሆነው ምድርሽ ከሚኖሩብሽ የተነሣ ዛሬ ጠባብ ትሆናለችና፥ የዋጡሽም ይርቃሉና። 20የወላድ መካን ከሆንሽ በኋላ የተወለዱልሽ ልጆችሽ በጆሮሽ፦ ስፍራ ጠብቦኛልና እቀመጥ ዘንድ ቦታ አስፊልኝ ይላሉ። 21አንቺም በልብሽ፦ የወላድ መካን ሆኛለሁና፥ እኔም ብቻዬን ተሰድጄአለሁና ተቅበዝብዤአለሁምና እነዚህን ማን ወለደልኝ? እነዚህንስ ማን አሳደጋቸው? እነሆ፥ ብቻዬን ቀርቼ ነበር፥ እነዚህስ ወዴት ነበሩ? ትያለሽ። 22ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እጄን ወደ አሕዛብ አነሣለሁ፥ ዓላማዬንም ወደ ወገኖች አቆማለሁ፥ ወንዶች ልጆችሽንም በብብታቸው ያመጡአቸዋል፥ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃቸው ላይ ይሸከሙአቸዋል። 23ነገሥታትም አሳዳጊ አባቶችሽ ይሆናሉ፥ እቴጌዎቻቸውም ሞግዝቶችሽ ይሆናሉ፥ ግንባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል፥ የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፥ እኔንም በመተማመን የሚጠባበቁ አያፍሩም። 24በውኑ ብዝበዛ ከኃያል እጅ ይወሰዳልን? ወይስ የጨካኙ ምርኮኞች ያመልጣሉን? 25እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፦ በኃያላን የተማረኩ ይወሰዳሉ፥ የጨካኞችም ብዝበዛ ያመልጣል፥ ከአንቺ ጋር የሚጣሉትን እጣላቸዋለሁ፥ ልጆችሽንም አድናለሁ። 26አስጨናቂዎችሽንም ሥጋቸውን አስበላቸዋለሁ፥ እንደ ጣፋጭም ወይን ጠጅ ደማቸውን ጠጥተው ይሠክራሉ፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ እኔ እግዚአብሔር መድኃኒትሽና ታዳጊሽ፥ የያዕቆብ ኃያል እንደ ሆንሁ ያውቃል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ