መጽሐፈ መሳፍንት 13
13
1የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ፥ እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን እጅ አርባ ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው።
2ከዳን ወገን የሆነ ማኑሄ የሚባል አንድ የጾርዓ ሰው ነበረ፥ ሚስቱም መካን ነበረች፥ ልጅም አልወለደችም። 3የእግዚአብሔርም መልአክ ለሴቲቱ ተገልጦ እንዲህ አላት፦ እነሆ፥ አንቺ መካን ነሽ፥ ልጅም አልወለድሽም፥ ነገር ግን ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። 4አሁንም ተጠንቀቂ፥ የወይን ጠጅን የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፥ ርኩስም ነገር አትብዪ። 5እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፥ እርሱም እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ማዳን ይጀምራል። 6ሴቲቱም ወደ ባልዋ መጥታ፦ አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጣ፥ መልኩም እንደ እግዚአብሔር መልአክ እጅግ የሚያስደነግጥ ነበረ፥ ከወዴትም እንደ መጣ አልጠየቅሁትም፥ እርሱም ስሙን አልነገረኝም። 7እርሱም፦ እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ እስኪሞት ድረስ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና አሁን የወይን ጠጅ የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፥ ርኩስም ነገር አትብዪ አለኝ ብላ ተናገረች።
8ማኑሄም፦ ጌታ ሆይ፥ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው፥ እባክህ፥ እንደ ገና ወደ እኛ ይምጣ፥ ለሚወለደውም ልጅ ምን እንድናደርግ ያስገንዝበን ብሎ ወደ እግዚአብሔር ለመነ። 9እግዚአብሔርም የማኑሄን ድምፅ ሰማ፥ የእግዚአብሔርም መልአክ እንደ ገና ለሴቲቱ በእርሻ ውስጥ ተቀምጣ ሳለች ተገለጠላት፥ ባልዋ ማኑሄ ግን ከእርስዋ ጋር አልነበረም። 10ሴቲቱም ፈጥና ሮጠች ለባልዋም፦ እነሆ፥ በቀደም ዕለት ወደ እኔ የመጣው ሰው ደግሞ ተገለጠልኝ ብላ ነገረችው። 11ማኑሄም ተነሥቶ ሚስቱን ተከተለ፥ ወደ ሰውዮውም መጥቶ፦ ከዚህች ሴት ጋር የተነጋገርህ አንተ ነህን? አለው። እርሱም፦ እኔ ነኝ አለ። 12ማኑሄም፦ ቃልህ በደረሰ ጊዜ የልጁ ሥርዓት ምንድር ነው? የምናደርግለትስ ምንድር ነው? አለው። 13የእግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን፦ ሴቲቱ ከነገርኋት ሁሉ ትጠንቀቅ። 14ከወይንም ከሚወጣው ሁሉ አትብላ፥ የወይን ጠጅንም የሚያሰክርንም ነገር አትጠጣ፥ ርኩስም ነገር ሁሉ አትብላ፥ ያዘዝኋትን ሁሉ ትጠብቅ አለው።
15ማኑሄም የእግዚአብሔርን መልአክ፦ የፍየል ጠቦት እስክናዘጋጅልህ ድረስ፥ እባክህ፥ ቆይ አለው። 16የእግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን፦ አንተ የግድ ብትለኝ መብልህን አልበላም፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ማዘጋጀት ብትወድድ ለእግዚአብሔር አቅርበው አለው። ማኑሄም የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አላወቀም ነበር። 17ማኑሄም የእግዚአብሔርን መልአክ፦ ነገርህ በደረሰ ጊዜ እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው? አለው። 18የእግዚአብሔርም መልአክ፦ ስሜ ድንቅ ነውና ለምን ትጠይቃለህ? አለው። 19ማኑሄም የፍየሉን ጠቦትና የእህሉን ቁርባን ወስዶ በድንጋይ ላይ ለእግዚአብሔር አቀረበው። መልአኩም ተአምራት አደረገ፥ ማኑሄና ሚስቱም ይመለከቱ ነበር። 20ነበልባሉም ከመሠዊያው ላይ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በመሠዊያው ነበልባል ውስጥ ዐረገ፥ ማኑሄና ሚስቱም ተመለከቱ፥ በምድርም በግምባራቸው ተደፉ።
21የእግዚአብሔርም መልአክ ዳግመኛ ላማኑሄና ለሚስቱ አልተገለጠም፥ ያን ጊዜም ማኑሄ የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አወቀ። 22ማኑሄም ሚስቱን፦ እግዚአብሔርን አይተናልና ሞት እንሞታለን አላት። 23ሚስቱም፦ እግዚአብሔርስ ሊገድለን ቢወድድ ኖሮ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቁርባን ከእጃችን ባልተቀበለን፥ ይህንም ነገር ሁሉ ባላሳየን፥ እንዲህ ያለ ነገርም በዚህ ጊዜ ባላስታወቀን ነበር አለችው።
24ሴቲቱም ወንድ ልጅ ወለደች፥ ስሙንም ሶምሶን ብላ ጠራችው፥ ልጁም አደገ እግዚአብሔርም ባረከው። 25የእግዚአብሔርም መንፈስ በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በዳን ሰፈር ውስጥ ሊያነቃቃው ጀመረ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 13: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ