የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መሳፍንት 21

21
1የእስራኤልም ሰዎች፦ ከእኛ ማንም ሰው ልጁን ለብንያም ልጆች አያጋባ ብለው በምጽጳ ተማምለው ነበር። 2ሕዝቡም ወደ ቤቴል መጥተው በዚያ በእግዚአብሔር ፊት እስከ ማታ ድረስ ተቀመጡ፥ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው ጽኑ ልቅሶ አለቀሱ። 3እነርሱም፦ አቤቱ፥ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ መታጣቱ፥ ስለ ምን ይህ በእስራኤል ላይ ሆነ? አሉ። 4በነጋውም ሕዝቡ ማልደው ተነሡ፥ በዚያም መሠዊያ ሠሩ፥ የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕትንም አቀረቡ። 5የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ ስላልወጣ ሰው፦ እርሱ ፈጽሞ ይገደል ብለው ታላቅ መሐላ ምለው ነበርና፦ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ወደ ጉባኤ ወደ እግዚአብሔር ያልወጣ ማን ነው? አሉ። 6የእስራኤልም ልጆች ስለ ወንድሞቻቸው ስለ ብንያም ልጆች ተጸጽተው፦ ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ ጠፍቶአል። 7እኛ ልጆቻችንን እንዳንድርላቸው በእግዚአብሔር ምለናልና የተረፉት ሚስቶችን እንዲያገኙ ምን እናድርግ? አሉ።
8እነርሱም፦ ከእስራኤል ነገድ ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ ያልወጣ ማን ነው? አሉ። እነሆም፥ ከኢያቢስ ገለዓድ ወደ ሰፈሩ ወደ ጉባኤ ማንም አልወጣም ነበር። 9ሕዝቡም በተቈጠሩ ጊዜ፥ እነሆ፥ በኢያቢስ ገለዓድ የሚኖር ሰው አልተገኘም። 10ማኅበሩም ወደዚያ አሥራ ሁለት ሺህ ኃያላን ሰዎች ሰድደው፦ ሂዱ በኢያቢስ ገለዓድም ያሉትን ሰዎች ከሴቶችና ከሕፃናት ጋር በሰይፍ ስለት ግደሉ። 11የምታደርጉትም ይህ ነው፥ ወንዱን ሁሉ፥ ከወንድ ጋር የተኛችይቱንም ሴት ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉ ብለው አዘዙአቸው። 12ወንድ ያላወቁ አራት መቶ ቈነጃጅት ደናግሎች በኢያቢስ ገለዓድ በሚኖሩ መካከል አገኙ፥ በከነዓንም አገር ወዳለችው ወደ ሴሎ ወደ ሰፈሩ አመጡአቸው።
13ማኅበሩም ሁሉ በሬሞን ዓለት ወዳሉት ወደ ብንያም ልጆች መልክተኞችን ላኩ፥ በዕርቅ ቃልም ተናገሩአቸው። 14በዚያም ጊዜ የብንያም ልጆች ተመለሱ፥ ከኢያቢስ ገለዓድም ሴቶች ያዳኑአቸውን ሴቶች አገቡአቸው። ነገር ግን የሚበቁ ሴቶች አላገኙም። 15እግዚአብሔርም በእስራኤል ነገድ ውስጥ ስብራት ስላደረገ ሕዝቡ ስለ ብንያም ተጸጸቱ።
16የማኅበሩ ሽማግሌዎች፦ ከብንያም ሴቶች ጠፍተዋልና የቀሩት ሰዎች ሚስት እንዲያገኙ ምን እናደርጋለን? አሉ። 17ደግሞም፦ ከእስራኤል አንድ ነገድ እንዳይደመሰስ ከብንያም ላመለጡት ርስት ይኑር። 18የእስራኤልም ልጆች፦ ልጁን ለብንያም የሚድር ርጉም ይሁን ብለው ምለዋልና እኛ ልጆቻችንን ለእነርሱ ማጋባት አይሆንልንም አሉ። 19እርሱም፦ እነሆ፥ በቤቴል በሰሜን በኩል፥ ከቤቴልም ወደ ሴኬም በሚወስደው መንገድ በምሥራቅ በኩል፥ በለቦና በደቡብ በኩል ባለችው በሴሎ የእግዚአብሔር በዓል በየዓመቱ አለ አሉ። 20የብንያምንም ልጆች እንዲህ ብለው አዘዙአቸው፦ ሂዱ በወይኑም ስፍራ ተደበቁ፥ 21ተመልከቱም፥ እነሆም፥ የሴሎ ሴቶች ልጆች አታሞ ይዘው ለዘፈን ሲወጡ ከወይኑ ስፍራ ውጡ፥ ከሴሎም ሴቶች ልጆች ለየራሳችሁ ሚስት ንጠቁ፥ ወደ ብንያም ምድርም ሂዱ። 22አባቶቻቸውና ወንድሞቻቸውም ሊጣሉአችሁ ወደ እኛ በመጡ ጊዜ፦ ስለ እኛ ማሩአቸው፥ እኛ ሚስት ለያንዳንዳቸው በሰልፍ አልወሰድንላቸውምና፥ እናንተም በደል ይሆንባችሁ ስለ ነበረ አላጋባችኋቸውምና፥ እንላችኋለን። 23የብንያምም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፥ በቁጥራቸውም መጠን ከተነጠቁት ዘፋኞች ሚስት ወሰዱ፥ ወደ ርስታቸውም ተመልሰው ሄዱ፥ ከተሞችንም ሠርተው ተቀመጡባቸው። 24በዚያን ጊዜም የእስራኤል ልጆች ከዚያ ተነሡ፥ እያንዳንዱም ወደ ነገዱና ወደ ወገኑ ሄደ፥ ሰውም ሁሉ ከዚያ ወደ ርስቱ ተመለሰ።
25በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፥ ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ