የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መሳፍንት 9

9
1የይሩበኣል ልጅ አቤሜሌክም ወደ ሴኬም ወደ እናቱ ወንድሞች ሄደ፥ ለእነርሱም ለእናቱ አባት ቤተ ሰቦችም ሁሉ፦ 2በሴኬም ሰዎች ሁሉ ጆሮ፦ ሰባ የሆኑት የይሩበኣል ልጆች ሁሉ ቢገዙአችሁ ወይስ አንድ ሰው ቢገዛችሁ ምን ይሻላችኋል? ብላችሁ ንገሩአቸው ብዬ እለምናችኋለሁ፥ ደግሞ እኔ የአጥንታችሁ ፍላጭ የሥጋችሁ ቁራጭ እንደ ሆንሁ አስቡ ብሎ ተናገራቸው። 3የእናቱም ወንድሞች ይህን ቃል ሁሉ ስለ እርሱ በሴኬም ሰዎች ሁሉ ጆሮ ተናገሩ፥ እነርሱም፦ እርሱ ወንድማችን ነው ብለው አቤሜሌክን ለመከተል ልባቸውን አዘነበሉት። 4ከበኣልብሪትም ቤት ሰባ ብር ሰጡት፥ በዚያም አቤሜሌክ ምናምንቴዎችንና ወሮበሎችን ቀጠረበት፥ እነርሱም ተከተሉት። 5ወደ አባቱም ቤት ወደ ዖፍራ ሄደ፥ ሰባ የሆኑትን የይሩበኣልን ልጆች ወንድሞቹን በአንድ ድንጋይ ላይ አረዳቸው፥ ትንሹ የይሩበኣል ልጅ ኢዮአታም ግን ተሸሽጎ ነበርና ተረፈ። 6የሴኬምም ሰዎች ሁሉ ቤትሚሎም ሁሉ ተሰበሰቡ፥ ሄደውም በሴኬም በዓምዱ አጠገብ ባለው በአድባሩ ዛፍ በታች አቤሜሌክን አነገሡ።
7ይህንም ነገር ለኢዮአታም በነገሩት ጊዜ፥ ሄዶ በገሪዛን ተራራ ራስ ላይ ቆመ፥ ድምፁንም እንሥቶ ጮኸ፥ እንዲህም አላቸው፦ የሴኬም ሰዎች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲሰማችሁ ስሙኝ። 8አንድ ጊዜ ዛፎች በላያቸው ንጉሥ ሊያነግሡ ጌዱ፥ ወይራውንም፦ በእኛ ላይ ንገሥ አሉት። 9ወይራው ግን፦ እግዚአብሔርና ሰዎች በእኔ የሚከበሩበትን ቅባቴን ትቼ በዛፎች ላይ እንድሰፍፍ ልሂድ? አላቸው። 10ዛፎችም በለሱን፦ መጥተህ በላያችን ንገሥ አሉት። 11በለሱ ግን፦ ጣፋጭነቴንና መልካሙን ፍሬዬን ትቼ በዛፎች ላይ እንድሰፍፍ ልሂድ? አላቸው። 12ዛፎችም ውይኑን፦ መጥተህ በላያችን ንገሥ አሉት። 13ወይኑም፦ እግዚአብሔርንና ሰውን ደስ የሚያሰኘውን የወይን ጠጄን ትቼ በዛፎች ላይ እንድሰፍፍ ልሂድ? አላቸው። 14ዛፎችም ሁሉ እሾህን፦ መጠተህ በላያችን ንገሥ አሉት። 15እሾሁም ዛፎችን፦ በእውነት እኔን በእናንተ ላይ ታነግሡኝ እንደ ሆነ ኑ ከጥላዬ በታች ተጠጉ። እንዲሁም ባይሆን እሳት ከእሾህ ይውጣ፥ የሊባኖስንም ዝግባ ያቃጥል አላቸው። 16አሁን እንግዲህ አቤሜሌክን በማንገሣችሁ እውነትንና ቅንነትን አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ ለይሩበኣልም ለቤቱም በጎ አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ እንዳደረገውም መጠን ለእርሱ የተገባውን አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ 17አባቴ ስለ እናንተ ተጋድሎ ነበርና፥ ከምድያምም እጅ ሊያድናችሁ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶ ነበርና፥ 18እናንተም ዛሬ በአባቴ ቤት ተነሥታችኋልና፥ ሰባ የሆኑትን ልጆቹንም በአንድ ድንጋይ ላይ አርዳችኋልና፥ ወንድማችሁም ስለ ሆነ የባሪያይቱን ልጅ አቤሜሌክን በሴኬም ሰዎች ላይ አንግሣችኋልና፥ 19እንግዲህ ለይሩበኣልና ለቤቱ እውነትንና ቅንነትን ዛሬ አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ በአቤሜሌክ ደስ ይበላችሁ፥ እርሱ ደግሞ በእናንተ ደስ ይበለው፥ 20እንዲህ ባይሆን ግን ከአቤሜሌክ እሳት ይውጣ፥ የሴኬምንም ሰዎች ቤትሚሎንም ይብላ፥ ከሴኬምም ሰዎች ከቤትሚሎም እሳት ይውጣ፥ አቤሜሌክንም ይብላ። 21ኢዮአታምም ሸሽቶ አመለጠ፥ ወንድሙንም አቤሜሌክን ፈርቶ ወደ ብኤር ሄደ፥ በዚያም ተቀመጠ።
22አቤሜሌክም በእስራኤል ላይ ሦስት ዓመት ነገሠ። 23እግዚአብሔር በአቤሜሌክና በሴኬም ሰዎች መካከል ክፉን መንፈስ ሰደደ፥ የሴኬምም ሰዎች በአቤሜሌክ ላይ ተንኰል አደረጉ። 24ይህም የሆነው፥ በሰባ የይሩባኣል ልጆች ላይ የተደረገው ዓመፅ እንዲመጣ፥ ደማቸውም በገደላቸው በወንድማቸው በአቤሜሌክ ላይ፥ ወንድሞቹን እንዲገድል እጆቹን ባጸኑአቸው በሴኬም ሰዎች ላይ እንዲሆን ነው። 25የሴኬምም ሰዎች በተራሮች ራስ ላይ ድብቅ ጦር አደረጉ፥ መንገድ ተላላፊዎችንም ሁሉ ይዘርፉ ነበር፥ አቤሜሌክም ይህን ወሬ ሰማ።
26የአቤድም ልጅ ገዓል ከወንድሞቹ ጋር መጥቶ ወደ ሴኬም ገባ፥ የሴኬምም ሰዎች ታመኑበት። 27ወደ እርሻውም ወጡ ወይናቸውንም ለቀሙ፥ ጠመቁትም፥ የደስታም በዓል አደረጉ፥ ወደ አምላካቸውም ቤት ገቡ፥ በሉም ጠጡም፥ አቤሜሌክንም ሰደቡ። 28የአቤድም ልጅ ገዓል፦ የምንገዛለት አቤሜሌክ ማን ነው? ሴኬምስ ምንድር ነው? እርሱ የይሩብኣል ልጅ አይደለምን? ዜቡልም የእርሱ ሹም አይደለምን? ለሴኬም አባት ለኤሞር ሰዎች ተገዙ፥ 29ስለ ምንስ ለዚህ እንገዛለን? ይህ ሕዝብ ከእጄ በታች ቢሆን ኖሮ አቤሜሌክን አሳድደው ነበር አለ። አቤሜሌክንም፦ ሠራዊትህን አብዝተህ ና፥ ውጣ አለው።
30የከተማይቱ ገዥ ዜቡልም የአቤድን ልጅ የገዓልን ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ። 31እንዲህም ብሎ ወደ አቤሜሌክ በተንኮል መልክተኞች ላከ፦ እነሆ፥ የአቤድ ልጅ ገዓልና ወንድሞቹ ወደ ሴኬም መጥተዋል፥ በአንተም ላይ ከተማይቱን አሸፍተዋል። 32-33አሁንም አንተና ከአንተ ጋር ያሉት ሕዝብ በሌሊት ተነሡ፥ በሜዳም ሸምቁ፥ ነገም ፀሐይ በወጣች ጊዜ ማልደህ ተነሣ፥ በከተማይቱም ላይ ውደቅባት፥ እነሆም፥ እርሱና ከእርሱ ጋር ያሉት ሕዝብ በአንተ ላይ በወጡ ጊዜ እጅህ እንዳገኘች አድርግበት።
34አቤሜሌክና ከእርሱም ጋር ያሉት ሕዝብ ሁሉ በሌሊት ተነሡ፥ በሴኬምም አቅራቢያ በአራት ወገን ሸመቁበት። 35የአቤድም ልጅ ገዓል ወጥቶ በከተማይቱ በር አደባባይ ቆመ፥ አቤሜሌክና ከእርሱ ጋር ያሉት ሕዝብ ከሸመቁበት ስፍራ ተነሱ። 36ገዓልም ሕዝቡን ባየ ጊዜ ዜቡልን፦ እነሆ፥ ከተራሮች ራስ ሕዝብ ይወርዳል አለው። ዜቡልም፦ ሰዎች የሚመስለውን የተራሮችን ጥላ ታያለህ አለው። 37ገዓልም ደግሞ፦ እነሆ፥ ሕዝብ በምድር መካከል ይወርዳል፥ አንድም ወገን በምዖንኒም በአድባሩ ዛፍ መንገድ ይመጣል ብሎ ተናገረ። 38ዜቡልም፦ እንገዛለት ዘንድ አቤሜሌክ ማን ነው? ያልህበት አፍህ አሁን የት አለ? ይህ የናቅኸው ሕዝብ አይደለምን? አሁንም ወጥተህ ከእነርሱ ጋር ተዋጋ አለው። 39ገዓልም በሴኬም ሰዎች ፊት ወጣ፥ ከአቤሜሌክም ጋር ተዋጋ። 40አቤሜሌክም አሳደደው፥ በፊቱም ሸሸ፥ እስከ በሩም አደባባይ ድረስ ብዙዎች ተጐድተው ወደቁ።
41አቤሜሌክም በአሩማ ተቀመጠ፥ ዜቡልም ገዓልንና ወንድሞቹን በሴኬም እንዳይኖሩ አሳደዳቸው። 42በነጋውም ሕዝቡ ወደ እርሻ ወጡ፥ አቤሜሌክም ሰማ። 43ሕዝቡንም ወስዶ በሦስት ወገን ከፈላቸው፥ በሜዳም ሸመቀ፥ ተመለከተም፥ እነሆም፥ ሕዝቡ ከከተማ ወጡ፥ ተነሣባቸውም መታቸውም። 44አቤሜሌክም ከእርሱም ጋር ያሉት ወገኖች ተጣደፉ በከተማይቱም በር አደባባይ ቆሙ፥ ሁለቱም ወገኖች በእርሻው ውስጥ በነበሩት ሁሉ ላይ ሮጡባቸው፥ መቱአቸውም። 45አቤሜሌክም በዚያ ቀን ሁሉ ከከተማይቱ ጋር ተዋጋ፥ ከተማይቱንም ይዞ በእርሷ የነበሩትን ሕዝብ ገደለ፥ ከተማይቱንም አፈረሰ፥ ጨውም ዘራባት።
46በሴኬምም ግንብ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ ወደ ኤልብሪት ቤት ወደ ምሽጉ ውስጥ ገቡ። 47አቤሜሌክም በሴኬም ግንብ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ አንድ ሆነው እንደ ተሰበሰቡ ሰማ። 48አቤሜሌክና ከእርሱ ጋር ያሉትም ሕዝብ ሁሉ ወደ ሰልሞን ተራራ ወጡ፥ አቤሜሌክም በእጁ መጥረቢያ ወስዶ የዛፉን ቅርንጫፍ ቈረጠ፥ አንሥቶም በጫንቃው ላይ አደረገው፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ሕዝብ፦ እኔ ሳደርግ ያያችሁትን፥ እናንተም ፈጥናችሁ እኔ እንዳደረግሁ አድርጉ አላቸው። 49ሕዝቡም ሁሉ እንዲሁ እያንዳንዳቸው የዛፉን ቅርንጫፎች ቈረጡ፥ አቤሜሌክንም ተከትለው በምሽጉ ዙሪያ አኖሩአቸው፥ ምሽጉንም በላያቸው አቃጠሉት፥ የሴኬምም ግንብ ሰዎች ሁሉ ደግሞ አንድ ሺህ የሚያህሉ ወንድና ሴት ሞቱ።
50አቤሜሌክም ወደ ቴቤስ መጣ፥ ቴቤስንም ከብቦ ያዛት። 51በከተማይቱም ውስጥ ብርቱ ግንብ ነበረ፥ የከተማይቱም ሰዎች ሁሉ፥ ወንዱና ሴቱ ሁሉ፥ ወደዚያ ሸሹ፥ ደጁንም በኋላቸው ዘጉ፥ ወደ ግንቡም ሰገነት ላይ ወጡ። 52አቤሜሌክም ወደ ግንቡ ቀርቦ ይዋጋ ነበር፥ በእሳትም ሊያቃጥለው ወደ ግንቡ ደጅ ደረሰ። 53አንዲትም ሴት በአቤሜሌክ ራስ ላይ የወፍጮ መጅ ጣለችበት፥ አናቱንም ሰበረችው። 54እርሱም ፈጥኖ ጋሻ ዣግሬውን ጠርቶ፦ እኔን፦ ሴት ገደለችው እንዳይሉ ሰይፍህን መዝዘህ ግደለኝ አለው፥ ጉልማሳውም ወጋው፥ ሞተም። 55የእስራኤልም ሰዎች አቤሜሌክ እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ እያንዳንዱ ወደ ስፍራው ተመለሰ። 56እንዲሁ ሰባ ወንድሞቹን በመግደል አቤሜሌክ በአባቱ ላይ ያደረገውን ክፋት እግዚአብሔር መለሰበት። 57እግዚአብሔርም የሴኬምን ሰዎች ክፋት ሁሉ በራሳቸው ላይ መለሰባቸው፥ የይሩበኣል ልጅ የኢዮአታም እርግማን ደረሰባቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ