ትንቢተ ኤርምያስ 38
38
1ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ የተናገረውን ቃል የማታን ልጅ ስፋጥያስ፥ የጳስኮርም ልጅ ጎዶልያስ፥ የሰሌምያም ልጅ ዮካል፥ የመልክያም ልጅ ጳስኮር ሰሙ። 2ኤርምያስ እንዲህ ብሎአልና፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚህች ከተማ የሚቀመጥ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይሞታል፥ ወደ ከለዳውያን ግን የሚወጣ በሕይወት ይኖራል፥ ነፍሱም እንደ ምርኮ ትሆንለታለች፥ በሕይወትም ይኖራል። 3እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ይህች ከተማ በባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት እጅ በእርግጥ ትሰጣለች፥ እርሱም ይይዛታል። 4አለቆቹም ንጉሡን፦ ይህን የመሰለውን ቃል ሲነግራቸው በዚህች ከተማ የቀሩትን የሰልፈኞቹን እጅ የሕዝቡንም ሁሉ እጅ ያደክማልና ይህ ሰው እንዲገደል እንለምንሃለን፥ ይህ ሰው ክፋትን እንጂ ለዚህ ሕዝብ ሰላምን አይመኝለትምና አሉት። 5ንጉሡም ሴዴቅያስ፦ ንጉሡ በእናንተ ላይ ምንም ሊያደርግ አይችልምና እነሆ፥ በእጃችሁ ነው አለ። 6ኤርምያስንም ወሰዱት በግዞት ቤቱም አደባባይ ወደ ነበረው ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ መልክያ ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት፥ ኤርምያስንም በገመድ አወረዱት። በጕድጓድም ውስጥ ጭቃ እንጂ ውኃ አልነበረበትም፥ ኤርምያስም ወደ ጭቃው ውስጥ ገባ።
7በንጉሡም ቤት የነበረው ጃንደረባ ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ኤርምያስን በጕድጓዱ ውስጥ እንዳኖሩት ሰማ። ንጉሡም በብንያም በር ተቀምጦ ነበር። 8አቤሜሌክም ከንጉሡ ቤት ወጥቶ ንጉሡን እንዲህ አለው፦ 9ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ነቢዩን ኤርምያስን በጕድጓድ ውስጥ በመጣላቸው በእርሱ ላይ በማድረጋቸው ሁሉ ክፉ አድርገዋል፥ በከተማይቱም ውስጥ እንጀራ ስለሌለ በዚያ በራብ ይሞታል። 10ንጉሡም ኢትዮጵያዊውን አቤሜሌክን፦ ከአንተ ጋር ሠላሳ ሰዎች ከዚህ ውሰድ፥ ነቢዩም ኤርምያስ ሳይሞት ከጕድጓድ አውጣው ብሎ አዘዘው። 11አቤሜሌክም ከእርሱ ጋር ሰዎችን ይዞ ሄደ፥ ከቤተ መዛግብቱም በታች ወደ ነበረው ወደ ንጉሥ ቤት ገባ፥ ከዚያም አሮጌ ጨርቅና እላቂ ልብስ ወሰደ፥ ወደ ኤርምያስም ወደ ጉድጓድ ውስጥ በገመድ አወረደው። 12ኢትዮጵያዊውም አቤሜሌክ ኤርምያስን፦ ይህን አሮጌ ጨርቅና እላቂውን ልብስ በብብትህ ከገመዱ በታች አድርግ አለው፥ ኤርምያስም እንዲሁ አደረገ። 13ኤርምያስንም በገመዱ ጐተቱት ከጕድጓድም አወጡት፥ ኤርምያስም በግዞት ቤት አደባባይ ተቀመጠ።
14ንጉሡም ሴዴቅያስ ልኮ በእግዚአብሔር ቤት ወደ ነበረው ወደ ሦስተኛው መግቢያ ወደ እርሱ ነቢዩን ኤርምያስን አስመጣው፥ ንጉሡም ኤርምያስን፦ አንዲት ነገር እጠይቅሃለሁ፥ ምንም አትሸሽገኝ አለው። 15ኤርምያስም ሴዴቅያስን፦ ብነግርህ በውኑ አትገድለኝምን? ብመክርህም አትሰማኝም አለው። 16ንጉሡም ሴዴቅያስ፦ ይህችን ነፍስ የፈጠረልን ሕያው እግዚአብሔርን! አልገድልህም፥ ነፍስህንም ለሚሹ ለእነዚህ ሰዎች እጅ አሳልፌ አልሰጥህም ብሎ በቈይታ ለኤርምያስ ማለ።
17ኤርምያስም ሴዴቅያስን፦ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ብትወጣ፥ ነፍስህ በሕይወት ትኖራለች ይህችም ከተማ በእሳት አትቃጠልም፥ አንተም ቤትህም በሕይወት ትኖራላችሁ። 18ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ባትወጣ ግን፥ ይህች ከተማ በከለዳውያን እጅ ትሰጣለች፥ በእሳትም ያቃጥሉአታል አንተም ከእጃቸው አታመልጥም አለው። 19ንጉሡም ሴዴቅያስ ኤርምያስን፦ ወደ ከለዳውያን በኰበለሉት በአይሁድ እጅ አሳልፈው ይሰጡኛል እነርሱም ያፌዙብኛል ብዬ እፈራለሁ አለው። 20ኤርምያስም እንዲህ አለው፦ አሳልፈው አይሰጡህም። እኔ የምነግርህን የእግዚአብሔርን ቃል እባክህ፥ ስማ፥ ይቀናሃል ነፍስህም በሕይወት ትኖራለች። 21ትወጣ ዘንድ እንቢ ብትል ግን፥ እግዚአብሔር ያሳየኝ ቃል ይህ ነው። 22እነሆ፥ በይሁዳ ንጉሥ ቤት የቀሩትን ሴቶች ሁሉ ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ያወጣሉ፥ እነዚያም ሴቶች፦ ባለምዋሎችህ አታልለውሃል አሸንፈውህማል፥ እግሮችህ ግን አሁን በጭቃ ውስጥ ከገቡ እነርሱ ከአንተ ወደ ኋላ ተመልሰዋል ይላሉ። 23ሚስቶችህንና ልጆችህንም ሁሉ ወደ ከለዳውያን ያወጣሉ፥ አንተም በባቢሎን ንጉሥ እጅ ትያዛለህ እንጂ ከእጃቸው አታመልጥም፥ ይህችም ከተማ በእሳት ትቃጠላለች።
24ሴዴቅያስም ኤርምያስን እንዲህ አለው፦ ይህም ቃል ማንም አይወቅ፥ አንተም አትሞትም። 25አለቆቹ ግን እኔ ከአንተ ጋር እንደ ተነጋገርሁ ቢሰሙ፥ ወደ አንተም መጥተው፦ ለንጉሡ ያልኸውን ንገረን አትሸሽገንም፥ እኛም አንገድልህም፥ ደግሞ ንጉሡ ያለህን ንገረን ቢሉህ፥ አንተ፦ 26በዚያ እሞት ዘንድ ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ ብዬ በንጉሡ ፊት ለመንሁ በላቸው። 27አለቆቹም ሁሉ ወደ ኤርምያስ መጥተው ጠየቁ፥ ንጉሡም እንዳዘዘው እንደዚህ ቃል ሁሉ ነገራቸው። ነገሩም አልተሰማምና ከእርሱ ጋር መነጋገርን ተዉ። 28ኢየሩሳሌም እስከ ተያዘችበት ቀን ድረስ በግዞት ቤት አደባባይ ተቀመጠ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 38: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ