የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ወንጌል 21

21
1ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ገና ተገለጠላቸው፤ 2እንዲህም ተገለጠ። ስምዖን ጴጥሮስና ዲዲሞስ የሚባለው ቶማስ ከገሊላ ቃና የሆነ ናትናኤልም የዘብዴዎስም ልጆች ከደቀ መዛሙርቱም ሌሎች ሁለት በአንድነት ነበሩ። 3ስምዖን ጴጥሮስ፦ “ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ” አላቸው። እነርሱም፦ “እኛም ከአንተ ጋር እንመጣለን” አሉት። ወጥተውም ወደ ታንኳይቱ ገቡ በዚያችም ሌሊት ምንም እላጠመዱም።
4በነጋም ጊዜ ኢየሱስ በባሕር ዳር ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም። 5ኢየሱስም፦ “ልጆች ሆይ፥ አንዳች የሚበላ አላችሁን?” አላቸው። “የለንም” ብለው መለሱለት። 6እርሱም፦ “መረቡን በታንኳይቱ በስተ ቀኝ ጣሉት ታገኙማላችሁ” አላቸው። ስለዚህ ጣሉት፤ በዚህም ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ ሊጐትቱት አቃታቸው። 7ኢየሱስ ይወደው የነበረውም ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን፦ “ጌታ እኮ ነው” አለው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ጌታ መሆኑን በሰማ ጊዜ ዕራቁቱን ነበረና ልብሱን ታጥቆ ወደ ባሕር ራሱን ጣለ። 8ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር ሁለት መቶ ክንድ ያህል እንጂ እጅግ አልራቁም ነበርና ዓሣ የሞላውን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ።
9ወደ ምድርም በወጡ ጊዜ ፍምና ዓሣ በላዩ ተቀምጦ እንጀራም አዩ። 10ኢየሱስም፦ “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ አምጡ” አላቸው። 11ስምዖን ጴጥሮስም ወደ ጀልባይቱ ገብቶ መቶ አምሳ ሦስት ታላላቅ ዓሦች ሞልቶ የነበረውን መረብ ወደ ምድር ጐተተ፤ ይህንም ያህል ብዙ ሲሆን መረቡ አልተቀደደም። 12ኢየሱስም፦ “ኑ፥ ምሳ ብሉ” አላቸው። ከደቀ መዛሙርቱ አንድ ስንኳ፦ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ሊመረምረው የደፈረ አልነበረም፤ ጌታ መሆኑን አውቀው ነበርና። 13ኢየሱስም መጣና እንጀራ አንሥቶ ሰጣቸው፥ እንዲሁም ዓሣውን። 14ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥላቸው ይህ ሦስተኛው ጊዜ ነበረ።
15ምሳ ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፦ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?” አለው። “አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። “ግልገሎቼን አሰማራ” አለው። 16ደግሞ ሁለተኛ፦ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን?” አለው። “አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። 17“ጠቦቶቼን ጠብቅ” አለው። ሦስተኛ ጊዜ፦ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን?” አለው። ሦስተኛ፦ “ትወደኛለህን?” ስላለው ጴጥሮስ አዘነና፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም፦ “በጎቼን አሰማራ። 18እውነት እውነት እልሃለሁ፥ አንተ ጕልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፥ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል” አለው። 19በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ። ይህንም ብሎ፦ “ተከተለኝ” አለው።
20ጴጥሮስም ዘወር ብሎ ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀ መዝሙር ሲከተለው አየ፤ እርሱም ደግሞ በእራት ጊዜ በደረቱ ተጠግቶ፦ “ጌታ ሆይ፥ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበረ። 21ጴጥሮስም ይህን አይቶ ኢየሱስን፦ “ጌታ ሆይ፥ ይህስ እንዴት ይሆናል?” አለው። 22ሲየሱስም፦ “እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ፥ ምን አግዶህ? አንተ ተከተለኝ” አለው። 23ስለዚህ፦ “ያ ደቀ መዝሙር አይሞትም” የሚለው ይህ ነገር ወደ ወንድሞች ወጣ፤ ነገር ግን ኢየሱስ፦ “እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን አግዶህ?” አለው እንጂ አይሞትም አላለውም።
24ስለ እነዚህም የመሰከረ ይህንንም ጽፎ ያለ ይህ ደቀ መዝሙር ነው፥ ምስክሩም እውነት እንደ ሆነ እናውቃለን።
25ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ