የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢያሱ 1

1
1እንዲህም ሆነ፥ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2ባሪያዬ ሙሴ ሞቶአል፥ አሁንም አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሥታችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር ይህን ዮርዳኖስ ተሻገሩ። 3ለሙሴ እንደ ነገርሁት የእግራችሁ ጫማ የሚረግጠውን ቦታ ሁሉ ለእናንተ ሰጥቼአለሁ። 4ከምድረ በዳው ከዚህም ከሊባኖስ ጀምሮ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ የኬጥያውያን ምድር ሁሉ እስከ ፀሐይ መግቢያ እስክ ታላቁ ባሕር ድረስ ዳርቻችሁ ይሆናል። 5በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፥ ከሙሴ ጋር እንደሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ አልጥልህም፥ አልተውህም። 6ለአባቶቻቸው፦ እሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወርሳለህና ጽና፥ አይዞህ። 7ነገር ግን ጽና፥ እጅግ በርታ፥ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፥ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። 8የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፥ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። 9በምትሄድበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ነውና ጽና፥ አይዞህ፥ አትፍራ፥ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?
10-11ኢያሱም የሕዝቡን አለቆች፦ በሰፈሩ መካከል እለፉ፥ ሕዝቡንም፦ አምላካችሁ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ወደሚሰጣችሁ ምድር እስከ ሦስት ቀን ይህን ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ልትወርሱአት ትገቡባታላችሁና ስንቃችሁን አዘጋጁ ብላችሁ እዘዙአቸው ብሎ አዘዘ።
12አያሱም የሮቤልን ልጆች የጋድንም ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌታ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 13የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ እንዲህ ብሎ ያዘዛችሁን ቃል አስቡ፦ አምላካችሁ እግዚአብሔር ያሳርፋችኋል፥ ይህችንም ምድር ይሰጣችኋል። 14ሚስቶቻችሁና ልጆቻችሁ ከብቶቻችሁም ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ በሰጣችሁ ምድር ይቀመጡ፥ ነገር ግን እናንተ፥ ጽኑዓን ኃያላን ሁሉ፥ ተሰልፋችሁ በወንድሞቻችሁ ፊት ተሻገሩ፥ እርዱአቸውም፥ 15እግዚአብሔር እናንተን እንዳሳረፋችሁ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፍ ድረስ፥ እነርሱም ደግሞ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ፥ ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በፀሐይ መውጫ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ትመለሳላችሁ ትወርሱአትማላችሁ። 16እነርሱም ለኢያሱ እንዲህ ብለው መለሱለት፦ ያዘዝኸንን ነገር ሁሉ እናደርጋለን ወደምትልከንም ስፍራ እንሄዳለን። 17በሁሉም ለሙሴ እንደ ታዘዝን እንዲሁ ለአንተ ደግሞ እንታዘዛለን፥ ብቻ አምላክህ እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር እንደ ነበረ ከአንተ ጋር ይሁን። 18በትእዛዝህ የሚያምፅ ሁሉ የምታዝዘውንም ቃል ሁሉ የማይሰማ፥ እርሱ ይገደል፥ ብቻ ጽና፥ አይዞህ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ