የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢያሱ 18

18
1የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በሴሎ ተሰበሰቡ፥ በዚያም የመገናኛውን ድንኳን ተከሉ፥ ምድሩም ጸጥ ብሎ ተገዛላቸው። 2ከእስራኤልም ልጆች ርስት ያልተካፈሉ ሰባት ነገድ ቀርተው ነበር። 3ኢያሱም የእስራኤልን ልጆች አላቸው፦ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ምድር ትወርሱ ዘንድ እስከ መቼ ለመግባት ቸል ትላላችሁ? 4ከየነገዱ ሁሉ ሦስት ሦስት ሰዎች ምረጡ፥ እኔም እልካቸዋለሁ፥ ተነሥተውም አገሩን ይዞራሉ፥ እንደ ርስታቸውም መጠን ይጽፉታል፥ ወደ እኔም ይመለሳሉ። 5በሰባትም ክፍል ይከፍሉታል፥ ይሁዳ በደቡብ በኩል በዳርቻው ውስጥ ይቀመጣል፥ የዮሴፍ ወገኖች በሰሜን በኩል በዳርቻው ውስጥ ይቀመጣሉ። 6እናንተም ምድሩን በሰባት ክፍል ጻፉት፥ የጻፋችሁትንም ወዲህ አምጡልኝ፥ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ፊት በዚህ ዕጣ አጣጥላችኋለሁ። 7ነገር ግን የእግዚአብሔር ክህነት ርስታቸው ነውና ለሌዋውያን በመካከላችሁ እድል ፈንታ የላቸውም፥ ጋድም ሮቤልም የምናሴም ነገድ እኩሌታ በዮርዳኖስ ማዶ በምሥራቅ በኩል የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ የሰጣቸውን ርስታቸውን ተቀብለዋል።
8ሰዎችም ተነሥተው ሄዱ፥ ኢያሱም ምድሩን ሊጽፉ የሄዱትን፦ ሂዱ፥ ምድሩንም ዞራችሁ ጻፉት፥ ወደ እኔም ተመለሱ፥ በዚህም በሴሎ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ አጣጥላችኋለሁ ብሎ አዘዛቸው። 9ሰዎቹም ሄደው ምድሩን ዞሩ፥ እንደ ከተሞችም በሰባት ክፍል ከፈሉት፥ በመጽሐፍም ጻፉት፥ ኢያሱም ወደ ሰፈረበት ወደ ሴሎ ተመለሱ። 10ኢያሱም በእግዚአብሔር ፊት በሴሎ ዕጣ አጣጣላቸው፥ በዚያም ኢያሱ ለእስራኤል ልጆች እንደ ክፍሎቻቸው ምድሩን ከፈለ።
11የብንያምም ልጆች ነገድ ዕጣ በየወገኖቻቸው ወጣ፥ የዕጣቸውም ዳርቻ በይሁዳ ልጆችና በዮሴፍ ልጆች መካከል ወጣ። 12በሰሜን በኩል ድንበራቸው ከዮርዳኖስ ጀመረ፥ ድንበሩም ወደ ኢያሪኮ ወደ ሰሜን ወገን ወጣ፥ ከዚያም በተራራማው አገር ወደ ምዕራብ ወጣ፥ መውጫውም በቤትአዌን ምድረ በዳ ነበረ። 13ድንበሩም ከዚያ በደቡብ በኩል ቤቴል ወደምትባል ወደ ሎዛ አለፈ፥ ድንበሩም በታችኛው ቤትሖሮን በደቡብ በኩል ባለው ተራራ ወደ አጣሮትአዳር ወረደ። 14ድንበሩም ወደ ምዕራብ ሄደ፥ በቤትሖሮንም ፊት ለፊት ካለው ተራራ ወደ ደቡብ ዞረ፥ መውጫውም ቂርያትይዓሪም በምትባል በይሁዳ ልጆች ከተማ በቂርያትበኣል ነበረ፥ ይህ የምዕራቡ ዳርቻ ነበረ። 15የደቡብም ዳርቻ ከቂርያትይዓሪም መጨረሻ ነበረ፥ ድንበሩም በምዕራቡ በኩል ወደ ነፍቶ ውኃ ምንጭ ወጣ። 16ድንበሩም በሄኖም ልጅ ሸለቆ ፊት ለፊት ወዳለው ተራራ መጨረሻ ወረደ፥ እርሱም በራፋይም ሸለቆ በሰሜን በኩል ነው፥ ወደ ሄኖም ሸለቆ ወደ ኢያቡስ ዳር በደቡብ በኩል ወረደ፥ ወደ ዓይንሮጌልም ወረደ። 17ወደ ሰሜንም አለፈ በቤትሳሚስ ምንጭ ላይ ወጣ፥ በአዱሚም ዐቀበት ፊት ለፊት ወዳለው ወደ ጌሊሎት ደረሰ፥ ወደ ሮቤልም ልጅ ወደ ቦሀን ድንጋይ ወረደ፥ 18በሰሜንም ወገን ወደ ዓረባ አጠገብ አለፈ፥ ወደ ዓረባም ወረደ፥ 19ድንበሩም ወደ ቤትሖግላ ወደ ሰሜን ወገን አለፈ፥ መውጫውም በዮርዳኖስ መጨረሻ በደቡብ በኩል ባለው በጨው ባሕር ልሳን አጠገብ ነበረ፥ ይህ የደቡቡ ዳርቻ ነበረ። 20በምሥራቅም በኩል ድንበሩ ዮርዳኖስ ነበረ። ይህ በዙርያቸው ዳርቻ በየወገኖቻቸው የብንያም ልጆች ርስት ነበረ።
21የብንያምም ልጆች ነገድ ከተሞች በየወገኖቻቸው እነዚህ ነበሩ፥ ኢያሪኮ፥ ቤትሖግላ፥ ዓመቀጺጽ፥ 22ቤትዓረባ፥ ዘማራይም፥ ቤቴል፥ 23-24ዓዊም፥ ፋራ፥ ኤፍራታ፥ ክፊርዓሞናይ፥ ዖፍኒ፥ ጋባ፥ አሥራ ሁለት ከተሞችና መንደሮቻቸው። 25ገባዖን፥ ራማ፥ ብኤሮት፥ 26ምጽጳ፥ ከፊራ፥ አሞቂ፥ 27-28ሬቄም፥ ይርጵኤል፥ ተርአላ፥ ጼላ፥ ኤሌፍ፥ ኢየሩሳሌም የምትባል የኢያቡስ ከትማ፥ ቂርያትጊብዓት፥ አሥራ ሦስት ከተሞችና መንደሮቻቸው። የብንያም ልጆች ርስት በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ