የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሚልክያስ 1

1
1በሚልክያስ እጅ ለእስራኤል የሆነ የእግዚአብሔር ቃል ሸክም ይህ ነው።
2ወድጃችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እናንተ ግን፦ በምን ወደድኸን? ብላችኋል። ዔሳው የያዕቆብ ወንድም አልነበረምን? ይላል እግዚአብሔር ያዕቆብንም ወደድሁ፥ ዔሳውንም ጠላሁ፥ 3ተራሮቹንም በረሃ አደረግኋቸው፥ ርስቱንም ለምድረ በዳ ቀበሮች አሳልፌ ሰጠኋቸው። 4ኤዶምያስ፦ እኛ ፈርሰናል፥ ነገር ግን የፈረሰውን መልሰን እንሠራለን ቢል፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነርሱ ይሠራሉ፥ እኔ ግን አፈርሳለሁ፥ በሰዎችም ዘንድ፦ የበደል ዳርቻና እግዚአብሔር ለዘላለም የተቈጣው ሕዝብ ይባላል። 5ዓይኖቻችሁም ያያሉ፥ እናንተም፦ እግዚአብሔር ከእስራኤል ዳርቻ ወዲያ ታላቅ ይሁን ትላላችሁ።
6እናንተ ስሜን የምታቃልሉ ካህናት ሆይ፥ ልጅ አባቱን፥ ባሪያም ጌታውን ያከብራል፥ እኔስ አባት ከሆንሁ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ ወዴት አለ? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተም፦ ስምህን ያቃለልን በምንድር ነው? ብላችኋል። 7በመሠዊያዬ ላይ ርኩስ እንጀራ ታቀርባላችሁ። እናንተም፦ ያረከስንህ በምንድር ነው? ብላችኋል። የእግዚአብሔር ገበታ የተነቀፈ ነው በማለታችሁ ነው። 8ዕውር መሥዋዕትንም ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን? አንካሳውንና የታመመውን ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን? ያንን ለአለቃህ አቅርብ፥ በውኑ በአንተ ደስ ይለዋልን? ወይስ ፊትህን ይቀበላልን? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 9አሁንም ጸጋን ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔርን ለምኑ፥ ይህ ከእጃችሁ የተሰጠ ሲሆን ከቶ ፊታችሁን ይቀበላልን? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 10በመሠዊያዬ ላይ እሳትን በከንቱ እንዳታቃጥሉ ከእናንተ ዘንድ ደጅ የሚዘጋ ሰው ምነው በተገኘ! በእናንተ ደስ አይለኝም፥ ቍርባንንም ከእጃችሁ አልቀበልም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 11ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፥ በየስፍራውም ለስሜ ዕጣን ያጥናሉ፥ ንጹሕም ቍርባን ያቀርባሉ፥ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 12እናንተ ግን፦ የእግዚአብሔር ገበታ ርኩስ ነው፥ ፍሬውና መብሉም የተናቀ ነው በማለታችሁ አስነቀፋችሁት። 13እናንተ፦ እነሆ፥ ይህ ድካም ነው ብላችሁ ጢቅ አላችሁበት፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ በቅሚያ የያዛችሁትንም አንካሳውንም የታመመውንም አቅርባችኋል፥ እንዲሁ ቍርባንን ታመጣላችሁ፥ በውኑ ከእጃችሁ ይህን ልቀበለውን? ይላል እግዚአብሔር። 14እኔ ታላቅ ንጉሥ ነኝና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ ስሜም በአሕዛብ ዘንድ የተፈራ ነውና በመንጋው ውስጥ ተባት እያለው ለጌታ ተስሎ ነውረኛውን የሚሠዋ ሸንጋይ ሰው ርጉም ይሁን።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ