የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 14

14
1ማኅበሩም ሁሉ ድምፃቸውን አንሥተው ጮኹ፤ ሕዝቡም በዚያ ሌሊት አለቀሱ። 2የእስራኤልም ልጆች ሁሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ፦ በግብፅ ምድር ሳለን ምነው በሞትን ኖሮ! ወይም በዚህ ምድረ በዳ ምነው በሞትን ኖሮ! 3እግዚአብሔርም በሰይፍ እንሞት ዘንድ ወደዚች ምድር ለምን ያገባናል? ሴቶቻችንና ልጆቻችን ምርኮ ይሆናሉ፤ ወደ ግብፅ መመለስ አይሻለንምን? አሉአቸው። 4እርስ በርሳቸውም፦ ኑ፥ አለቃ ሾመን ወደ ግብፅ እንመለስ ተባባሉ። 5ሙሴና አሮንም በእስራኤል ልጆች ጉባኤ ፊት በግምባራቸው ወደቁ። 6ምድርን ከሰለሉት ጋር የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ 7ለእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ፦ ዞረን የሰለልናት ምድር እጅግ መልካም ናት። 8እግዚአብሔርስ ከወደደን ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ወደዚች ምድር ያገባናል እርስዋንም ይሰጠናል። 9ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ ይሆኑልናልና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ ጥላቸው ከላያቸው ተገፍፎአል፥ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ነው፤ አትፍሩአቸው ብለው ተናገሩአቸው። 10ማኅበሩ ሁሉ ግን በድንጋይ ይወግሩአቸው ዘንድ ተማከሩ። የእግዚአብሔርም ክብር ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ተገለጠ። 11እግዚአብሔርም ሙሴን፦ ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል? በፊቱስ ባደረግሁት ተአምራት ሁሉ እስከ መቼ አያምንብኝም? 12ከርስታቸው አጠፋቸው ዘንድ በቸነፈር እመታቸዋለሁ፤ አንተንም ከእነርሱ ለሚበዛና ለሚጠነክር ሕዝብ አደርግሃለሁ አለው። 13ሙሴም እግዚአብሔርን አለው፦ ግብፃውያን ይሰማሉ፤ ይህን ሕዝብ ከመካከላቸው በኃይልህ አውጥተኸዋልና፤ 14ለዚችም ምድር ሰዎች ይናገራሉ። አንተ እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ መካከል እንደ ሆንህ ሰምተዋል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ ፊት ለፊት ተገልጠሃል፥ ደመናህም በላያቸው ቆሞአል፥ በቀንም በደመና ዓምድ፥ በሌሊትም በእሳት ዓምድ በፊታቸው ትሄዳለህ። 15ይህን ሕዝብ እንደ አንድ ሰው ብትገድል ዝናህን የሰሙ አሕዛብ፦ 16እግዚአብሔር ይህን ሕዝብ ወደ ማለላቸው ምድር ያገባቸው ዘንድ አልቻለምና በምድረ በዳ ገደላቸው ብለው ይናገራሉ። 17-18አሁንም፥ እባክህ፦ እግዚአብሔር ታጋሽና ምሕረቱ የበዛ፥ አበሳንና መተላለፍን ይቅር የሚል፥ ኃጢአተኞችንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችን ኃጢአት እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ በልጆች ላይ የሚያመጣ ነው ብለህ እንደ ተናገርህ፥ የጌታ ኃይል ታላቅ ይሁን። 19ይህን ሕዝብ ከግብፅ ምድር ካወጣህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይቅር እንዳልሃቸው፥ እባክህ፥ እንደ ምሕረትህ ብዛት የዚህን ሕዝብ ኃጢአት ይቅር በል። 20እግዚአብሔርም አለ፦ እንደ ቃልህ ይቅር አልሁ፤ 21ነገር ግን እኔ ሕያው ነኝና በእውነት የእግዚአብሔር ክብር ምድርን ሁሉ ይሞላል። 22በግብፅ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግሁትን ተአምራቴንና ክብሬን ያዩ እነዚህ ሰዎች ሁሉ አሥር ጊዜ ስለ ተፈታተኑኝ፥ 23ነገሬንም ስላልሰሙ፥ በእውነት ለአባቶቻቸው የማልሁላቸውን ምድር አያዩም፤ ከእነርሱም የናቀኝ ሰው ሁሉ አያያትም፤ 24ባሪያዬ ካሌብ ግን ሌላ መንፈስ ከእርሱ ጋር ስለ ሆነ ፈጽሞም ስለተከተለኝ እርሱ ወደ ገባባት ምድር አገባዋለሁ፤ ዘሩም ይወርሳታል። 25አማሌቅና ከነዓናዊውም በሸለቆው ውስጥ ተቀምጦአል፤ በነጋው ተመልሳችሁ በኤርትራ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ። 26እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 27የሚያጕረመርምብኝን ይህን ክፉ ሕዝብ እስከ መቼ እታገሠዋለሁ? በእኔ ላይ የሚያጕረመርሙትን የእስራኤልን ልጆች ማጕረምረም ሰማሁ። 28እንዲህ በላቸው፦ እኔ ሕያው ነኝና በጆሮዬ እንደ ተናገራችሁት እንዲሁ በእውነት አደርግባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ 29በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ፤ የተቈጠራችሁ ሁሉ፥ እንደ ቍጥራችሁ ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የሆነ ሁሉ፥ እናንተ ያጕረመረማችሁብኝ፥ 30ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር በእርስዋ አስቀምጣችሁ ዘንድ እጄን ዘርግቼ ወደ ማልሁላችሁ ምድር በእውነት እናንተ አትገቡም። 31ምርኮኛ ይሆናሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን እነርሱን አገባቸዋለሁ፥ እናንተም የናቃችኋትን ምድር ያውቃሉ። 32እናንተ ግን በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ። 33ልጆቻችሁም በምድረ በዳ አርባ ዓመት ይቅበዘበዛሉ፥ በድኖቻችሁም በምድረ በዳ እስኪጠፉ ድረስ ግልሙትናችሁን ይሸከማሉ። 34ምድሪቱን በሰላለችሁባት ቀን ቍጥር፥ አርባ ቀን፥ ስለ አንድ ቀንም አንድ ዓመት፥ ኃጢአታችሁን አርባ ዓመት ትሸከማላችሁ፥ ቍጣዬንም ታውቃላችሁ። 35እኔ እግዚአብሔር፦ በእኔ ላይ በተሰበሰበ በዚህ ክፉ ማኅበር ሁሉ ላይ እንዲህ አደርጋለሁ ብዬ ተናገርሁ፤ በዚህ ምድረ በዳ ያልቃሉ፥ በዚያም ይሞታሉ። 36ምድሪቱንም ሊሰልሉ ሙሴ ልኮአቸው የተመለሱት ሰዎች ክፉ ወሬም ስለ ምድሪቱ እያወሩ በእርሱ ላይ ማኅበሩ ሁሉ እንዲያጕረመርሙ ያደረጉ፥ 37ክፉ ወሬ ያወሩ እነዚያ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት በመቅሠፍት ሞቱ። 38ነገር ግን ምድሪቱን ሊሰልሉ ከሄዱ ሰዎች የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ በሕይወት ተቀመጡ። 39ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ነገረ፥ ሕዝቡም እጅግ አዘኑ። 40በነጋውም ማልደው ተነሡ፥ ወደ ተራራውም ራስ ወጥተው፦ እነሆ፥ መጣን፤ እኛ በድለናልና እግዚአብሔር ወዳለው ስፍራ እንወጣለን አሉ። 41ሙሴም አለ፦ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? አይጠቅማችሁም። 42እግዚአብሔር በእናንተ መካከል አይደለምና በጠላቶቻችሁ ፊት እንዳትወድቁ አትውጡ። 43አማሌቃዊና ከነዓናዊ በፊታችሁ ናቸውና በሰይፍ ትወድቃላችሁ፤ እግዚአብሔርን ከመከተል ተመልሳችኋልና እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር አይሆንም። 44እነርሱ ግን ወደ ተራራው ራስ ሊወጡ ደፈሩ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦትና ሙሴ ከሰፈሩ አልተነሡም። 45በዚያም ተራራ ላይ የተቀመጡ አማሌቃዊና ከነዓናዊ ወረዱ፥ መትተዋቸውም እስከ ሔርማ ድረስ አሳደዱአቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ