ኦሪት ዘኊልቊ 19
19
1እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 2እግዚአብሔር ያዘዘው የሕጉ ትእዛዝ ይህ ነው፤ መልካሚቱን፥ ነውርም የሌለባትን፥ ቀንበርም ያልተጫነባትን ቀይ ጊደር ያመጡልህ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። 3እርስዋንም ለካህኑ ለአልዓዛር ትሰጣላችሁ፥ እርስዋንም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወስዳታል፥ አንድ ሰውም በፊቱ ያርዳታል። 4ካህኑም አልዓዛር ከደምዋ በጣቱ ይወስዳል፥ ከደምዋም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ሰባት ጊዜ ይረጫል። 5ጊደሪቱም በፊቱ ትቃጠላለች፤ ቁርበትዋም ሥጋዋም ደምዋም ፈርስዋም ይቃጠላል። 6ካህኑም የዝግባ እንጨት ሂሶጵም ቀይ ግምጃም ወስዶ ጊደሪቱ በምትቃጠልበት እሳት መካከል ይጥለዋል። 7ካህኑም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል፤ ካህኑም እስከ ማታ ርኩስ ይሆናል። 8ያቃጠላትም ሰው ልብሱን በውኃ ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። 9ንጹሕም ሰው የጊደሪቱን አመድ ያከማቻል ከሰፈሩም ውጭ በንጹሕ ስፍራ ያኖረዋል፤ ርኵሰትም ለሚያነጻ ውኃ ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ይጠበቃል፤ ከኃጢአት ለማንጻት የሚሆን ነው። 10የጊደሪቱንም አመድ ያከማቸ ሰው ልብሱን ያጥባል እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ይህም ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸውም ለሚኖር መጻተኛ ለዘላለም ሥርዓት ይሆናል። 11የሞተውን ሰው በድን የሚነካ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል፤ 12በዚህም ውኃ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ያጠራል፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ነገር ግን በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ባያጠራ ንጹሕ አይሆንም። 13የሞተውን ሰው በድን የነካ ሁለመናውን ባያጠራ የእግዚአብሔርን ማደሪያ ያረክሳል፤ ያ ሰው ከእስራኤል ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ በእርሱም ላይ የሚያነጻ ውኃ አልተረጨምና ርኩስ ይሆናል፤ ርኵሰቱ ገና በእርሱ ላይ ነው። 14ሰው በድንኳን ውስጥ ቢሞት ሕጉ ይህ ነው፤ ወደ ድንኳኑ የሚገባ ሁሉ በድንኳኑም ውስጥ ያለው ሁሉ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል። 15መክደኛው ያልታሰረ የተከፈተ ዕቃ ሁሉ ርኩስ ነው። 16በሜዳም በሰይፍ የተገደለውን ወይም የሞተውን በድን ወይም የሰውን አጥንት ወይም መቃብር የሚነካ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል። 17ከኃጢአት ለማንጻት እንድትሆን ከተቃጠለችው ጊደር አመድ ለርኩሱ ይወስዱለታል፥ በዕቃውም ውስጥ የምንጭ ውኃ ይቀላቀልበታል። 18ንጹሕም ሰው ሂሶጱን ወስዶ በውኃው ውስጥ ያጠልቀዋል፤ በድንኳኑም፥ በዕቃውም ሁሉ፥ በዚያም ባሉ ሰዎች ላይ፥ አጥንቱንም ወይም የተገደለውን ወይም የሞተውን ወይም መቃብሩን በነካው ላይ ይረጨዋል፤ 19ንጹሑም በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን በርኩሱ ላይ ይረጨዋል፤ በሰባተኛውም ቀን ያጠራዋል፤ እርሱም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ በማታም ጊዜ ንጹሕ ይሆናል። 20ሰውም ርኩስ ቢሆን ሁለመናውንም ባይጠራ፥ ያ ሰው የእግዚአብሔርን መቅደስ አርክሶአልና ከጉባኤው መካከል ተለይቶ ይጠፋል፤ በሚያነጻ ውኃ አልተረጨም፤ ርኩስ ነው። 21ይህም የዘላለም ሥርዓት ይሆንላችኋል፤ የሚያነጻውን ውኃ የሚረጭ ሰው ልብሱን ያጥባል፤ የሚያነጻውንም ውኃ የሚነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 22ርኩሱም የሚነካው ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ የሚነካውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኊልቊ 19: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ