ኦሪት ዘኊልቊ 24
24
1በለዓምም እግዚአብሔር እስራኤልን ይባርክ ዘንድ እንዲወድድ ባየ ጊዜ፥ አስቀድሞ ያደርግ የነበረውን አስማት ይሻ ዘንድ አልሄደም፤ ነገር ግን ወደ ምድረ በዳ ፊቱን አቀና። 2በለዓምም ዓይኑን አንሥቶ እስራኤል በየነገዱ ተቀምጦ አየ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዩ መጣ። 3ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ ዓይኖቹ የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤ 4የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል፦ 5ያዕቆብ ሆይ፥ ድንኳኖችህ፥ እስራኤል ሆይ፥ ማደሪያዎችህ ምንኛ ያምራሉ! 6እንደ ሸለቆች፥ በወንዝ ዳር እንዳሉ አትክልቶች፥ እግዚአብሔር እንደ ተከለው እሬት በውኃም ዳር እንዳሉ ዝግባዎች ተዘርግተዋል። 7ከማድጋዎቹ ውኃ ይፈስሳል፥ ዘሩም በብዙ ውኆች ይሆናል፥ ንጉሡም ከአጋግ ይልቅ ከፍ ከፍ ይላል፥ መንግሥቱም ይከበራል። 8እግዚአብሔርም ከግብፅ አውጥቶታል፤ ጕልበቱ አንድ ቀንድ እንዳለው ነው፤ ጠላቶቹን አሕዛብን ይበላል፥ አጥንቶቻቸውንም ይሰባብራል፥ በፍላጾቹም ይወጋቸዋል። 9እንደ አንበሳ ዐርፎ ተኝቶአል፥ እንደ እንስቲቱም አንበሳ ተጋድሞአል፤ ማን ያስነሣዋል? የሚመርቅህ ሁሉ የተመረቀ ይሁን፥ የሚረግምህም ሁሉ የተረገመ ይሁን። 10የባላቅም ቍጣ በበለዓም ላይ ነደደ፤ እጆቹንም አጨበጨበ፤ ባላቅም በለዓምን፦ ጠላቶቼን ትረግም ዘንድ ጠራሁህ፥ እነሆም፥ ሦስት ጊዜ ፈጽመህ መረቅሃቸው፤ አሁንም እንግዲህ ወደ ስፍራህ ሽሽ፤ 11እኔ አከብርህ ዘንድ ወድጄ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን፥ እነሆ፥ ክብርህን ከለከለ አለው። 12-13በለዓምም ባላቅን አለው፦ ባላቅ በቤቱ የሞላውን ብርና ወርቅ ቢሰጠኝ፥ መልካሙን ወይም ክፉውን ከልቤ ለማድረግ እግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም፤ እግዚአብሔር የተናገረውን እርሱን እናገራለሁ ብዬ ወደ እኔ ለላክሃቸው መልእክተኞችህ አልተናገርኋቸውምን? 14አሁንም፥ እነሆ፥ ወደ ሕዝቤ እሄዳለሁ፤ ና፥ ይህ ሕዝብ በኋለኛው ዘመን በሕዝብህ ላይ የሚያደርገውን እነግርሃለሁ። 15ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ ዓይኖቹ የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤ 16የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥ የልዑልንም እውቀት የሚያውቅ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል፦ 17አየዋለሁ፥ አሁን ግን አይደለም፤ እመለከተዋለሁ፥ በቅርብ ግን አይደለም፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፥ ከእስራኤል በትር ይነሣል፥ የሞዓብንም ማዕዘኖች ይመታል፥ የሤትንም ልጆች ያጠፋል። 18ኤዶምያስም ርስቱ ይሆናል፥ ጠላቱ ሴይር ደግሞ ርስቱ ይሆናል፤ እስራኤልም በኃይል ያደርጋል። 19ከያዕቆብም የሚወጣ ገዥ ይሆናል፥ ከከተማውም የቀሩትን ያጠፋል። 20አማሌቅንም አይቶ ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ አማሌቅ የአሕዛብ አለቃ ነበረ፤ ፍጻሜው ግን ወደ ጥፋት ይመጣል። 21ቄናውያንምም አይቶ ምሳሌውን ይምስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ ማደሪያህ የጸና ነው፥ ጎጆህም በአምባ ላይ ተሠርቶአል፤ 22ነገር ግን አሦር እስኪማርክህ ድረስ ቄናዊው ለጥፋት ይሆናል። 23ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ እግዚአብሔር ይህን ሲያደርግ አወይ! ማን በሕይወት ይኖራል? 24ከኪቲም ዳርቻ መርከቦች ይመጣሉ፥ አሦርንም ያስጨንቃሉ፥ ዔቦርንም ያስጨንቃሉ፤ እርሱም ደግሞ ወደ ጥፋት ይመጣል። 25በለዓምም ተነሣ፥ ተመልሶም ወደ ስፍራው ሄደ፤ ባላቅም ደግሞ መንገዱን ሄደ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኊልቊ 24: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ