የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 32

32
1የሮቤልና የጋድ ልጆችም እጅግ ብዙ እንስሶች ነበሩአቸው፤ እነሆም፥ የኢያዜር ምድርና የገለዓድ ምድር ለእንስሶች የተመቸ ስፍራ እንደ ነበረ ባዩ ጊዜ፥ 2የጋድና የሮቤል ልጆች መጥተው ሙሴንና ካሁኑን አልዓዛርን የማኅበሩንም አለቆች እንዲህ ብለው ተናገሩአቸው፦ 3-4እግዚአብሔር በእስራኤል ማኅበር ፊት የመታው ምድር፥ አጣሮት፥ ዲቦን፥ ኢያዜር፥ ነምራ፥ ሐሴቦን፥ ኤልያሊ፥ ሴባማ፥ ናባው፥ ባያን፥ ለእንስሶች የተመቸ ምድር ነው፤ ለእኛም ለባሪያዎችህ እንስሶች አሉን። 5እኛስ በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝተን እንደ ሆነ ይህን ምድር ለባሪያዎችህ ርስት አድርገህ ስጠን፤ ወደ ዮርዳኖስም ማዶ አታሻግረን። 6ሙሴም ለጋድና ለሮቤል ልጆች አላቸው፦ ወንድሞቻችሁ ወደ ጦርነት ሲሄዱ እናንተ በዚህ ትቀመጣላችሁን? 7እግዚአብሔር ወደሚሰጣቸው ምድር እንዳይሻገሩ የእስራኤልን ልጆች ልብ ለምን ታደክማላችሁ? 8ምድሪቱን ይሰልሉ ዘንድ ከቃዴስ በርኔ በሰደድኋቸው ጊዜ አባቶቻችሁ እንዲህ አደረጉ። 9ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ በሄዱ ጊዜ፥ ምድሪቱንም ባዩ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ የእስራኤልን ልጆች ልብ አደከሙ። 10በዚያም ቀን የእግዚአብሔር ቁጣ ነደደ፥ 11-12እርሱም፦ በእውነት እግዚአብሔርን ፈጽመው ከተከተሉ ከእነዚህ ከቄኔዛዊው ከዮፎኔ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር፥ ከግብፅ የወጡት ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት ሰዎች እኔን ፈጽመው አልተከተሉምና ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እሰጥ ዘንድ የማልሁበትን ምድር አያዩም ብሎ ማለ። 13የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ጸና፥ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ያደረገ ትውልድ ሁሉ እስኪጠፋ ድረስ አርባ ዓመት በምድረ በዳ ውስጥ አቅበዘበዛቸው። 14እነሆም፥ የእግዚአብሔርን መዓት በእስራኤል ላይ አብዝታችሁ ትጨምሩ ዘንድ እናንተ የኃጢአተኞች ትውልድ በአባቶቻችሁ ፋንታ ቆማችኋል። 15እርሱን ከመከተል ብትመለሱ እርሱ ሕዝቡን በምድረ በዳ ደግሞ ይተዋል፤ ይህንንም ሕዝብ ሁሉ ታጠፋላችሁ። 16ወደ እርሱም ቀርበው አሉት፦ በዚህ ለእንስሶቻችን በረቶች ለልጆቻችንም ከተሞች እንሠራለን፤ 17እኛ ግን ለጦርነት ተዘጋጅተን ወደ ስፍራቸው እስክናገባቸው ድረስ በእስራኤል ልጆች ፊት እንድሄዳለን፤ በዚህም ምድር ስላሉ ሰዎች ልጆቻችን በተመሸጉ ከተሞች ይቀመጣሉ። 18የእስራኤል ልጆች ሁሉ ርስታቸውን እስኪወርሱ ድረስ ወደ ቤቶቻችን አንመለስም፤ 19ከዮርዳኖስ ወዲህ ወደ ምሥራቅ ርስታችን ደርሶናልና እኛ ከዮርዳኖስ ማዶ ወደዚያ ከእነርሱ ጋር ርስት አንወርስም። 20ሙሴም አላቸው፦ ይህንስ ነገር ብታደርጉ፥ ተዘጋጅታችሁም በእግዚአብሔር ፊት ወደ ሰልፍ ብትሄዱ፥ 21እርሱም ጠላቶቹን ከፊቱ እስኪያሳድድ ድረስ ምድሪቱም በእግዚአብሔር ፊት ድል እስክትሆን ድረስ ከእናንተ ሰው ሁሉ ጋሻ ጦሩን ይዞ በእግዚአብሔር ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገር፥ 22ከዚያ በኋላ ትመለሳላችሁ፥ በእግዚአብሔርም ፊት በእስራኤል ዘንድ ንጹሐን ትሆናላችሁ፤ ይህች ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ርስት ትሆንላችኋለች። 23እናንተ ግን እንዲህ ባታደርጉ፥ እነሆ፥ እግዚአብሔርን ትበድላላችሁ፤ ኃጢአታችሁም እንዲያገኛችሁ እወቁ። 24ለልጆቻችሁ ከተሞች፥ ለበጎቻችሁም በረቶች ሥሩ፤ ከአፋችሁም የወጣውን ነገር አድርጉ። 25የጋድና የሮቤልም ልጆች ሙሴን እንዲህ ብለው ተናገሩት፦ እኛ ባሪያዎችህ ጌታችን እንዳዘዘ እናደርጋለን። 26ልጆቻችን፥ ሚስቶቻችንም፥ መንጎቻችንም፥ እንስሶቻችንም ሁሉ በዚያ በገለዓድ ከተሞች ይሆናሉ፤ 27እኛ ባሪያዎችህ ግን ሁላችን ጋሻ ጦራችንን ይዘን በእግዚአብሔር ፊት ጌታችን እንደ ተናገረ ወደ ጦርነት እንሄዳለን። 28ሙሴም ካህኑን አልዓዛርን የነዌንም ልጅ ኢያሱን የእስራኤልንም ልጆች ነገድ አለቆች ስለ እነርሱ አዘዘ። 29ሙሴም፦ የጋድና የሮቤል ልጆች ሁላቸው ጋሻ ጦራቸውን ይዘው ከእናንተ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገሩ፥ ምድሪቱንም ድል ብትነሡ፥ የገለዓድን ምድር ርስት አድርጋችሁ ትሰጡአቸዋላችሁ። 30ጋሻ ጦራቸውን ይዘው ከእናንተ ጋር ባይሻገሩ ግን በከነዓን ምድር በእናንተ መካከል ርስታቸውን ይወርሳሉ አላቸው። 31የጋድና የሮቤልም ልጆች መልሰው፦ እግዚአብሔር ለእኛ ለባሪያዎችህ እንደ ተናገረ እንዲሁ እናደርጋለን። 32ጋሻ ጦራችንን ይዘን በእግዚአብሔር ፊት ወደ ከነዓን ምድር እንሻገራለን፥ ከዮርዳኖስም ማዶ ከወዲሁ የወረስነው ርስት ይሆንልናል አሉት። 33ሙሴም ለጋድና ለሮቤል ልጆች ለዮሴፍም ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ፥ የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ግዛት፥ ምድሪቱንና በዙሪያዋ ያሉትን ከተሞች ሰጣቸው። 34የጋድም ልጆች ዲቦንን፥ አጣሮትን፥ አሮዔርን፥ 35ዓጥሮትሽፋንን፥ ኢያዜርን፥ ዮግብሃን፥ 36ቤትነምራን፥ ቤትሃራንን የተመሸጉ ከተሞች አድርገው ሠሩ፤ የበጎች በረቶችንም ሠሩ። 37የሮቤልም ልጆች ሐሴቦንን፥ ኤልያሊን፥ 38ቂርያትይምን፥ ስማቸውም የተለወጠውን ናባውን፥ በኣልሜዎንን፥ ሴባማን ሠሩ፤ እነዚህንም የሠሩአቸውን ከተሞች በሌላ ስም ጠሩአቸው። 39የምናሴም ልጅ የማኪር ልጆች ወደ ገለዓድ ሄዱ፥ ወሰዱአትም፥ በእርስዋም የነበሩትን አሞራውያንን አሳደዱ። 40ሙሴም ለምናሴ ልጅ ለማኪር ገለዓድን ሰጠ፤ በእርስዋም ተቀመጠ። 41የምናሴም ልጅ ኢያዕር ሄዶ መንደሮችዋን ወሰደ፥ የኢያዕርም መንደሮች ብሎ ጠራቸው። 42ኖባህም ሄደ ቄናትንም መንደሮችዋንም ወሰደ፥ በስሙም ኖባህ ብሎ ጠራቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ