ኦሪት ዘኊልቊ 36
36
1ከዮሴፍ ልጆች ወገኖች የምናሴ ልጅ የማኪር ልጅ የገለዓድ ልጆች ወገን አለቆች ቀረቡ፥ በሙሴና በእስራኤልም ልጆች አባቶች አለቆች ፊት ተናገሩ፤ 2አሉም፦ ምድሪቱን ለእስራኤል ልጆች ርስት አድርገህ በዕጣ ከፍለህ ትሰጣቸው ዘንድ እግዚአብሔር አንተን ጌታችንን አዘዘህ፤ እግዚአብሔርም የወንድማችንን የሰለጰዓድን ርስት ለሴቶች ልጆቹ ትሰጥ ዘንድ አንተን ጌታችንን አዘዘ። 3ከሌላም ከእስራኤል ልጆች ነገድ ባል ቢያገቡ፥ ርስታቸው ከአባቶቻችን ርስት ይነቀላል፥ እነርሱም ለሚሆኑበት ለሌላው ነገድ ርስት ይጨመራል፤ እንደዚህም የርስታችን ዕጣ ይጐድላል። 4ለእስራኤልም ልጆች ኢዮቤልዩ በመጣ ጊዜ ርስታቸው ለሚሆኑበት ነገድ ርስት ይጨመራል፤ እነዚህም ርስታቸው ከአባቶቻችን ነገድ ርስት የጐድላል። 5ሙሴም የእስራኤልን ልጆች እንደ እግዚአብሔር ቃል እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ የዮሴፍ ልጆች ነገድ በእውነት ተናገሩ። 6እግዚአብሔር ስለ ሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤ የወደዱትን ያግቡ፤ ነገር ግን ከአባታቸው ነገድ ብቻ ያግቡ። 7እንደዚህም የእስራኤል ልጆች ርስት ከነገድ ወደ ነገድ ምንም አይተላለፍ፤ ከእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ ወደ አባቶቹ ነገድ ርስት ይጠጋ። 8ከእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ ሰው የአባቶቹን ርስት ይወርስ ዘንድ፥ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ ርስት ያላት ሴት ልጅ ሁሉ ከአባትዋ ነገድ ባል ታግባ። 9እንደዚህም ከአንድ ነገድ ወደ ሌላ ነገድ ምንም ርስት አይተላለፍ ከእስራኤልም ልጆች ነገድ እያንዳንዱ ወደ ርስቱ ይጠጋ። 10እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች አደረጉ። 11የሰለጰዓድ ልጆች ማህለህ፥ ቲርጻ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ኑዓ ከአባታቸው ወንድሞች ልጆች ጋር ተጋቡ። 12ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ልጆች ወገኖች ባሎቻቸውን አገቡ፥ ርስታቸውም በአባታቸው ነገድ ጸና። 13እግዚአብሔር በሙሴ እጅ የእስራኤልን ልጆች በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ሜዳ ያዘዛቸው ትእዛዝና ፍርድ እነዚህ ናቸው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኊልቊ 36: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ