የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ራእይ 12

12
1ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች። 2እርስዋም ፀንሳ ነበር፥ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጭንቃ ጮኸች። 3ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆም ታላቅ ቀይ ዘንዶ፤ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ነበሩት በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፥ 4ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው። ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ። 5አሕዛብንም፥ ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ። 6ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሀ ሸሸች።
7በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም፥ 8ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። 9ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። 10ታላቅም ድምፅ በሰማይ ሰማሁ እንዲህ ሲል፦
አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም
ሥልጣን ሆነ፥ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው
የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።
11እነርሱም ከበጉ ደም የተነሣ ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ
ድል ነሡት፥ ነፍሳቸውንም እስከ ሞት ድረስ አልወደዱም።
12ስለዚህ፥ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፥ ደስ
ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፥ ዲያብሎስ ጥቂት
ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቍጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።
13ዘንዶውም ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት። 14ከእባቡም ፊት ርቃ አንድ ዘመን፥ ዘመናትም፥ የዘመንም እኵሌታ ወደ ምትመገብበት ወደ ስፍራዋ ወደ በረሀ እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የታላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት። 15እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውኃ ከአፉ በስተ ኋላዋ አፈሰሰ። 16ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፥ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው። 17ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ፤ 18በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ