የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 8

8
1ሳውልም በእስጢፋኖስ መገደል ተስማምቶ ነበር።
የአማኞች መሰደድና መበተን
በዚያ ቀን በኢየሩሳሌም በነበረችው ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ተነሣ፤ ከሐዋርያትም በስተቀር አማኞች በሙሉ በይሁዳና በሰማርያ አውራጃዎች ሁሉ ተበተኑ፤ 2በመንፈሳዊ ነገር የተጉ ሰዎችም እስጢፋኖስን ቀበሩት፤ ደግሞም እጅግ አለቀሱለት። 3ሳውል ግን ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ታጥቆ ተነሣ፤ ከቤት ወደ ቤት በመግባትም ወንዶችንና ሴቶችን ጐትቶ እያወጣ ወህኒ ቤት ያስገባቸው ነበር።
ፊልጶስ በሰማርያ
4የተበተኑትም በሄዱበት ሁሉ ቃሉን ሰበኩ፤ 5ፊልጶስም ወደ አንዲት የሰማርያ ከተማ ወርዶ ክርስቶስን#8፥5 ወይም መሲሕ ሰበከላቸው። 6ብዙ ሕዝብም ፊልጶስ የተናገረውን ሲሰሙና ያደረገውንም ታምራዊ ምልክቶች ሲያዩ፣ አንድ ልብ ሆነው ያዳምጡት ነበር። 7ርኩሳን#8፥7 ወይም ክፉ መናፍስትም እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ወጡ፤ ብዙ ሽባዎችና ዐንካሶችም ተፈወሱ፤ 8ከዚህ የተነሣም በከተማዪቱ ታላቅ ደስታ ሆነ።
ጠንቋዩ ሲሞን
9ነገር ግን ከዚህ ቀደም ሲል በከተማዪቱ ውስጥ እየጠነቈለ የሰማርያን ሰዎች ሁሉ ያስገረመ፣ ሲሞን የሚሉት አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ራሱን እንደ ታላቅ ሰው ይቈጥር ነበር። 10ከታናሽ እስከ ታላቅ ያለው ሰው ሁሉ፣ “ይህ ሰው ‘ታላቁ ኀይል’ በመባል የሚታወቀው መለኮታዊ ኀይል ነው” በማለት ከልብ ያዳምጡት ነበር፤ 11ከብዙ ጊዜ ጀምሮ በጥንቈላ ሥራው ስላስገረማቸውም ትኵረት ሰጥተው ይከተሉት ነበር። 12ነገር ግን ፊልጶስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም የሰበከላቸውን አምነው በመቀበላቸው ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ፤ 13ራሱ ሲሞን እንኳ ሳይቀር አምኖ ተጠመቀ፤ ፊልጶስንም ተከትሎ ሄደ፤ የሚደረገውን ምልክትና ታላቅ ታምራት አይቶም ተገረመ።
14በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል መቀበላቸውን በሰሙ ጊዜ፣ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ እነርሱ ላኳቸው። 15እነርሱም ሰማርያ በደረሱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ለሰማርያ ሰዎች ጸለዩላቸው፤ 16ምክንያቱም በዚያን ጊዜ በጌታ ኢየሱስ ስም ተጠምቀው ነበር እንጂ ገና መንፈስ ቅዱስ በአንዳቸውም ላይ አልወረደም ነበር። 17ስለዚህ ጴጥሮስና ዮሐንስ እጃቸውን ጫኑባቸው፤ እነርሱም መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።
18ሲሞንም ሐዋርያት እጃቸውን በሚጭኑበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጥ አይቶ፣ ገንዘብ አመጣላቸውና እንዲህ አላቸው፤ 19“እጄን የምጭንበት ሰው ሁሉ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበል ይህን ሥልጣን ለእኔም ስጡኝ።”
20ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፤ “የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ ለመግዛት አስበሃልና፣ አንተም ገንዘብህም አብራችሁ ጥፉ! 21ልብህ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ስላልሆነ፣ አንተ በዚህ አገልግሎት ድርሻ ወይም ዕድል ፈንታ የለህም። 22አሁንም ስለዚህ ክፋትህ ንስሓ ግባ፤ ወደ ጌታም ጸልይ፤ ምናልባት ይህን የልብህን ሐሳብ ይቅር ይልህ ይሆናል፤ 23ምክንያቱም በመራራነት ተሞልተህ፣ በዐመፅ ሰንሰለት ተይዘህ አይሃለሁና።”
24ሲሞንም መልሶ፣ “ከተናገራችሁት ምንም ነገር እንዳይደርስብኝ ጌታን ለምኑልኝ” አላቸው።
25ጴጥሮስና ዮሐንስም የጌታን ቃል ከመሰከሩና ገልጠው ከተናገሩ በኋላ፣ በብዙ የሰማርያ መንደሮች ወንጌልን እየሰበኩ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ
26የጌታም መልአክ ፊልጶስን፣ “ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚያወርደው በምድረ በዳው መንገድ ሂድ” አለው፤ 27እርሱም ተነሥቶ ሄደ። እነሆ፤ የኢትዮጵያ ንግሥት የህንደኬ ባለሟልና የሀብት ንብረቷ ሁሉ አዛዥ የሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አገኘ። ይህም ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር። 28ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብብ ነበር። 29መንፈስም ፊልጶስን፣ “ሂድ፤ ወደዚህ ሠረገላ ቅረብ” አለው።
30ፊልጶስም ፈጥኖ ወደ ሠረገላው ሄደ፤ ጃንደረባውም የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብብ ሰምቶ፣ “ለመሆኑ፣ የምታነብበውን ታስተውለዋለህን?” አለው።
31ጃንደረባውም፣ “የሚያስረዳኝ ሰው ሳይኖር እንዴት አድርጌ አስተውላለሁ” አለው፤ እርሱም ወደ ሠረገላው ወጥቶ አብሮት እንዲቀመጥ ፊልጶስን ለመነው።
32ጃንደረባው ያነብብ የነበረው የመጽሐፍ ክፍል ይህ ነበር፤
“እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤
የበግ ጠቦት በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል፣
እንዲሁ አፉን አልከፈተም።
33ራሱን በማዋረዱም ፍትሕን ተነፈገ፤
ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና፣
ስለ ትውልዱ ማን ሊናገር ይችላል?”
34ጃንደረባውም መልሶ ፊልጶስን፣ “ነቢዩ ይህን የሚናገረው ስለ ማን ነው? ስለ ራሱ ነው ወይስ ስለ ሌላ ሰው? እባክህ ንገረኝ” አለው። 35ፊልጶስም አፉን ከፈተ፤ ከዚሁም መጽሐፍ ክፍል ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌል ሰበከለት።
36በመጓዝ ላይ ሳሉም ውሃ ካለበት ስፍራ ደረሱ፤ ጃንደረባውም፣ “እነሆ፤ ውሃ እዚህ አለ፤ ታዲያ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” አለው።
37ፊልጶስም፣ “በፍጹም ልብህ ካመንህ መጠመቅ ትችላለህ” አለው።
ጃንደረባውም፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ” ሲል መለሰለት፤#8፥37 አንዳንድ የጥንት ቅጆች ይህ ጥቅስ የላቸውም። 38ሠረገላውም እንዲቆም አዘዘ። ከዚያም ሁለቱ አብረው ወደ ውሃው ወረዱ፤ ፊልጶስም ጃንደረባውን አጠመቀው። 39ከውሃውም በወጡ ጊዜ፣ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጥቆ ወሰደው፤ ጃንደረባውም ከዚህ በኋላ አላየውም፤ ሆኖም ደስ እያለው ጕዞውን ቀጠለ። 40ከዚያ በኋላ ግን ፊልጶስ በአዛጦን ታየ፤ ቂሳርያም እስኪደርስ ድረስ በሚያልፍባቸው ከተሞች ሁሉ ወንጌልን ይሰብክ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ