የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፍጥረት 48

48
ምናሴና ኤፍሬም
1ከጥቂት ጊዜ በኋላም፣ “አባትህ ታሟል” ተብሎ ለዮሴፍ ስለ ተነገረው ሁለቱን ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ሄደ። 2ለያዕቆብ፣ “ልጅህ ዮሴፍ ወደ አንተ መጥቷል” ተብሎ በተነገረው ጊዜ፣ እስራኤል ተበረታትቶ ዐልጋው ላይ ተቀመጠ።
3ያዕቆብም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ሁሉን የሚችል አምላክ#48፥3 ዕብራይስጡ ኤልሻዳይ ይላል። በከነዓን ምድር ሎዛ በምትባል ቦታ ተገለጠልኝ፤ ባረከኝም፤ 4እንዲህም አለኝ፤ ‘ፍሬያማ አደርግሃለሁ፣ ይህችንም ምድር ከአንተ በኋላ ለሚነሡ ዘሮችህ የዘላለም ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ።’
5“ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት በግብፅ የወለድሃቸው ሁለቱ ልጆችህ ከእንግዲህ የእኔ ልጆች ሆነው ይቈጠራሉ፤ ሮቤልና ስምዖን ልጆቼ እንደ ሆኑ ሁሉ፣ ኤፍሬምና ምናሴም ልጆቼ ይሆናሉ። 6ከእነርሱ በኋላ የሚወለዱልህ ልጆች ግን፣ የአንተ ይሁኑ፤ በርስት ድልድላቸው ግን በወንድሞቻቸው ስም ይቈጠራሉ። 7ከሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ መልስ ኤፍራታ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረኝ፣ እናትህ ራሔል በከነዓን ምድር ሞታብኝ ዐዘንሁ። እኔም ወደ ኤፍራታ ማለት ወደ ቤተ ልሔም በሚወስደው መንገድ ዳር ቀበርኋት።”
8እስራኤልም የዮሴፍን ልጆች ባየ ጊዜ፣ “እነዚህ እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀ፤
9ዮሴፍም፣ “እነዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የሰጠኝ ልጆች ናቸው” ብሎ ለአባቱ መለሰለት፤ እስራኤልም፣ “አቅርባቸውና ልመርቃቸው” አለ።
10በዚህ ጊዜ እስራኤል ዐይኖቹ በእርጅና ምክንያት በመድከማቸው አጥርቶ ማየት ይሳነው ነበር፤ ስለዚህ ዮሴፍ ልጆቹን አባቱ ዘንድ አቀረባቸው፤ አባቱም ስሞ ዐቀፋቸው።
11እስራኤልም ዮሴፍን፣ “ዐይንህን እንደ ገና አያለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ግን ልጆችህን ጭምር ለማየት አበቃኝ” አለው።
12ዮሴፍም ልጆቹን ከእስራኤል ጕልበት ፈቀቅ በማድረግ አጐንብሶ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ። 13ከዚያም ዮሴፍ ሁለቱን ልጆቹን ይዞ ኤፍሬምን ከራሱ በስተ ቀኝ፣ ከእስራኤል በስተ ግራ፣ ምናሴን ደግሞ ከራሱ በስተ ግራ፣ ከእስራኤል በስተ ቀኝ በኩል አቀረባቸው። 14እስራኤል ግን ቀኝ እጁን በታናሹ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረ፤ ግራ እጁንም በቀኝ እጁ ላይ አስተላልፎ በበኵሩ በምናሴ ራስ ላይ አኖረ።
15ከዚህ በኋላ ዮሴፍን ባረከ፤ እንዲህም አለው፤
“አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ
የተመላለሱት እግዚአብሔር (ኤሎሂም)
ለእኔም እስከ ዛሬ ድረስ
በዘመኔ ሁሉ እረኛ የሆነኝ አምላክ (ኤሎሂም)
16ከጕዳትም ሁሉ የታደገኝ መልአክ፣
እርሱ እነዚህን ልጆች ይባርክ፤
እነርሱም በስሜ፣
በአባቶቼ በአብርሃምና
በይስሐቅ ስም ይጠሩ፤
በምድር ላይ እጅግ ይብዙ።”
17ዮሴፍ፣ አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ማድረጉን ሲያይ ተከፋ፤ ከኤፍሬም ራስ ላይ አንሥቶ በምናሴ ራስ ላይ ለማኖር የአባቱን እጅ ያዘ፤ 18ዮሴፍም፣ “አባቴ ሆይ፤ እንዲህ አይደለም፤ በኵሩ ይህኛው ስለሆነ፣ ቀኝ እጅህን እርሱ ራስ ላይ አድርግ” አለው።
19አባቱ ግን፣ “ዐውቃለሁ፤ ልጄ ዐውቃለሁ፤ እርሱም እኮ ሕዝብ ይሆናል፤ ታላቅም ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ታናሽ ወንድሙ ከእርሱ ይበልጣል፤ ዘሮቹም ታላቅ ሕዝቦች ይሆናሉ” ብሎ እንቢ አለው። 20በዚያን ዕለት ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤
“በአንተ ስም እስራኤል እንዲህ ብሎ ይመርቃል፤
‘እግዚአብሔር (ኤሎሂም) እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርጋችሁ።’ ”
በዚህ ሁኔታም ኤፍሬምን ከምናሴ አስቀደመው።
21ከዚህ በኋላ እስራኤል ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “እኔ የምሞትበት ጊዜ ተቃርቧል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ወደ አባቶቻችሁም ምድር መልሶ ያገባችኋል። 22እነሆ በሰይፌና በቀስቴ ከአሞራውያን እጅ የወሰድኳትን ዐምባ ከወንድሞችህ ድርሻ አብልጬ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ።”#48፥22 ወይም ከወንድሞችህ ድርሻ አብልጬ ለአንተ አንድ ክፍል እሰጥሃለሁ

Currently Selected:

ዘፍጥረት 48: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ