1 ቆሮንቶስ 9:19-23
1 ቆሮንቶስ 9:19-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እኔ ከሁሉ ይልቅ ነጻ ስሆን ብዙዎችን ወደ ሃይማኖት እሰበስባቸው ዘንድ እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛሁ። አይሁድን እጠቅማቸው ዘንድ ለአይሁድ እንደ አይሁዳዊ ሆንሁላቸው፤ ከኦሪት በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ እኔ ራሴ ከኦሪት በታች ሳልሆን ከኦሪት በታች ላሉት ከኦሪት በታች እንዳለ ሰው ሆንሁላቸው። የእግዚአብሔርን ሕግ የዘነጋሁ ሳልሆን፥ በክርስቶስ ሕግም ሳለሁ ሕግ የሌላቸውን እጠቅማቸው ዘንድ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደሌለው ሆንሁላቸው። ደካሞችንም እጠቅማቸው ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁላቸው፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶቹን አድን ዘንድ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ። በወንጌልም ትምህርት አንድነት ይኖረኝ ዘንድ ስለ ወንጌል ትምህርት ሁሉን አደርጋለሁ።
1 ቆሮንቶስ 9:19-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እኔ ነጻ ሰው ነኝ፤ የማንም ባሪያ አይደለሁም፤ ነገር ግን ብዙዎችን እመልስ ዘንድ ራሴን ለሰው ሁሉ ባሪያ አደርጋለሁ። አይሁድን እመልስ ዘንድ ከአይሁድ ጋራ እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፣ ከሕግ በታች ያሉትን እመልስ ዘንድ ከሕግ በታች እንዳሉት ሆንሁ። እኔ ራሴ ከእግዚአብሔር ሕግ ነጻ ያልሆንሁና፣ ለክርስቶስ ሕግ የምገዛ ብሆንም፣ ሕግ የሌላቸውን እመልስ ዘንድ፣ ሕግ እንደሌለው ሰው ሆንሁ። ደካሞችን እመልስ ዘንድ፣ ከደካሞች ጋራ እንደ ደካማ ሆንሁ። በሚቻለኝ ሁሉ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፣ ከሁሉም ጋራ ሁሉን ነገር ሆንሁ። ይህን ሁሉ የማደርገው፣ ከወንጌል በረከት እካፈል ዘንድ፣ ስለ ወንጌል ብዬ ነው።
1 ቆሮንቶስ 9:19-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከሰው ሁሉ አርነት የወጣሁ ስሆን የሚበልጡትን እንድጠቅም እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛለሁ። አይሁድንም እጠቅም ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ ከሕግ በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ፥ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፥ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንሁ፤ ሕግ የሌላቸውን እጠቅም ዘንድ፥ ያለ እግዚአብሔር ህግ ሳልኖር ነገር ግን በክርስቶስ ሕግ በታች ሳለሁ፥ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደ ሌለኝ ሆንሁ፤ ደካሞችን እጠቅም ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፥ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ። በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ።
1 ቆሮንቶስ 9:19-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እኔ የማንም ባሪያ ሳልሆን ነጻ ሰው ነኝ፤ ይሁን እንጂ በተቻለኝ መጠን ብዙዎቹን በማዳን ለመጥቀም ብዬ የሁሉም ባሪያ ሆኜአለሁ። ከአይሁድ ጋር ስሆን አይሁድን ለማዳን እንደ አይሁዳዊ ሆንኩ፤ እኔ ከሕግ በታች ባልሆንም እንኳ ከሕግ በታች ያሉትን ለማዳን ስል ከሕግ በታች እንዳሉት ሰዎች ሆንኩ። እኔ የእግዚአብሔር ሕግ ያለኝና ከክርስቶስ ሕግ ሥር ብሆንም እንኳ ሕግ የሌላቸውን አሕዛብ ለማዳን ስል ሕግ እንደሌለው ሰው ሆንኩ። በእምነት ደካሞች የሆኑትን ለማዳን ስል እንደ ደካሞች ደካማ ሆንኩ፤ በተቻለ መጠን ጥቂቶችን ለማዳን ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር ሆንኩ። ይህን ሁሉ ማድረጌ የወንጌልን በረከት ለመካፈል ስለ ወንጌል ብዬ ነው።
1 ቆሮንቶስ 9:19-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከሰው ሁሉ ነጻ የወጣሁ ስሆን፥ ብዙዎችን እንድጠቅም እንደ ባርያ ራሴን ለሁሉ አስገዛሁ። አይሁድንም ለመጥቀም ስል ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ ከሕግ በታች ያሉትን መጥቀም እንድችል፥ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፥ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንኩ። ሕግ የሌላቸውን ለመጠቅም ስል፥ የእግዚአብሔር ህግ ሳይኖረኝ ቀርቶ ሳይሆን በክርስቶስ ሕግ ስር ሳለሁ፥ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደሌለኝ ሆንኩ። ደካሞችን መጥቀም እንድችል ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንኩ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን ማዳን እንድችል፥ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ። በወንጌልም ተካፋይ እንድሆን፥ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ።