መክብብ 5:1-7 - ሁሉንም ስሪቶች ያወዳድሩ

መክብብ 5:1-7 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)

ወደ እግዚአብሔር ቤት ስትሄድ እግርህን ጠብቅ። ለመስማት መቅረብ የሞኞችን መሥዋዕት ከማቅረብ ይበልጣል፤ እነርሱ ክፉ እንደሚሠሩ አያውቁምና። በአፍህ አትፍጠን፤ በአምላክም ፊት ማንኛውንም ነገር ለመናገር፣ በልብህ አትቸኵል፤ አምላክ በሰማይ፣ አንተ ደግሞ በምድር ነህ፤ ስለዚህ ቃልህ ጥቂት ይሁን። በሥራ ብዛት ሕልም እንደሚታይ፣ ብዙ ቃል ባለበትም የሞኝ ንግግር ይገለጣል። ለአምላክ ስእለትን በተሳልህ ጊዜ ለመፈጸም አትዘግይ፤ በሞኞች ደስ አይለውምና፤ ስእለትህን ፈጽም። ስእለት ተስሎ ካለመፈጸም፣ አለመሳል ይሻላል። አንደበትህ ወደ ኀጢአት እንዲመራህ አትፍቀድ፤ ለቤተ መቅደስ መልእክተኛም፣ “የተሳልሁት በስሕተት ነበር” አትበል። አምላክ በተናገርኸው ተቈጥቶ የእጅህን ሥራ ለምን ያጥፋ? ብዙ ሕልምና ብዙ ቃል ከንቱ ነው፤ ስለዚህ አምላክን ፍራ።

መክብብ 5:1-7 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

ወደ እግዚአብሔር ቤት በምትገባበት ጊዜ ለአረማመድህ ጥንቃቄ አድርግ፤ እዚያ ሄዶ ደጉን ከክፉ ለይተው የማያውቁ ሞኞች ሰዎች እንደሚያደርጉት መሥዋዕት ከማቅረብ ይልቅ የምክር ቃላትን ለመስማት ዝግጁ ሆኖ መገኘት ይበልጣል። ከመናገርህ በፊት አስብ፤ ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ለመስጠት በችኰላ ስእለት አታድርግ፤ እግዚአብሔር በሰማይ አንተ ግን በምድር መሆንህን በማሰብ የምትናገረው ቃል የተመጠነ ይሁን። ስለ አንድ ነገር ብታስብ ስለ እርሱ ታልማለህ፤ ብዙ ከመናገር የተነሣ ትሳሳታለህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በሞኞች አይደሰትም፤ ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ለመስጠት በተሳልክ ጊዜ ወዲያውኑ የተሳልከውን ለመፈጸም ዝግጁ ሁን፤ ተስለህ የማትፈጽመው ከሆነ ግን ቀድሞውንም ባትሳል የተሻለ ነው። ወደ ኃጢአት እንዳይመራህ ለአንደበትህ ከገደብ ያለፈ ነጻነት አትስጠው፤ በዚህ ዐይነት “ይህን የተናገርኩት ሳላውቅ ነው” ብለህ በእግዚአብሔር አገልጋይ ፊት ይቅርታ ከመጠየቅ ትድናለህ፤ አለበለዚያ ግን የደከምክበትን ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቊጣ በገዛ እጅህ እንደ መጋበዝ ይሆንብሃል። ብዙ ሕልምና ብዙ ልፍለፋ ከንቱ ነው፤ ከዚህስ ይልቅ እግዚአብሔርን ፍራ።

መክብብ 5:1-7 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))

ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤት በም​ት​ሄ​ድ​በት ጊዜ እግ​ር​ህን ጠብቅ፤ የጠ​ቢ​ባ​ን​ንም ትም​ህ​ርት ለመ​ስ​ማት ቅረብ፤ ዳግ​መ​ኛም ከሰ​ነ​ፎች ስጦታ መሥ​ዋ​ዕት አድ​ር​ገህ ከመ​ቀ​በል ተጠ​በቅ፤ እነ​ርሱ መል​ካም ለመ​ሥ​ራት ዐዋ​ቂ​ዎች አይ​ደ​ሉ​ምና። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በሰ​ማይ፥ አን​ተም በም​ድር ነህና በአ​ፍህ አት​ፍ​ጠን፥ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ፊት ቃልን ይና​ገር ዘንድ ልብህ አይ​ቸ​ኩል፤ ስለ​ዚ​ህም ቃልህ ጥቂት ይሁን። ሕልም በብዙ መከራ፥ እን​ዲ​ሁም የሰ​ነፍ ቃል በብዙ ነገር ይመ​ጣ​ልና። ፈቃዱ አይ​ደ​ለ​ምና ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ስእ​ለት በተ​ሳ​ልህ ጊዜ ትፈ​ጽ​መው ዘንድ አት​ዘ​ግይ፤ አንተ ግን እንደ ተሳ​ልህ ስእ​ለ​ት​ህን ስጥ። ተስ​ለህ የማ​ት​ፈ​ጽም ከሆነ ባት​ሳል ይሻ​ላል። ለሥ​ጋህ በደል አፍ​ህን አት​ስጥ፥ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ፊት፥ “ባለ​ማ​ወቅ ነው” አት​በል፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ስለ ቃልህ እን​ዳ​ይ​ቈጣ፥ የእ​ጅ​ህ​ንም ሥራ እን​ዳ​ያ​ጠ​ፋ​ብህ፤ ብዙ ሕልም፥ እን​ዲሁ ደግሞ ብዙ ቃል ከንቱ ነውና፤ አንተ ግን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ፈጽ​መህ ፍራ።

መክብብ 5:1-7 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))

ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባህ ጊዜ እግርህን ጠብቅ፥ ለመስማት መቅረብ ከሰነፎች መሥዋዕት ይበልጣልና፥ እነርሱም ክፉ እንዲያደርጉ አያውቁምና። እግዚአብሔር በሰማይ፥ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠን፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኵል፥ ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ትሁን። ሕልም በሥራ ብዛት ይታያል፥ እንዲሁም የሰነፍ ድምፅ በቃሉ ብዛት ይሰማል። ሰነፎች ደስ አያሰኙትምና ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ ትፈጽመው ዘንድ አትዘግይ፥ የተሳልኸውን ፈጽመው። ተስለህ የማትፈጽም ብትሆን ባትሳል ይሻላል። ሥጋህን በኃጢአት እንዳያስተው ለአፍህ አርነት አትስጥ፥ በመልአክም ፊት፦ ስሕተት ነበረ አትበል፥ እግዚአብሔር በቃልህ ይቈጣ ዘንድ የእጅህንም ሥራ ያጠፋ ዘንድ ስለምን ትሻለህ? ብዙ ሕልም ባለበት ዘንድ፥ እንዲሁም ደግሞ ብዙ ቃል ባለበት ስፍራ በዚያ ብዙ ከንቱ ነገር አለ፥ አንተ ግን እግዚአብሔርን ፍራ።

መክብብ 5:1-7 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))

እግዚአብሔር በሰማይ፥ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትቸኩል፥ ልብህም በእግዚአብሔር ፊት ቃልን ለመናገር አይቸኩል፥ ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ትሁን። ሕልም በሥራ ብዛት ይታያል፥ እንዲሁም የአላዋቂም ድምፅ በቃሉ ብዛት ይሰማል። አላዋቂዎች ደስ አያሰኙትምና ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ ለመፈጸም አትዘግይ፥ የተሳልኸውን ፈጽመው። ተስለህ ካለመፈጸም ባትሳል ይሻላል። አፍህ ወደ ኃጢአት እንዲወስድህ አትፍቀድለት፥ በመልአክም ፊት፦ ስሕተት ነበረ አትበል፥ እግዚአብሔር በቃልህ ለምን ይቈጣ? ለምንስ የእጅህንም ሥራ ያጥፋ? ብዙ ሕልም ባለበት፥ እንዲሁም ብዙ ቃል ባለበት፥ ብዙ ከንቱ ነገር አለ፥ አንተ ግን እግዚአብሔርን ፍራ። ከፍ ካለው ባለ ሥልጣን በላይ ሌላ ከፍ ያለ ይመለከታልና፥ ከእነርሱም በላይ ደግሞ ሌሎች ከፍ ይላሉና በአገሩ ድሆች ሲገፉ፥ ፍርድና ጽድቅም ሲነጠቅ ባየህ ጊዜ በዚህ ነገር አትደነቅ።