ኤፌሶን 2:1-5
ኤፌሶን 2:1-5 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እናንተም በኀጢአታችሁ ምውታን ሆናችሁ ነበር። ይኸውም ቀድሞ በዚህ ዓለም ሥርዐት፥ አሁን በከሓድያን ልጆች የሚበረታታባቸውና፥ በነፋስ አምሳል የሚገዛቸው አለቃ እንደ ነበረው ፈቃድ ጸንታችሁ የነበራችሁበት ነው። እኛ ሁላችን ቀድሞ እንደ ሥጋችን ምኞት ኖርን፤ የሥጋችንንም ፈቃድና ያሰብነውን አደረግን፤ እንደ ሌሎች ኃጥአንም ሁሉ የጥፋት ልጆች ሆንን። እግዚአብሔር ግን በምሕረቱ ባለጸግነትና በወደደን በፍቅሩ ብዛት፥ በኃጢአታችን የሞትን ሳለን በክርስቶስ ሕይወትን ሰጠን፤ በጸጋውም ዳንን።
ኤፌሶን 2:1-5 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እናንተም በበደላችሁና በኀጢአታችሁ ምክንያት ሙታን ነበራችሁ፤ በዚህም፣ የዓለምን ክፉ መንገድ ተከትላችሁ፣ በአየር ላይ ላሉት መንፈሳውያን ኀይላት ገዥ ለሆነውና አሁንም ለእግዚአብሔር በማይታዘዙት ሰዎች ላይ ለሚሠራው መንፈስ እየታዘዛችሁ ትኖሩ ነበር። እኛ ሁላችን በአንድ ወቅት የሥጋችንን ምኞት እያረካን፣ መንገዱንም እየተከተልን በመካከላቸው እንኖር ነበር፤ እንደ ሌሎቹም የቍጣ ልጆች ነበርን። ነገር ግን በምሕረቱ ባለጠጋ የሆነ እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ፣ በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለ፣ በክርስቶስ ሕያዋን አደረገን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው።
ኤፌሶን 2:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥
ኤፌሶን 2:1-5 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እናንተ በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ምክንያት በመንፈሳዊ ኑሮአችሁ የሞታችሁ ነበራችሁ፤ በዚያን ጊዜ የዚህን ዓለም ክፉ አካሄድ ትከተሉ ነበር፤ እንዲሁም በአየር ላይ ያሉትን የመናፍስት ኀይሎች ለሚገዛው ትታዘዙ ነበር፤ እርሱ በማይታዘዙት ሰዎች ላይ የሚሠራ ርኩሱ መንፈስ ነው። እኛም ሁላችን ከዚህ በፊት በእነርሱ መካከል የሥጋችንን ፈቃድና የአእምሮአችንን ሐሳብ እየተከተልን በሥጋችን ምኞት እንኖር ነበር፤ እንደ ሌሎቹም በተፈጥሮአችን በእግዚአብሔር ቊጣ ሥር ነበርን። ነገር ግን የእግዚአብሔር ምሕረቱ ብዙ ከመሆኑና ለእኛም ያለው ፍቅር ታላቅ ከመሆኑ የተነሣ በበደላችን የሞትን ብንሆንም እንኳ እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር እንድንኖር አድርጎናል፤ እናንተም የዳናችሁት በጸጋው ነው።
ኤፌሶን 2:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እናንተ በበደላችሁና በኀጢአታችሁ ምክንያት ሙታን ነበራችሁ፤ በዚህም የዚህን ዓለም አኗኗር በመከተል፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው፥ በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ እየታዘዛችሁ ትኖሩ ነበር። በእነዚህም ልጆች መካከል እኛም ሁላችን፥ የሥጋችንንና የህዋሳቶቻችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበር፤ ደግሞም እንደ ሌሎቹ በባሕርያችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ እኛን ከወደደበት ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ፥ በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለን ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው።