ኤፌሶን 2:8-16 - ሁሉንም ስሪቶች ያወዳድሩ

ኤፌሶን 2:8-16 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)

በእምነት፣ በጸጋ ድናችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ በሥራ አይደለም፤ ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንድንመላለስባቸው ያዘጋጀልንን መልካም የሆኑትን ሥራዎች እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን። ስለዚህ እናንተ ቀድሞ በትውልድ አሕዛብ የሆናችሁ፣ በአካል ላይ በሰው እጅ ከተደረገው የተነሣ፣ ራሳቸውን “ተገርዘናል” በሚሉት፣ “ያልተገረዙ” የተባላችሁ ያን አስታውሱ፤ በዚያ ዘመን ከክርስቶስ ተለይታችሁ፣ ከእስራኤል ወገንነት ርቃችሁ፣ ለኪዳኑም ተስፋ ባዕዳን ሆናችሁ፣ በዓለም ላይ ያለ ተስፋና ያለ እግዚአብሔር እንደ ነበራችሁ አስታውሱ። አሁን ግን እናንተ ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም አማካይነት ቀርባችኋል። ሁለቱን አንድ ያደረገ፣ የሚለያየውንም የጥል ግድግዳ ያፈረሰ ሰላማችን እርሱ ራሱ ነውና፤ ሕግንም፣ ከትእዛዞቹና ከሥርዐቱ ጋራ በሥጋው ሻረ። ዐላማውም ከሁለቱ አንድን አዲስ ሰው በራሱ ፈጥሮ ሰላምን ለማድረግ ነው። ጥልን በገደለበት በመስቀሉም ሁለቱን በዚህ በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋራ አስታረቀ።

ኤፌሶን 2:8-16 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

እናንተ የዳናችሁት በእምነት አማካይነት በጸጋው ነው፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ በእናንተ ሥራ የተገኘ አይደለም። ማንም ሰው እንዳይመካ፥ የመዳን ጸጋ የተገኘው በሥራ አይደለም፤ እኛ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጃቸውን መልካም ሥራዎች እንድንሠራ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንደገና የተፈጠርን የእግዚአብሔር ፍጡሮች ነን። ስለዚህ እናንተ ቀድሞ በትውልዳችሁ አሕዛብ የነበራችሁ፥ አይሁድ በሰው እጅ በመገረዛቸው እየተመኩ እናንተን ያልተገረዙ እያሉ ይሰድቡአችሁ እንደ ነበር አስታውሱ። እናንተ ከእስራኤል ማኅበረሰብ ግንኙነት የሌላችሁ፥ ለተስፋው ቃል ኪዳን እንግዶች የሆናችሁ፥ በዚህ ዓለምም አንዳች ተስፋ የሌላችሁ፥ ያለ እግዚአብሔር የምትኖሩ፥ ከክርስቶስም የተለያችሁ እንደ ነበራችሁ አስታውሱ። አሁን ግን እናንተ ከዚህ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁት በኢየሱስ ክርስቶስ ሆናችሁ በእርሱ ደም ቀርባችኋል። ለያይቶን የነበረውን የጥል ግድግዳ ያፈረሰና አይሁድንና አሕዛብን አንድ ያደረገ ሰላማችን ክርስቶስ ነው። ከሁለቱ ሕዝቦች ከእርሱ ጋር የሚተባበር አንድ አዲስ ሕዝብን ለመፍጠር የሕግን ትእዛዞችና ደንቦች በሥጋው ሽሮ ሰላምን አደረገ። በመስቀል ላይ በመሞትም ጠላትነትን አስወገደ፤ ሁለቱንም አንድ አካል አድርጎ ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቃቸው።

ኤፌሶን 2:8-16 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))

አም​ነን በጸ​ጋው ድነ​ና​ልና፤ ይህም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጸጋ ነው እንጂ የእ​ና​ንተ ሥራ አይ​ደ​ለም። የሚ​መ​ካም እን​ዳ​ይ​ኖር በም​ግ​ባ​ራ​ችን አይ​ደ​ለም። እን​መ​ላ​ለ​ስ​በት ዘንድ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አስ​ቀ​ድሞ ላዘ​ጋ​ጀው በጎ ሥራ በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ የፈ​ጠ​ረን ፍጥ​ረቱ ነንና። እና​ንተ አሕ​ዛብ አስቡ፤ ቀድሞ በሥጋ ሥር​ዐት ነበ​ራ​ችሁ፤ ያል​ተ​ገ​ዘ​ሩም ይሉ​አ​ችሁ ነበር፤ እን​ዲህ የሚ​ሉ​አ​ች​ሁም የተ​ገ​ዘሩ ሰዎች ናቸው፤ ግዝ​ረት ግን በሥጋ ላይ የሚ​ደ​ረግ የሰው እጅ ሥራ ነው። ያን​ጊዜ ክር​ስ​ቶ​ስን አታ​ው​ቁ​ትም ነበር፤ ከእ​ስ​ራ​ኤል ሕግ የተ​ለ​ያ​ችሁ ነበ​ራ​ችሁ፤ ከተ​ስ​ፋው ሥር​ዐ​ትም እን​ግ​ዶች ነበ​ራ​ችሁ፤ ተስ​ፋም አል​ነ​በ​ራ​ች​ሁም፤ በዚ​ህም ዓለም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን አታ​ው​ቁ​ትም ነበር። አሁን ግን ቀድሞ ርቃ​ችሁ የነ​በ​ራ​ችሁ እና​ንተ በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ሆና​ችሁ በክ​ር​ስ​ቶስ ደም ቀረ​ባ​ችሁ። ሁለ​ቱን አንድ ያደ​ረገ ሰላ​ማ​ችን እርሱ ነውና፥ በሥ​ጋ​ውም በመ​ካ​ከል የነ​በ​ረ​ውን የጥል ግድ​ግዳ አፍ​ርሶ ጥልን ሻረ። ሁለ​ቱ​ንም አድሶ አንድ ያደ​ር​ጋ​ቸው ዘንድ በሥ​ር​ዐቱ የት​እ​ዛ​ዝን ሕግ አጠፋ፤ ዕር​ቅ​ንም አደ​ረገ። በመ​ስ​ቀ​ሉም በአ​ንድ ሥጋው ሁለ​ቱን ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አቀ​ረ​ባ​ቸው፤ በእ​ር​ሱም ጥልን አጠፋ።

ኤፌሶን 2:8-16 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))

ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም። ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም። እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ፤ በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ። አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።

ኤፌሶን 2:8-16 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))

ጸጋው በእምነት አድኗችኋልና፤ ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ የመጣም አይደለም። ማንም እንዳይመካ ከሥራ የመጣም አይደለም። እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ በሕይወት እንድንመላለስ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በትውልድ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በአካል ላይ በሰው እጅ ከተደረገው የተነሣ፥ “ተገርዘናል” በሚሉት፥ “ያልተገረዛችሁ” የተባላችሁትን ያን አስታውሱ፤ በዚያ ዘመን በዚህም ዓለም ያለ ክርስቶስ ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ፥ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ፥ ተስፋን አጥታችሁና ከእግዚአብሔር ተለይታችሁ እንደ ነበር አስታውሱ። አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፥ ሁለቱን አንድ ያደረገ፥ እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሕግን ከትእዛዛቱና ከሥርዓቱ ጋር ሻረ፤ ከሁለቱ አንድ አዲስ ሕዝብ ፈጥሮ ሰላምን አደረገ፤ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለቱን ሕዝቦች በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ።