ኤፌሶን 6:10-13
ኤፌሶን 6:10-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንግዲህስ ወዲህ በእግዚአብሔርና በኀይሉ ጽናት በርቱ። የሰይጣንን ተንኰል መቋቋም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ጋሻ ልበሱ። ሰልፋችሁ፦ ከጨለማ ገዦች ጋርና ከሰማይ በታች ካሉ ከክፉዎች አጋንንት ጋር ነው እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ጋር አይደለምና። ስለዚህም በክፉ ቀን መቃወም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ጋሻ ያዙ፤ እንድትጸኑም በሁሉ የተዘጋጃችሁ ሁኑ።
ኤፌሶን 6:10-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በተረፈ በጌታና ብርቱ በሆነው ኀይሉ ጠንክሩ። የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ መቋቋም ትችሉ ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ። ምክንያቱም ተጋድሏችን ከሥጋና ከደም ጋራ ሳይሆን ከዚህ ከጨለማ ዓለም ገዦች፣ ከሥልጣናትና ከኀይላት እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከርኩሳን መናፍስት ሰራዊት ጋራ ነው። ክፉው ቀን ሲመጣ መቋቋም ትችሉ ዘንድ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ፤ ሁሉን ከፈጸማችሁ በኋላ ጸንታችሁ መቆም ትችላላችሁና።
ኤፌሶን 6:10-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በቀረውስ በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ። የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ። ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ።
ኤፌሶን 6:10-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በቀረውስ በጌታና በእርሱም ታላቅ ኀይል በርቱ፤ የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ ለመቃወም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን የጦር መሣሪያ በሙሉ ልበሱ። የእኛ ውጊያ ከሰዎች ጋር ሳይሆን በዚህ በጨለማ ዘመን ከሚሠሩት ገዢዎች፥ ከባለ ሥልጣኖችና ከዚህ ዓለም ኀይሎችና ይህም ማለት በሰማይ ካሉት ከርኩሳን መናፍስት ሠራዊት ጋር ነው። ስለዚህ በክፉ ቀን የጠላትን ኀይል ለመቋቋም እንድትችሉና ሁሉንም ፈጽማችሁ ጸንታችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር መሣሪያ አንሡ!
ኤፌሶን 6:10-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በተረፈ በጌታ በኃይሉ ብርታትም ጠንክሩ። የዲያብሎስን ሽንገላ ለመቃወም እንድትችሉ፥ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ትጥቅ ልበሱ። ተጋድሏችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለም፤ ነገር ግን ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር፥ ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር፥ በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው። ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን የጦር ትጥቅ አንሡ።