አስቴር 9:20-22 - ሁሉንም ስሪቶች ያወዳድሩ

አስቴር 9:20-22 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)

መርዶክዮስ የተፈጸሙትን እነዚህን ድርጊቶች ጻፈ፤ ደብዳቤ አዘጋጅቶም በመላው የንጉሥ ጠረክሲስ አውራጃ በቅርብና በሩቅ ለሚገኙት አይሁድ ሁሉ ላከ፤ የላከውም የአዳርን ወር ዐሥራ አራተኛና ዐሥራ ዐምስተኛ ቀን በየዓመቱ እንዲያከብሩ ነው፤ የሚያከብሩበትም ምክንያት አይሁድ ከጠላቶቻቸው ዕረፍት ያገኙበት፣ ሐዘናቸው ወደ ደስታ፣ ልቅሷቸውም ወደ ክብረ በዓል የተለወጠበት ቀን ስለ ሆነ ነው። ቀኖቹንም የተድላና የደስታ ቀኖች አድርገው፣ እርስ በርሳቸውም የምግብ ስጦታ እየተለዋወጡና ለድኾችም ስጦታ እየሰጡ እንዲያከብሩ ጻፈላቸው።

አስቴር 9:20-22 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

መርዶክዮስም የዚህን ሁሉ ድርጊት ታሪክ ጽፎ በመላው የፋርስ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ግዛት ውስጥ በቅርብም በሩቅም ወደሚኖሩት አይሁድ ሁሉ በደብዳቤ ላከው። በየዓመቱ የአዳርን ወር ዐሥራ አራተኛና ዐሥራ አምስተኛ ቀን በዓል አድርገው በማክበር እንዲጠብቁት ነገራቸው። እነዚህም ዕለቶች አይሁድ ራሳቸውን ከጠላቶቻቸው እጅ በማዳን ዕረፍት ያገኙባቸው ቀኖች ናቸው፤ ከሐዘንና ከተስፋ መቊረጥ ወደ ደስታና ወደ ሐሴት የተላለፉት በዚህ ወር ነበር፤ በእነዚህ ዕለቶች በዓል አድርገው በመብላትና በመጠጣት እየተደሰቱ፥ እርስ በርሳቸው አንዳቸው ለሌላው የምግብ ስጦታ እየተለዋወጡና ለድኾችም ስጦታ እየሰጡ እንዲጠብቁአቸው ተነገራቸው።

አስቴር 9:20-22 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))

መርዶክዮስም ይህን ነገር ጻፈ፥ በንጉሡም በአርጤክስስ አገሮች ሁሉ በቅርብና በሩቅ ወዳሉት አይሁድ ሁሉ ደብዳቤዎችን ላከ። በየዓመቱም አዳር በሚባለው ወር አሥራ አራተኛውና አሥራ አምስተኛው ቀን፥ አይሁድ ከጠላቶቻቸው ዕረፍትን ያገኙበት ቀን፥ ወሩም ከኀዘን ወደ ደስታ ከልቅሶም ወደ መልካም ቀን የተለወጠበት ወር ሆኖ ይጠብቁት ዘንድ፥ የግብዣና የደስታም ቀን፥ እርስ በርሳቸውም ስጦታ የሚሰጣጡበትና ለድሆች ስጦታ የሚሰጡበት ቀን ያደርጉት ዘንድ አዘዛቸው።