ዘፀአት 3:7-8
ዘፀአት 3:7-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፦ ከአሠሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም ዐውቄአለሁ፤ ከግብፃውያንም እጅ አድናቸው ዘንድ፥ ከዚያችም ሀገር ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ሀገር፥ ወደ ሰፊዪቱና ወደ መልካሚቱ ሀገር፥ ወደ ከነዓናውያንም፥ ወደ ኬጤዎናውያንም፥ ወደ አሞሬዎናውያንም፥ ወደ ፌርዜዎናውያንም፥ ወደ ጌርጌሴዎናውያንም፥ ወደ ኤዌዎናውያንም፥ ወደ ኢያቡሴዎናውያንም ስፍራ አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ።
ዘፀአት 3:7-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለ፣ “በግብፅ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ። ስለዚህም ከግብፃውያን እጅ ልታደጋቸውና ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ሰፊና ለም ወደሆነችው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ላወጣቸው ወርጃለሁ።
ዘፀአት 3:7-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም አለ፦ “በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፤ ከአስገባሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም አውቄአለሁ። ከግብፃውያንም እጅ አድናቸው ዘንድ፥ ከዚያችም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር ወደ ሰፊይቱና ወደ መልካሚቱ አገር ወደ ከነዓናውያንም ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ስፍራ አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ።
ዘፀአት 3:7-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “በግብጽ ያለውን የሕዝቤን ጭንቀት አይቻለሁ፤ በአስጨናቂዎቻቸው ምክንያት የሚጮኹትን ጩኸት ሰምቼአለሁ፤ ጭንቀታቸውንም ዐውቃለሁ። እነርሱንም ከግብጻውያን እጅ ለማዳን ወርጃለሁ፤ ከግብጽም አውጥቼ አሁን ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን፥ የሚኖሩባትን፥ በማርና በወተት የበለጸገችውን ሰፊና ለም የሆነችውን ምድር እሰጣቸዋለሁ።