ዘፍጥረት 39:2-5 - ሁሉንም ስሪቶች ያወዳድሩ
ዘፍጥረት 39:2-5 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋራ ነበረ፤ ኑሮው ተቃናለት፤ እርሱም በግብጻዊው አሳዳሪው ቤት ኖረ። አሳዳሪውም እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ እንዳለና ሥራውንም ሁሉ እንዳከናወለት ባየ ጊዜ፣ ዮሴፍ በርሱ ዘንድ ሞገስ አገኘ፤ የቅርብ አገልጋዩም ሆነ። ጲጥፋራ በቤቱ ላይ ሾመው፤ ያለውንም ሀብት ሁሉ በኀላፊነት ሰጠው። ዮሴፍ በጲጥፋራ ቤትና ባለው ሀብት ሁሉ ላይ ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ፣ እግዚአብሔር የግብጻዊውን ቤት ባረከ፤ የእግዚአብሔርም በረከት በግቢም በውጭም ባለው የጲጥፋራ ሀብት ንብረት ሁሉ ላይ ሆነ።
ዘፍጥረት 39:2-5 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበር፤ ስለዚህም በግብጻዊው አሳዳሪው ቤት ሲኖር ሁሉ ነገር ተቃናለት። እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር እንደ ነበረና ሥራውንም ሁሉ እንዳቃናለት ባየ ጊዜ፥ ጶጢፋር ዮሴፍን ወደደው፤ የቅርብ አገልጋዩም አደረገው፤ በቤቱ ላይ አዛዥነትን፥ በንብረቱም ሁሉ ላይ ኀላፊነትን ሰጠው። ይህም ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር በዮሴፍ ምክንያት የግብጻዊውን ሰው ቤት ንብረትና በውጪም በእርሻ ያለውን ሀብት ሁሉ ባረከለት።
ዘፍጥረት 39:2-5 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
እግዚአብሔርም ከዮሴፍ ጋር ነበር፤ ሥራውም የተከናወነለት ሰው ሆነ፤ በግብፃዊው ጌታውም ቤት ተሾመ። ጌታውም እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር እንዳለ፥ እርሱ የሚሠራውንም ሁሉ እግዚአብሔር በእጁ እንዲያከናውንለት አየ። ዮሴፍም በጌታው ፊት ሞገስን አገኘ፤ እርሱንም ደስ ያሰኘው ነበር፤ በቤቱም ላይ ሾመው፤ ያለውንም ሁሉ በእጁ ሰጠው። እንዲህም ሆነ፤ በቤቱ ባለውም ሁሉ ላይ ከሾመው በኋላ እግዚአብሔር የግብፃዊውን ቤት በዮሴፍ ምክንያት ባረከው። የእግዚአብሔርም በረከት በቤቱም፥ በእርሻውም ባለው ሁሉ ላይ ሆነ።
ዘፍጥረት 39:2-5 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበረ፥ ሥራውም የተከናወነለት ሰው ሆነ በግብፃዊው ጌታውም ቤት ነበረ። ጌታውም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንዳለ እርሱ የሚሠራውንም ሁሉ እግዚአብሔር በእጁ እንዲያከናውንለት አየ ዮሴፍም በጌታው ፊት ሞገስን አገኘ እርሱንም ያገለግለው ነበር በቤቱም ላይ ሾመው ያለውንም ሁሉ በእጁ ሰጠው። እንዲህም ሆነ በቤቱ ባለውም ሁሉ ላይ ከሾመው በኍላ እግዚአብሔር የግብፃዊውን ቤት ስለ ዮሴፍ ባረከው የእግዚአብሔር በረከት በውጪም በግቢም ባለው ሁሉ ላይ ሆነ።
ዘፍጥረት 39:2-5 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
ጌታ ከዮሴፍ ጋር ነበረ፤ ኑሮው ተቃናለት፤ እርሱም በግብፃዊው አሳዳሪው ቤት ኖረ። አሳዳሪውም ጌታ ከእርሱ ጋር እንዳለና ሥራውንም ሁሉ እንዳከናወነለት ባየ ጊዜ፥ ዮሴፍ በእርሱ ዘንድ ሞገስ አገኘ፤ የቅርብ አገልጋዩም ሆነ። ጲጥፋራ በቤቱ ላይ ሾመው፤ ያለውንም ሀብት ሁሉ በኀላፊነት ሰጠው። ዮሴፍ በጲጥፋራ ቤትና ባለው ሀብት ሁሉ ላይ ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ ጌታ የግብፃዊውን ቤት ባረከ፥ የጌታም በረከት በግቢም በውጭም ባለው የጲጥፋራ ሀብት ንብረት ሁሉ ላይ ሆነ።