የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሉቃስ 10:25-37

ሉቃስ 10:25-37 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እነሆም አንድ ቀን፣ አንድ ሕግ ዐዋቂ ኢየሱስን ሊፈትነው ተነሥቶ፣ “መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ላድርግ?” አለው። ኢየሱስም፣ “በሕግ የተጻፈው ምንድን ነው? እንዴትስ ታነብበዋለህ?” ሲል መለሰለት። ሰውየውም መልሶ፣ “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህና በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል” አለው። ኢየሱስም፣ “በትክክል መልሰሃል፤ አንተም እንደዚሁ አድርግ፤ በሕይወት ትኖራለህ” አለው። ሰውየውም ራሱን ጻድቅ ለማድረግ ፈልጎ፣ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መልስ ሰጠው፤ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርድ በወንበዴዎች እጅ ወደቀ፤ ልብሱንም ገፍፈው ደበደቡት፤ በሞት አፋፍ ላይ ጥለውት ሄዱ። አንድ ካህን በአጋጣሚ በዚያው መንገድ ቍልቍል ሲወርድ አየውና ገለል ብሎ ዐለፈ። ደግሞም አንድ ሌዋዊ እዚያ ቦታ ሲደርስ አየውና እርሱም ገለል ብሎ ዐለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን እግረ መንገዱን ሲሄድ ሰውየው ወዳለበት ቦታ ደረሰ፤ ባየውም ጊዜ ዐዘነለት፤ ቀርቦም ቍስሎቹ ላይ ዘይትና የወይን ጠጅ አፍስሶ አሰረለት፤ በራሱም አህያ ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማረፊያ ቤት ወሰደው፤ በዚያም ተንከባከበው። በማግስቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለማረፊያ ቤቱ ባለቤት ሰጠና፣ ‘ይህን ሰው ዐደራ አስታምመው፤ ከዚህ በላይ የምታወጣውንም ወጭ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ’ አለው። “እንግዲህ፣ ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው የትኛው ይመስልሃል?” ሕግ ዐዋቂውም፣ “የራራለት ነዋ” አለ። ኢየሱስም፣ “አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” አለው።

ሉቃስ 10:25-37 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እነሆም፥ አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው ተነሥቶ፦ መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? አለው። እርሱም በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ? አለው። እርሱም መልሶ፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው። ኢየሱስም፦ እውነት መለስህ፤ ይህን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ አለው። እርሱ ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ ኢየሱስን፦ ባልንጀራዬስ ማን ነው? አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ። ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት፥ ቀርቦም ዘይትና የወይ ጠጅ በቍስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፥ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደርያ ወሰደው ጠበቀውም። በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና፦ ጠብቀው፥ ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ አለው። እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል? እርሱም፦ ምሕረት ያደረገለት አለ። ኢየሱስም፦ ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ አለው።

ሉቃስ 10:25-37 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

አንድ ቀን አንድ የሕግ መምህር ወደ ኢየሱስ መጣ፤ ሊፈትነውም ፈልጎ “መምህር ሆይ! የዘለዓለምን ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ ይገባኛል?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም “በሕግ ምን ተጽፎአል? አንብበህስ እንዴት ትረዳዋለህ?” አለው። ሰውየውም “ሕጉማ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ኀይልህ፥ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ እንዲሁም ‘ጐረቤትህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፤’ ይላል” አለው። ኢየሱስም “በትክክል መልሰሃል፤ እንግዲህ አንተም ይህን አድርግ! የዘለዓለም ሕይወትንም ታገኛለህ” አለው። የሕግ መምህሩ ግን ራሱን ጻድቅ ለማድረግ ፈልጎ፥ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርድ በመንገድ ላይ ሳለ ቀማኞች አግኝተውት ልብሱን ገፈፉት፤ ከደበደቡትም በኋላ ሊሞት ሲያጣጥር ጥለውት ሄዱ። እንደ አጋጣሚ አንድ ካህን በዚያ መንገድ ይሄድ ነበር፤ ተደብድቦ የተጣለውን ሰው ባየው ጊዜ ምንም ሳያደርግለት በሌላ በኩል አልፎ ሄደ። እንዲሁም አንድ ሌዋዊ በዚያ መንገድ ይሄድ ነበር፤ እርሱም ሰውየውን ባየው ጊዜ ምንም ሳያደርግለት በሌላ በኩል አልፎ ሄደ። አንድ ሳምራዊ ግን በዚያ በኩል ሲያልፍ ወደ ሰውየው መጣ፤ ባየውም ጊዜ ራራለት፤ ወደ እርሱም ቀርቦ ዘይትና የወይን ጠጅ በቊስሉ ላይ አፈሰሰ፤ በጨርቅም ጠምጥሞ አሠረለት፤ ከዚያም በኋላ በገዛ ራሱ አህያ ላይ አስቀምጦት ወደ አንድ የእንግዶች ማደሪያ ቤት ወሰደው፤ በዚያም በልዩ ጥንቃቄ ተንከባከበው፤ በማግስቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዳ ማደሪያው ባለቤት ሰጠና ‘ይህን ሰው በጥንቃቄ አስታምልኝ፤ ተጨማሪ ወጪ ብታደርግም በምመለስበት ጊዜ እከፍልሃለሁ፤’ አለው። “ታዲያ፥ ከእነዚህ ከሦስት ሰዎች፥ በቀማኞቹ ተደብድቦ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነለት የትኛው ይመስልሃል?” የሕግ መምህሩም “ያ የራራለትና የረዳው ነው፤” ሲል መለሰ፤ ኢየሱስም “እንግዲያውስ ሂድ፤ አንተም እንዲሁ አድርግ!” አለው።

ሉቃስ 10:25-37 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከዚህ በኋላ አንድ ሕግ ዐዋቂ ሊፈ​ት​ነው ተነ​ሣና፥ “መም​ህር ሆይ፥ የዘ​ለ​ዓ​ለም ሕይ​ወ​ትን እወ​ርስ ዘንድ ምን ላድ​ርግ?” አለው። እር​ሱም፥ “በኦ​ሪት ምን ተጽ​ፎ​አል? እን​ዴ​ትስ ታነ​ብ​ባ​ለህ?” አለው። እር​ሱም መልሶ፥ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አም​ላ​ክ​ህን በፍ​ጹም ልብህ፥ በፍ​ጹም ሰው​ነ​ትህ፥ በፍ​ጹም ኀይ​ልህ፥ በፍ​ጹም ዐሳ​ብህ ውደ​ደው፤ ባል​ን​ጀ​ራ​ህ​ንም እንደ ራስህ ውደድ ይላል” አለው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “መል​ካም መል​ሰ​ሃል፤ እን​ዲሁ አድ​ርግ፤ ትድ​ና​ለ​ህም” አለው። ራሱን ሊያ​ከ​ብር ባል​ን​ጀ​ራ​ው​ንም ሊንቅ ወድዶ፥ “ባል​ን​ጀ​ራዬ ማነው?” አለው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ እን​ዲህ አለው፥ “አንድ ሰው ከኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ወደ ኢያ​ሪኮ ይወ​ርድ ነበር፤ ሽፍ​ቶ​ችም አገ​ኙት፤ ደበ​ደ​ቡት፥ አቈ​ሰ​ሉት፥ ልብ​ሱ​ንም ገፍ​ፈው፤ በሕ​ይ​ወ​ትና በሞት መካ​ከል ጥለ​ውት ሄዱ። አንድ ካህ​ንም በዚ​ያች መን​ገድ ሲወ​ርድ ድን​ገት አገ​ኘው፤ አይ​ቶም አል​ፎት ሄደ። እን​ዲ​ሁም አንድ ሌዋዊ በዚያ ቦታ አገ​ኘ​ውና፥ አይቶ እንደ ፊተ​ኛው አል​ፎት ሄደ። አንድ ሳም​ራዊ ግን በዚ​ያች መን​ገድ ሲሄድ አገ​ኘው፤ አይ​ቶም አዘ​ነ​ለት። ወደ እር​ሱም ቀረበ፤ ቍስ​ሉ​ንም አጋ​ጥሞ አሰ​ረ​ለት፤ በቍ​ስሉ ላይም ወይ​ንና ዘይት ጨመ​ረ​ለት፤ በአ​ህ​ያ​ውም ላይ አስ​ቀ​ምጦ እን​ዲ​ፈ​ው​ሰው የእ​ን​ግ​ዶ​ችን ቤት ወደ​ሚ​ጠ​ብ​ቀው ወሰ​ደው፤ የሚ​ድ​ን​በ​ት​ንም ዐሰበ። በማ​ግ​ሥ​ቱም ሁለት ዲናር አው​ጥቶ ለእ​ን​ግዳ ቤት ጠባ​ቂው ሰጠ​ውና፦ ‘በዚህ አስ​ታ​ም​ልኝ፤ ከዚህ የሚ​በ​ልጥ ለእ​ርሱ የም​ታ​ወ​ጣው ቢኖር እኔ በተ​መ​ለ​ስሁ ጊዜ እከ​ፍ​ል​ሃ​ለሁ’ አለው። እን​ግ​ዲህ ሽፍ​ቶች ለደ​በ​ደ​ቡት ሰው ከእ​ነ​ዚህ ከሦ​ስቱ ባል​ን​ጀራ የሚ​ሆ​ነው ማን​ኛው ይመ​ስ​ል​ሃል?” እር​ሱም“ምሕ​ረት ያደ​ረ​ገ​ለት ነዋ” አለው፤ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “እን​ኪ​ያስ አን​ተም ሂድና እን​ዲሁ አድ​ርግ” አለው።

ሉቃስ 10:25-37 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እነሆም፥ አንድ ሕግ አዋቂ ተነሥቶ ሊፈትነው እንዲህ አለ፦ “መምህር ሆይ! የዘለዓለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” እርሱም፦ “በሕግ ምን ተጽፎአል? እንዴትስ ታነበዋለህ?” አለው። እርሱም መልሶ፦ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ፤” አለው። ኢየሱስም፦ “በትክክል መልሰሃል፤ ይህን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ፤” አለው። እርሱ ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ ኢየሱስን፦ “ባልንጀራዬስ ማን ነው?” አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ፤ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት፤ ደበደቡትም፤ በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ። እንደ አጋጣሚም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ፤ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን በጉዞ ላይ ሳለ እርሱ ወደ ነበረበት መጣ አይቶትም አዘነለት፤ ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቁስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፤ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደሪያ ወሰደው፤ ተንከባከበውም። በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዳ ማደሪያው ባለቤት ሰጠና፦ ‘ተንከባከበው፤ ከዚህም በላይ የምታወጣውን ወጪ ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ፤’ አለው። እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል?” እርሱም፦ “ምሕረት ያደረገለት፤” አለ። ኢየሱስም፦ “ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ!” አለው።