ሉቃስ 10:34-37
ሉቃስ 10:34-37 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወደ እርሱም ቀረበ፤ ቍስሉንም አጋጥሞ አሰረለት፤ በቍስሉ ላይም ወይንና ዘይት ጨመረለት፤ በአህያውም ላይ አስቀምጦ እንዲፈውሰው የእንግዶችን ቤት ወደሚጠብቀው ወሰደው፤ የሚድንበትንም ዐሰበ። በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዳ ቤት ጠባቂው ሰጠውና፦ ‘በዚህ አስታምልኝ፤ ከዚህ የሚበልጥ ለእርሱ የምታወጣው ቢኖር እኔ በተመለስሁ ጊዜ እከፍልሃለሁ’ አለው። እንግዲህ ሽፍቶች ለደበደቡት ሰው ከእነዚህ ከሦስቱ ባልንጀራ የሚሆነው ማንኛው ይመስልሃል?” እርሱም“ምሕረት ያደረገለት ነዋ” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እንኪያስ አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” አለው።
ሉቃስ 10:34-37 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ቀርቦም ቍስሎቹ ላይ ዘይትና የወይን ጠጅ አፍስሶ አሰረለት፤ በራሱም አህያ ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማረፊያ ቤት ወሰደው፤ በዚያም ተንከባከበው። በማግስቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለማረፊያ ቤቱ ባለቤት ሰጠና፣ ‘ይህን ሰው ዐደራ አስታምመው፤ ከዚህ በላይ የምታወጣውንም ወጭ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ’ አለው። “እንግዲህ፣ ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው የትኛው ይመስልሃል?” ሕግ ዐዋቂውም፣ “የራራለት ነዋ” አለ። ኢየሱስም፣ “አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” አለው።
ሉቃስ 10:34-37 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ቀርቦም ዘይትና የወይ ጠጅ በቍስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፥ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደርያ ወሰደው ጠበቀውም። በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና፦ ጠብቀው፥ ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ አለው። እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል? እርሱም፦ ምሕረት ያደረገለት አለ። ኢየሱስም፦ ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ አለው።
ሉቃስ 10:34-37 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ወደ እርሱም ቀርቦ ዘይትና የወይን ጠጅ በቊስሉ ላይ አፈሰሰ፤ በጨርቅም ጠምጥሞ አሠረለት፤ ከዚያም በኋላ በገዛ ራሱ አህያ ላይ አስቀምጦት ወደ አንድ የእንግዶች ማደሪያ ቤት ወሰደው፤ በዚያም በልዩ ጥንቃቄ ተንከባከበው፤ በማግስቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዳ ማደሪያው ባለቤት ሰጠና ‘ይህን ሰው በጥንቃቄ አስታምልኝ፤ ተጨማሪ ወጪ ብታደርግም በምመለስበት ጊዜ እከፍልሃለሁ፤’ አለው። “ታዲያ፥ ከእነዚህ ከሦስት ሰዎች፥ በቀማኞቹ ተደብድቦ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነለት የትኛው ይመስልሃል?” የሕግ መምህሩም “ያ የራራለትና የረዳው ነው፤” ሲል መለሰ፤ ኢየሱስም “እንግዲያውስ ሂድ፤ አንተም እንዲሁ አድርግ!” አለው።
ሉቃስ 10:34-37 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቁስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፤ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደሪያ ወሰደው፤ ተንከባከበውም። በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዳ ማደሪያው ባለቤት ሰጠና፦ ‘ተንከባከበው፤ ከዚህም በላይ የምታወጣውን ወጪ ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ፤’ አለው። እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል?” እርሱም፦ “ምሕረት ያደረገለት፤” አለ። ኢየሱስም፦ “ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ!” አለው።