ሉቃስ 6:17-23

ሉቃስ 6:17-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከእ​ነ​ር​ሱም ጋር ወርዶ በሰፊ ቦታ ቆመ፤ ከደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም ወገን ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ከመ​ላው ይሁ​ዳና ከኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም፥ ከጢ​ሮ​ስና ከሲ​ዶና ባሕር ዳርቻ ትም​ህ​ር​ቱን ሊሰሙ፥ ከደ​ዌ​አ​ቸ​ውም ሊፈ​ወሱ የመ​ጡት ከሕ​ዝቡ ወገን እጅግ ብዙ​ዎች ነበሩ። ክፉ​ዎች አጋ​ን​ንት ያደ​ሩ​ባ​ቸ​ውም ይፈ​ወሱ ነበር። ሕዝቡ ሁሉ ሊዳ​ስ​ሱት ይሹ ነበር፤ ኀይል ከእ​ርሱ ይወጣ ነበ​ርና፥ ሁሉ​ንም ይፈ​ው​ሳ​ቸው ነበር። እር​ሱም ወደ ደቀ መዛ​ሙ​ርቱ ዐይ​ኖ​ቹን አን​ሥቶ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እና​ንተ ድሆች፥ ብፁ​ዓን ናችሁ፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ግ​ሥት የእ​ና​ንተ ናትና። ዛሬ የም​ት​ራቡ፥ ብፁ​ዓን ናችሁ፤ ትጠ​ግ​ባ​ላ​ች​ሁና፤ ዛሬ የም​ታ​ለ​ቅሱ፥ ብፁ​ዓን ናችሁ፤ ትስ​ቃ​ላ​ች​ሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ቢጠ​ሉ​አ​ችሁ፥ ከሰው ለይ​ተው ቢአ​ሳ​ድ​ዱ​አ​ችሁ፥ ቢሰ​ድ​ቡ​አ​ችሁ፥ ክፉ ስምም ቢአ​ወ​ጡ​ላ​ችሁ ብፁ​ዓን ናችሁ። ያን​ጊዜ ደስ ይበ​ላ​ችሁ፤ በደ​ስ​ታም ዝለሉ፤ ዋጋ​ችሁ በሰ​ማይ ብዙ ነውና፤ አባ​ቶ​ቻ​ቸ​ውም ነቢ​ያ​ትን እን​ዲሁ አድ​ር​ገ​ዋ​ቸው ነበ​ርና።

ሉቃስ 6:17-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስም ዐብሯቸው ከተራራው ወርዶ ደልዳላ ቦታ ላይ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም እጅግ ብዙ ሰዎች በዚያ ነበሩ፤ ከይሁዳ ሁሉና ከኢየሩሳሌም እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ጠረፍ የመጣ ብዙ ሕዝብም በዚያ ነበረ፤ እነዚህም የመጡት ሊሰሙትና ካለባቸው ደዌ ሊፈወሱ ነበር። በርኩሳን መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩትም ተፈወሱ፤ ኀይል ከርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር፣ ሰዎቹ ሁሉ እርሱን ለመንካት ይፈልጉ ነበር። ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመመልከት እንዲህ አለ፤ “እናንተ ድኾች ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና፤ እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፤ ኋላ ትጠግባላችሁና፤ እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፤ ኋላ ትሥቃላችሁና፤ ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሏችሁ፣ ከመካከላቸው ሲለዩአችሁና ሲነቅፏችሁ፣ ክፉ ስምም ሲሰጧችሁ ብፁዓን ናችሁ። “እነሆ፤ ወሮታችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፣ በዚያ ቀን ደስ ይበላችሁ፤ ፈንድቁም፤ የቀድሞ አባቶቻቸውም በነቢያት ላይ ያደረጉት ይህንኑ ነበርና።

ሉቃስ 6:17-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ከተራራው ወርዶ በሜዳ ላይ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎቹ በዚያ ነበሩ፤ እንዲሁም ሊሰሙትና ከበሽታቸው ሊፈወሱ ፈልገው የመጡ፥ እጅግ ብዙ ሕዝብ ነበሩ። እነርሱም የመጡት ከይሁዳ ምድር ከኢየሩሳሌም ከተማ፥ በባሕር አጠገብ ከሚገኙት ከጢሮስና ከሲዶና ከተሞች ነበር። በርኩሳን መናፍስት ተይዘው ይታወኩ የነበሩት ሰዎችም መጥተው ይፈወሱ ነበር። የማዳን ኀይል ከእርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር የተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ ኢየሱስን ለመንካት ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስ ቀና ብሎ ወደ ደቀ መዛሙርቱ እየተመለከተ እንዲህ አላቸው፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና፥ እናንተ ድኾች የተባረካችሁ ናችሁ! እናንተ አሁን የምትራቡ፥ በኋላ ትጠግባላችሁና የተባረካችሁ ናችሁ! እናንተ አሁን የምታለቅሱ፥ በኋላ ትስቃላችሁና የተባረካችሁ ናችሁ፤ “በእኔ በሰው ልጅ ምክንያት ሰዎች ሲጠሉአችሁ፥ ሲለዩአችሁ፥ ሲያንቋሽሹአችሁና ስማችሁን ሲያጠፉ የተባረካችሁ ናችሁ! በሰማይ ዋጋችሁ ትልቅ ነውና ይህ ሁሉ ሲደርስባችሁ የተባረካችሁ ናችሁ! ሐሴትም አድርጉ፤ የቀድሞ አባቶቻቸውም በነቢያት ላይ እንዲህ ያለውን ክፋት አድርገውባቸው ነበር።