ሉቃስ 8:4-15

ሉቃስ 8:4-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሕዝ​ቡም ሁሉ፥ ከየ​ከ​ተ​ማ​ዉም ሁሉ ወደ እርሱ የመ​ጡት ሲያ​ዳ​ም​ጡት እን​ዲህ ያለ ምሳሌ ነገ​ራ​ቸው። “ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘ​ራም አን​ዳ​ንዱ በመ​ን​ገድ ወደ​ቀና ተረ​ገጠ፤ የሰ​ማይ ወፎ​ችም በሉት። ሌላ​ውም በጭ​ንጫ መሬት ላይ ወደቀ፤ በበ​ቀ​ለም ጊዜ ወዲ​ያው ደረቀ፤ ሥር አል​ነ​በ​ረ​ው​ምና። ሌላ​ዉም በእ​ሾህ መካ​ከል ወደቀ፤ እሾ​ሁም አብሮ አደ​ገና አነ​ቀው። በመ​ል​ካም መሬት ላይ የወ​ደቀ ዘርም ነበረ፤ በበ​ቀ​ለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ።” ይህ​ንም ብሎ፥ “የሚ​ሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” አላ​ቸው። ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም፥ “ይህቺ ምሳሌ ምን​ድን ናት?” ብለው ጠየ​ቁት። እር​ሱም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መን​ግ​ሥት ምሥ​ጢር ማወቅ ለእ​ና​ንተ ተሰ​ጥ​ቶ​አ​ች​ኋል፤ ለእ​ነ​ዚያ ግን አይ​ተው እን​ዳ​ያዩ፥ ሰም​ተ​ውም እን​ዳ​ይ​ሰሙ፥ እን​ዳ​ያ​ስ​ተ​ው​ሉም በም​ሳሌ ነው። ምሳ​ሌ​ዉም ይህ ነው፤ ዘሩ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቃል ነው፤ በመ​ን​ገድ የወ​ደ​ቀው ቃሉን የሚ​ሰሙ ናቸው፤ አም​ነ​ውም እን​ዳ​ይ​ድኑ ሰይ​ጣን መጥቶ ቃሉን ከል​ባ​ቸው ይወ​ስ​ድ​ባ​ቸ​ዋል። በጭ​ን​ጫም ላይ የወ​ደ​ቀው ሰም​ተው ነገ​ሩን በደ​ስታ የሚ​ቀ​በ​ሉት ናቸው፤ ነገር ግን ለጊ​ዜው ያም​ናሉ እንጂ ሥር የላ​ቸ​ውም፤ መከ​ራም በአ​ገ​ኛ​ቸው ጊዜ ይክ​ዳሉ። በእ​ሾ​ህም መካ​ከል የወ​ደ​ቀው ቃሉን ሰም​ተው የባ​ለ​ጠ​ግ​ነት ዐሳብ፥ የኑ​ሮም መቈ​ር​ቈር የተ​ድ​ላና የደ​ስታ መጣ​ፈ​ጥም የሚ​አ​ስ​ጨ​ን​ቃ​ቸ​ውና ፍሬ የማ​ያ​ፈሩ ናቸው። በመ​ል​ካም ምድር የወ​ደ​ቀው ግን ቃሉን በበ​ጎና በን​ጹሕ ልብ የሚ​ሰ​ሙና የሚ​ጠ​ብ​ቁት፥ ታግ​ሠ​ውና ጨክ​ነ​ውም የሚ​ያ​ፈሩ ናቸው።

ሉቃስ 8:4-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰብስቦ ሳለ፣ ደግሞም ሰዎች ከተለያዩ ከተሞች ወደ እርሱ በሚጐርፉበት ጊዜ፣ ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “አንድ ዐራሽ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፣ በእግርም ተረጋገጠ፤ የሰማይ ወፎችም በሉት። አንዳንዱም ዘር በድንጋያማ ቦታ ላይ ወደቀ፤ እንደ በቀለም ርጥበት አልነበረውምና ደረቀ። ሌላው ዘር ደግሞ በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም ዐብሮት አደገና ዐንቆ አስቀረው። ሌላውም ዘር በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ ዕጥፍ አፈራ።” ይህን ብሎ ሲያበቃም ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ። ደቀ መዛሙርቱም የዚህን ምሳሌ ትርጕም ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ምስጢር ማወቅ ለእናንተ ተሰጥቷል፤ ለሌሎች ግን በምሳሌ እናገራለሁ፤ ይኸውም፣ “ ‘እያዩ ልብ እንዳይሉ፣ እየሰሙም እንዳያስተውሉ ነው።’ “እንግዲህ የምሳሌው ትርጕም ይህ ነው፤ ዘር የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ነው። በመንገድ ዳር የወደቀው ቃሉን የሚሰሙ፣ ነገር ግን አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው የሚወስድባቸው ናቸው። በድንጋያማ ቦታ ላይ የወደቀውም ቃሉን ሲሰሙ በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነዚህ ለጊዜው ያምናሉ እንጂ ሥር ስለሌላቸው በፈተና ጊዜ ፈጥነው የሚክዱ ናቸው። በእሾኽ መካከል የወደቀውም ቃሉን የሚሰሙት ናቸው፤ እነዚህም ውለው ዐድረው በምድራዊ ሕይወት ጭንቀት፣ በባለጠግነትና ተድላ ደስታ ታንቀው በሚገባ አያፈሩም። በመልካም መሬት ላይ የወደቀውም ቃሉን ቅንና በጎ በሆነ ልብ ሰምተው የሚጠብቁ፣ ታግሠውም በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።

ሉቃስ 8:4-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ብዙ ሕዝብም በተሰበሰቡ ጊዜ ከከተማዎችም ሁሉ ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በምሳሌ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፦ ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ ተረገጠም፥ የሰማይ ወፎችም በሉት። ሌላውም በዓለት ላይ ወደቀ፥ በበቀለም ጊዜ እርጥበት ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾሁም አብሮ በቀለና አነቀው። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ። ይህን በተናገረ ጊዜ፦ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ ብሎ ጮኸ። ደቀ መዛሙርቱም፦ ይህ ምሳሌ ምንድር ነው? ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አለ፦ ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለሌሎች ግን እያዩ እንዳያዩ እየሰሙም እንዳያስተውሉ በምሳሌ ነው። ምሳሌው ይህ ነው። ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በመንገድ ዳርም ያሉት የሚሰሙ ናቸው፤ ከዚህ በኋላም ዲያብሎስ ይመጣል አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። በዓለት ላይም ያሉት ሲሰሙ ቃሉን በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነርሱም ለጊዜው ብቻ ያምናሉ እንጂ በፈተና ጊዜ የሚክዱ ሥር የሌላቸው ናቸው። በእሾህ መካከልም የወደቀ እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፥ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። በመልካም መሬት ላይም የወደቀ እነርሱ በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።

ሉቃስ 8:4-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ብዙ ሕዝብ ከየከተማው ወደ እርሱ መጥተው በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ “አንድ ገበሬ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም አንዳንዱ ዘር በመንገድ ዳር ወደቀና ተረገጠ፤ ወፎችም በሉት። ሌላውም ዘር በጭንጫማ መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መሬቱ እርጥበት ስላልነበረው ቡቃያው ደረቀ። ሌላውም ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹ አብሮ አደገና አንቆ አስቀረው። ሌላው ዘር ግን በመልካም መሬት ላይ ወድቆ በቀለ፤ ቡቃያውም አድጎ እያንዳንዱ መቶ እጥፍ አፈራ።” ቀጥሎም ኢየሱስ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” አለ። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን “የዚህ ምሳሌ ትርጒም ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ሌሎች ግን ሁሉ ነገር በምሳሌ ይነገራቸዋል፤ እነርሱ እያዩ ልብ እንዳያደርጉ፥ እየሰሙም እንዳያስተውሉ ነው።” የምሳሌው ትርጒም ይህ ነው፦ “ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ቃሉን ለጊዜው የሚሰሙትን ሰዎች ነው፤ ነገር ግን እነርሱ አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። በጭንጫማ መሬት ላይ የወደቀውም ዘር የሚያመለክተው ቃሉን ሰምተው በደስታ የሚቀበሉትን ሰዎች ነው፤ ነገር ግን እነርሱ የሚያምኑት ለጊዜው ነው፤ ሥር ስለሌላቸውም በፈተና ጊዜ ወዲያውኑ ይክዳሉ። በእሾኽም ቊጥቋጦ መካከል የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ቃሉን ለጊዜው የሚሰሙትን ሰዎች ነው፤ ነገር ግን የዚህ ዓለም ሐሳብና ሀብት፥ የምድራዊ ኑሮ ምቾትም አንቆ ያለ ፍሬ ያስቀራቸዋል። በመልካም መሬት ላይ የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ግን በመልካምና በቅን ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁትን ነው፤ እነርሱ በቃሉ ጸንተው ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።”

ሉቃስ 8:4-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ብዙ ሕዝብም በተሰበሰበና ከየከተማውም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ እንዲህ ሲል በምሳሌ ተናገረ፦ “ዘሪ ዘሩን ለመዝራት ወጣ። በሚዘራበትም ጊዜ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ተረገጠም፤ የሰማይ ወፎችም ጨረሱት። ሌላውም በዐለት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ እርጥበት ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾሁም አብሮ በቀለና አነቀው። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ።” ይህንንም እየተናገረ፦ “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ፤” ብሎ ጮኸ። ደቀ መዛሙርቱም፦ “ይህ ምሳሌ ትርጓሜው ምንድነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለሌሎች ግን እያዩ እንዳያዩ እየሰሙም እንዳያስተውሉ በምሳሌዎች ይነገራቸዋል” አላቸው። “የምሳሌውም ትርጒም ይህ ነው፦ ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በመንገድ ዳርም ያሉት የሰሙት ናቸው፤ ከዚያ በኋላም አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። እንዲሁም በዐለት ላይ ያሉት ቃሉን በሰሙ ጊዜ በደስታ የሚቀበሉት ናቸው፤ ነገር ግን ሥር የላቸውም፥ እነርሱም ለጊዜው ብቻ ያምናሉ እንጂ በፈተና ጊዜ ይክዳሉ። በእሾህም መካከል የወደቁት እንዲሁ ከእነዚያ ከሰሙት ወገን ናቸው፤ በመንገዳቸውም በዚህ የምድራዊ ሕይወት ምኞትና ሀብት እንዲሁም ምቾት ይታነቃሉ፤ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። በመልካም መሬት ላይ ያሉት ደግሞ ቃሉን በመልካምና በቅን ልብ ሰምተው የሚጠብቁ፥ በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።