ማቴዎስ 16:5-12 - ሁሉንም ስሪቶች ያወዳድሩ

ማቴዎስ 16:5-12 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)

ባሕሩን እንደ ተሻገሩም፣ ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ረስተው ነበር። ኢየሱስም፣ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ” አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው፣ “እንጀራ ስላልያዝን ነው” ተባባሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ እርስ በርሳችሁ፣ እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት የምትነጋገሩት ስለ ምንድን ነው? ዐምስቱ እንጀራ ለዐምስት ሺሕ ሰው በቅቶ ስንት መሶብ ተርፎ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? እንዲሁም ሰባቱ እንጀራ ለአራት ሺሕ ሰው በቅቶ ስንት መሶብ ተርፎ እንዳነሣችሁ ልብ አላላችሁም ማለት ነውን? ታዲያ የነገርኋችሁ ስለ እንጀራ እንዳልሆነ እንዴት አታስተውሉም? አሁንም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ።” በዚህ ጊዜ ያስጠነቀቃቸው እንጀራ ውስጥ ስለሚጨመረው እርሾ ሳይሆን፣ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት መሆኑ ገባቸው።

ማቴዎስ 16:5-12 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕር ማዶ በተሻገሩ ጊዜ ረስተው እንጀራ አልያዙም ነበር፤ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ልብ አድርጉ፤ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ” አላቸው። እነርሱም “ይህን ማለቱ ምናልባት እንጀራ ስላልያዝን ይሆናል” በማለት እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ! ‘እንጀራ ስላልያዝን ነው’ ብላችሁ ስለምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? ገና የማታስተውሉ ናችሁን? አምስት እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው እንደበቃና የተረፈውን ፍርፋሪ ምን ያኽል መሶብ ሙሉ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? እንዲሁም ሰባት እንጀራ ለአራት ሺህ ሰው እንደበቃና የተረፈውን ፍርፋሪ ምን ያኽል መሶብ ሙሉ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? እንግዲህ ‘ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ!’ ብዬ ስነግራችሁ ስለ እንጀራ አለመሆኑን እንዴት አታስተውሉም?” ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ተጠንቀቁ ያላቸው ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዳልሆነ ተገነዘቡ።

ማቴዎስ 16:5-12 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))

ደቀ መዛሙርቱም ወደ ማዶ በመጡ ጊዜ እንጀራ መያዝን ረሱ። ኢየሱስም “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ፤” አላቸው። እነርሱም “እንጀራ ባንይዝ ነው፤” ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እንጀራ ስለ ሌላችሁ ስለ ምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? ገና አታስተውሉምን? ለአምስቱ ሺህ አምስቱ እንጀራ፥ ስንት መሶብም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? ወይስ ለአራቱ ሺህ ሰባቱ እንጀራ፥ ስንት ቅርጫትም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ እንድትጠበቁ ብዬ ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉም?” እነርሱም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠበቁ እንዳላላቸው ያን ጊዜ አስተዋሉ።

ማቴዎስ 16:5-12 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))

ደቀ መዛሙርቱም ወደ ማዶ በመጡ ጊዜ እንጀራ መያዝን ረሱ። ኢየሱስም፦ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ አላቸው። እነርሱም፦ እንጀራ ባንይዝ ነው ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው፦ እናንተ እምነት የጕኦደላችሁ፥ እንጀራ ስለ ሌላችሁ ስለ ምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? ገና አታስተውሉምን? ለአምስቱ ሺህ አምስቱ እንጀራ፥ ስንት መሶብም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? ወይስ ለአራቱ ሺህ ሰባቱ እንጀራ፥ ስንት ቅርጫትም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ እንድትጠበቁ ብዬ ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉምን? እነርሱም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠበቁ እንዳላላቸው ያን ጊዜ አስተዋሉ።

ማቴዎስ 16:5-12 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))

ደቀመዛሙርቱ ወደ ማዶ በሚሻገሩበት ጊዜ እንጀራ መያዝን ረስተው ነበር። ኢየሱስም “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ” አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው “እንጀራ ስላልያዝን ነው” ብለው አሰቡ። ኢየሱስም ይህንን አውቆ እንዲህ አላቸው “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እንጀራ ስላልያዛችሁ ለምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? አሁንም አታስተውሉምን? አምስቱ እንጀራ ለአምስት ሺህ በቅቶ ስንት መሶብ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? እንዲሁም ሰባቱ እንጀራ ለአራት ሺህ በቅቶ ስንት ቅርጫት እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉም? ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ።” ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠነቀቁ እንዳልነገራቸው ተገነዘቡ።