ማቴዎስ 23:23-28 - ሁሉንም ስሪቶች ያወዳድሩ
ማቴዎስ 23:23-28 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
“እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! ከአዝሙድ፣ ከእንስላልና ከከሙን ዐሥራት እየሰጣችሁ በሕጉ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን ማለትም ፍትሕን፣ ምሕረትንና ታማኝነትን ግን ንቃችኋልና፤ እነዚያን ሳትተዉ እነዚህን ማድረግ በተገባችሁ ነበር፤ እናንተ የታወራችሁ መሪዎች፤ ትንኝን አጥርታችሁ ትጥላላችሁ፤ ግመልን ግን ትውጣላችሁ። “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጸዳላችሁ፤ በውስጣቸው ግን ቅሚያና ሥሥት ሞልቶባቸዋል። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፤ አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጥ አጽዳ፤ ከዚያም ውጭው የጸዳ ይሆናል። “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ውጫቸው በኖራ ተለስነው የሚያምሩ፣ ውስጣቸው ግን በሙታን ዐፅምና በብዙ ርኩሰት የተሞላ መቃብሮችን ስለምትመስሉ ወዮላችሁ! እናንተም በውጭ ለሰዎች ጻድቃን ትመስላላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በግብዝነትና በክፋት የተሞላ ነው።
ማቴዎስ 23:23-28 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
“እናንተ ግብዞች የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ! ከአዝሙድ፥ ከእንስላል፥ ከከሙን ዐሥራት ትሰጣላችሁ፤ ነገር ግን በሕግ ውስጥ የሚገኙትን ዋና ዋና ነገሮች ትተዋላችሁ፤ እነርሱም ትክክለኛ ፍርድ፥ ምሕረትና ታማኝነት ናቸው፤ ያንን ሳትተዉ ይህንንም ማድረግ ይገባችሁ ነበር። እናንተ ዕውሮች መሪዎች! ከምትጠጡትም ሁሉ እንደ ትንኝ ትንሽ የሆነችውን ነገር አጥልላችሁ ትጥላላችሁ፤ እንደ ግመል ትልቅ የሆነውን ነገር ግን ትውጣላችሁ! “እናንተ ግብዞች የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ! ብርጭቆውንና ሳሕኑን ከውጪ በኩል ታጠራላችሁ፤ ውስጡ ግን ቅሚያና ሥሥት የሞላበት ነው፤ አንተ ዕውር ፈሪሳዊ! አስቀድመህ ብርጭቆውንና ሳሕኑን ከውስጥ በኩል አጥራ! በዚያን ጊዜ በውጪም በኩል ንጹሕ ይሆናል። “እናንተ ግብዞች የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ! በውስጣቸው በሞቱ ሰዎች አጥንትና በርኩስ ነገር ሁሉ የተሞሉ፥ በውጪ ግን በኖራ ተለስነው የሚያምሩ መቃብሮችን ትመስላላችሁ። እንዲሁም እናንተ፥ በውጪ ለሰው ጻድቃን መስላችሁ ትታያላችሁ፤ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ክፋት ሞልቶባችኋል።
ማቴዎስ 23:23-28 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
“እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር። እናንተ ዕውሮች መሪዎች! ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ፥ ወዮላችሁ። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ! ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ። እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፤ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዐመፀኝነት ሞልቶባችኋል።
ማቴዎስ 23:23-28 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር። እናንተ ዕውሮች መሪዎች፥ ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ፥ ወዮላችሁ። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፥ ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ። እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፥ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል።
ማቴዎስ 23:23-28 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
“እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን!ወዮላችሁ፥ ምክንያቱም ከአዝሙድ፥ ከእንስላልና ከከሙን አሥራት ታወጣላችሁ፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ፍርድን፥ ምሕረትንና እምነትን ትተዋላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ እነዚህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር። እናንተ ዕውራን መሪዎች! ትንኝን አጥልላችሁ ታወጣላችሁ ግመልን ግን ትውጣላችሁ። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን!ወዮላችሁ፥ የጽዋውንና የሳሕኑን ውጭ ታጠራላችሁ በውስጣቸው ግን ቅሚያና ራስን አለመግዛት ሞልቶባቸዋል። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ! ውጭው ንጹሕ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውን ውስጡን አጥራ። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን!ወዮላችሁ፥ በውጫቸው አምረው የሚታዩ በውስጣቸው ግን በሙታን አጥንትና በርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ትመስላላችሁና። እንዲሁም እናንተ በውጭ ለሰው ጻድቃን መስላችሁ ትታያላችሁ፤ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ሕገ ወጥነት ሞልቶባችኋል።