መዝሙር 119:41-80

መዝሙር 119:41-80 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ወደ እኔ ይምጣ፤ ማዳንህም እንደ ቃልህ ይላክልኝ። በቃልህ ታምኛለሁና፣ ለሚሰድቡኝ መልስ እሰጣለሁ። ሕግህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣ የእውነትን ቃል ከአፌ ፈጽመህ አታርቅ። ከዘላለም እስከ ዘላለም፣ ሕግህን ዘወትር እጠብቃለሁ። ሥርዐትህን እሻለሁና፣ እንደ ልቤ ወዲያ ወዲህ እመላለሳለሁ። ምስክርነትህን በነገሥታት ፊት እናገራለሁ፤ ይህን በማድረግም ዕፍረት አይሰማኝም። እኔ እወድደዋለሁና፣ በትእዛዝህ ደስ ይለኛል። እጆቼን ወደምወዳቸው ትእዛዞችህ አነሣለሁ፤ ሥርዐትህንም አሰላስላለሁ። ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል ዐስብ፤ በዚያ ተስፋ ሰጥተኸዋልና። ቃልህ ሕያው ያደርገኛልና፣ ይህች በመከራዬ መጽናኛዬ ናት። እብሪተኞች እጅግ ተሣለቁብኝ፤ እኔ ግን ከሕግህ ንቅንቅ አልልም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ከጥንት የነበረውን ድንጋጌህን አሰብሁ፤ በዚህም ተጽናናሁ። ሕግህን ከተዉ ክፉዎች የተነሣ፣ ቍጣ ወረረኝ። በእንግድነቴ አገር፣ ሥርዐትህ መዝሙሬ ናት። እግዚአብሔር ሆይ፤ ስምህን በሌሊት ዐስባለሁ፤ ሕግህንም እጠብቃለሁ። ሥርዐትህን እከተላለሁ፤ ይህችም ተግባሬ ሆነች። እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤ ቃልህን ለመታዘዝ ቈርጫለሁ። በፍጹም ልቤ ፊትህን ፈለግሁ፤ እንደ ቃልህ ቸርነትህን አሳየኝ። መንገዴን ቃኘሁ፤ አካሄዴንም ወደ ምስክርህ አቀናሁ። ትእዛዝህን ለመጠበቅ፣ ቸኰልሁ፤ አልዘገየሁምም። የክፉዎች ገመድ ተተበተበብኝ፤ እኔ ግን ሕግህን አልረሳሁም። ስለ ጻድቅ ሥርዐትህ፣ በእኩለ ሌሊት ላመሰግንህ እነሣለሁ። እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፣ ሥርዐትህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ምድር በምሕረትህ ተሞላች፤ ሥርዐትህን አስተምረኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ፣ ለአገልጋይህ በጎ ውለሃል። በትእዛዞችህ አምናለሁና፣ በጎ ማስተዋልንና ዕውቀትን አስተምረኝ። እንዲያው ሳይቸግረኝ መንገድ ስቼ ሄድሁ፤ አሁን ግን ቃልህን እጠብቃለሁ። አንተ መልካም ነህ፤ የምታደርገው መልካም ነው፤ እንግዲህ ሥርዐትህን አስተምረኝ። እብሪተኞች ስሜን በሐሰት አጠፉ፤ እኔ ግን ትእዛዝህን በፍጹም ልብ እጠብቃለሁ። ልባቸው የሠባና የደነደነ ነው፤ እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል። ሥርዐትህን እማር ዘንድ፣ በመከራ ውስጥ ማለፌ መልካም ሆነልኝ። ከአእላፋት ብርና ወርቅ ይልቅ፣ ከአፍህ የሚወጣው ሕግ ይሻለኛል። እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ ትእዛዞችህን እንድማር ማስተዋልን ስጠኝ። ቃልህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣ የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይበላቸው። እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍርድህ የጽድቅ ፍርድ፣ ያስጨነቅኸኝም በታማኝነት እንደ ሆነ ዐወቅሁ። ለአገልጋይህ በገባኸው ቃል መሠረት፣ ምሕረትህ ለመጽናናት ትሁነኝ። ሕግህ ደስታዬ ነውና፣ በሕይወት እኖር ዘንድ ቸርነትህ ትምጣልኝ። እብሪተኞች ያለ ምክንያት በደል አድርሰውብኛልና ይፈሩ፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን አሰላስላለሁ። አንተን የሚፈሩህ፣ ምስክርነትህንም የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ። እኔ እንዳላፍር፣ ልቤ በሥርዐትህ ፍጹም ይሁን።

መዝሙር 119:41-80 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር ሆይ! ዘለዓለማዊ ፍቅርህ ወደ እኔ ይድረስ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት አድነኝ። በቃልህ ስለምተማመን ለሚሰድቡኝ ሁሉ መልስ መስጠት እችላለሁ። ተስፋ የማደርገው የአንተን ፍርድ ስለ ሆነ ዘወትር እውነት እንድናገር እርዳኝ። ሕግህን ባለማቋረጥ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም እፈጽማለሁ። ትእዛዝህን መፈጸም ስለምወድ በፍጹም ነጻነት እኖራለሁ። ትእዛዞችህን በነገሥታት ፊት እናገራለሁ፤ ከቶም አላፍርም። በትእዛዞችህ የምደሰተው እነርሱን ስለምወዳቸው ነው። የምወዳቸውን ትእዛዞችህን አከብራለሁ፤ ስለ ሥርዓትህም በተመስጦ አሰላስላለሁ። ተስፋ የማደርገው በእርሱ ላይ ስለ ሆነ ለእኔ ለአገልጋይህ የሰጠኸውን የተስፋ ቃል አስብ። የተስፋ ቃልህ ሕይወቴን ስላደሰልኝ፥ በመከራዬ ጊዜ እንኳ እጽናናለሁ። ትዕቢተኞች ዘወትር ያፌዙብኛል፤ እኔ ግን ከትእዛዞችህ አልርቅም። እግዚአብሔር ሆይ! መጽናናትን የሚሰጠኝ ስለ ሆነ ከጥንት ጀምሮ የነበረውን ሕግህን አስታውሳለሁ። ክፉ ሰዎች ሕግህን ሲተላለፉ በማየቴ በብርቱ ተቈጣሁ። በምኖርበት ቦታ ሁሉ ሕጎችህ የመዝሙሬ አዝማቾች ናቸው። እግዚአብሔር ሆይ! በሌሊት ስምህን አስታውሳለሁ፤ በሕግህም ጸንቼ እኖራለሁ። ትእዛዞችህን ዘወትር ስለማከብር፥ በረከትን አገኘሁ። እግዚአብሔር ሆይ! እኔ የምፈልገው አንተን ብቻ ነው፤ ሕግህንም ለመጠበቅ ቃል እገባለሁ። በተስፋ ቃልህ መሠረት ምሕረት እንድታደርግልኝ ከልብ እለምንሃለሁ። አካሄዴን መርምሬ የተረዳሁት ስለ ሆነ ሥርዓትህን ለመከተል ቃል እገባለሁ። ያለ ማመንታት ትእዛዞችህን ለመፈጸም እተጋለሁ። ክፉዎች ወጥመድ ቢዘረጉብኝም እኔ ግን ሕግህን አልረሳም። ስለ ትክክለኛ ፍርድህ አንተን ለማመስገን በእኩለ ሌሊት እነሣለሁ። አንተን የሚፈሩትንና ሕግህን የሚያከብሩትን ሁሉ እወዳቸዋለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! ምድር በዘለዓለማዊው ፍቅርህ የተሞላች ናት፤ ሕጎችህን አስተምረኝ። እግዚአብሔር ሆይ! የተስፋ ቃልህን ጠብቀሃል፤ ለእኔም ለአገልጋይህ ቸር ሆነሃል። በትእዛዞችህ ስለምተማመን አስተዋይነትንና ዕውቀትን ስጠኝ። አንተ እኔን ከመቅጣትህ በፊት እሳሳት ነበር፤ አሁን ግን ለቃልህ እታዘዛለሁ። አንተ ቸር ስለ ሆንክ ቸር የሆነውን ታደርጋለህ፤ ሕጎችህን አስተምረኝ። ምንም እንኳ ትዕቢተኞች በሐሰት ስሜን ቢያጠፉ እኔ ትእዛዞችህን በሙሉ ልቤ እጠብቃለሁ። እነርሱ ትዕቢተኞችና ስሜተ ቢሶች ናቸው፤ እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል። ሕግህን እንድማር ስላደረገኝ መቀጣቴ መልካም ሆነልኝ። ከብዙ ወርቅና ከብዙ ብር ይልቅ ለእኔ እጅግ ዋጋ ያለው አንተ የምትሰጠው ሕግ ነው። እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ ትእዛዞችህን እማር ዘንድ አስተዋይነትን ስጠኝ። በተስፋ ቃልህ ስለምታመን አንተን የሚያከብሩ ሁሉ እኔን በሚያዩበት ጊዜ ደስ ይበላቸው። እግዚአብሔር ሆይ! ፍርድህ እውነተኛ እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤ የቀጣኸኝም እውነተኛ በመሆንህ ነው። ለእኔ ለአገልጋይህ በሰጠኸው የተስፋ ቃል መሠረት ዘለዓለማዊው ፍቅርህ ያጽናናኝ። በሕግህ ደስ ስለሚለኝ ሕያው ሆኜ ለመኖር እችል ዘንድ ርኅራኄ አድርግልኝ። በሐሰት ያለምክንያት የሚከሱኝ ትዕቢተኞች ይዋረዱ፤ እኔ ግን ሕግህን አሰላስላለሁ። አንተን የሚፈሩ ትእዛዞችህን ያውቁ ዘንድ ወደ እኔ ይምጡ። ኀፍረት እንዳይደርስብኝ ሕግህን በትክክል እንድፈጽም እርዳኝ።

መዝሙር 119:41-80 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አቤቱ፥ እንደ ቃልህ፥ ምሕረትህና መድኃኒትህ ይምጡልኝ። በቃልህ ታምኛለሁና ለሚሰድቡኝ በነገር እመልስላቸዋለሁ። በፍርድህም ታምኛለሁና የእውነትን ቃል ከአፌ ፈጽመህ አታርቅ። ለዘለዓለም ዓለም ሁልጊዜ ሕግህን እጠብቃለሁ። ትእዛዛትህንም ፈልጌአለሁና አስፍቼ እሄዳለሁ። በነገሥታት ፊት ምስክርህን እናገራለሁ፥ አላፍርምም፥ እጅግም በወደድኋቸው በትእዛዛትህ ደስ ይለኛል። እጆቼንም ወደ ወደድኋቸው ወደ ትእዛዛትህ አነሣለሁ፥ ሥርዓትህንም አሰላስላለሁ። ለባርያህ የሰጠኸውን የተስፋ ቃልህን አስብ። ቃልህ ሕያው አድርጎኛልና ይህች በመከራዬ ደስ አሰኘችኝ። ትዕቢተኞች እጅግ ዐመፁ፥ እኔ ግን ከሕግህ አልራቅሁም። ከጥንት የነበረውን ፍርድህን አሰብሁ፥ አቤቱ፥ ተጽናናሁም። ሕግህን ከተዉ ከኃጢአተኞች የተነሣ ኀዘን ያዘኝ። በእንግድነቴ አገር ሥርዓትህ መዝሙር ሆነችኝ። አቤቱ፥ በሌሊት ስምህን አሰብሁ፥ ሕግህንም ጠበቅሁ። ትእዛዛትህንም ፈልጌአለሁና ይህች ሆነችልኝ። ጌታ ድርሻዬ ነው፥ ቃልህን እጠብቃለሁ አልሁ። በፍጹም ልቤ ወደ ፊትህ ተማለልሁ፥ እንደ ቃልህ ማረኝ። ስለ መንገዶችህ አሰብሁ፥ እግሬንም ወደ ምስክሮችህ መለስሁ። ትእዛዝህን ለመጠበቅ ጨከንሁ አልዘገየሁምም። የኀጥኣን ገመዶች ተተበተቡብኝ፥ ሕግህን ግን አልረሳሁም። ስለ ጽድቅህ ፍርድ፥ በእኩለ ሌሊት አመሰግንህ ዘንድ እነሣለሁ። እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፥ ትእዛዝህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ። አቤቱ፥ ምሕረትህ በምድር ሁሉ ሞላች፥ ሥርዓትህን አስተምረኝ። አቤቱ፥ እንደ ቃልህ ለባርያህ መልካም አደረግህ። በትእዛዛትህ ታምኛለሁና መልካም ምክርና እውቀትን አስተምረኝ። በፊት ስቼ ከመንገድህ ርቄ ነበር፥ አሁን ግን ቃልህን ጠበቅሁ። አቤቱ፥ አንተ ቸር ነህ፥ በቸርነትህም ሥርዓትህን አስተምረኝ። የትዕቢተኞች ዓመጽ በላዬ በዛ፥ እኔ ግን በፍጹም ልቤ ትእዛዛትህን እፈልጋለሁ። ልባቸው እንደ ወተት ረጋ፥ እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል። ሥርዓትህን እማር ዘንድ ያስጨነቅኸኝ መልካም ሆነልኝ። ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል። ዮድ። እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም፥ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ትእዛዛትህንም እማራለሁ። በቃልህ ታምኛለሁና የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይላቸዋል። አቤቱ፥ ፍርድህ ጽድቅ እንደ ሆነች፥ በእውነትህም እንዳስቸገርኸኝ አወቅሁ። ምሕረትህ ለመጽናናቴ ትሁነኝ፥ እንደ ቃልህም ለባርያህ ይሁነው። ሕግህ ተድላዬ ናትና ቸርነትህ ትምጣልኝ፥ በሕይወትም ልኑር። ትዕቢተኞች በዓመፅ ጠምመውብኛልና ይፈሩ፥ እኔ ግን ትእዛዝህን አሰላስላለሁ። የሚፈሩህና ምስክሮችህን የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ። እንዳላፍር ልቤ በሥርዓትህ የቀና ይሁን።