ራእይ 22:1-21
ራእይ 22:1-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውሃ ወንዝ አሳየኝ። በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ ዐሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ። ከእንግዲህም ወዲህ መርገም ከቶ አይሆንም። የእግዚአብሔርና የበጉም ዙፋን በእርስዋ ውስጥ ይሆናል፤ ባሪያዎቹም ያመልኩታል፤ ፊቱንም ያያሉ፤ ስሙም በግምባሮቻቸው ይሆናል። ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይሆንም፤ ጌታ አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና የመብራት ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣሉ። እርሱም “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፤ የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ።” እነሆም “በቶሎ እመጣለሁ። የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው፤” አለኝ። ይህንም ያየሁትና የሰማሁት እኔ ዮሐንስ ነኝ። በሰማሁትና ባየሁትም ጊዜ ይህን ባሳየኝ በመልአኩ እግር ፊት እሰግድ ዘንድ ተደፋሁ። እርሱም “እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ነቢያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤” አለኝ። ለእኔም “ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው። ዐመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፤ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፤ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፤ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ፤” አለ። “እነሆ በቶሎ እመጣለሁ፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።” ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱም እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው። ውሻዎችና አስማተኞች ሴሰኛዎችም ነፍሰ ገዳዮችም ጣዖትንም የሚያመልኩት ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ። “እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልአኬን ላክሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፤ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ።” መንፈሱና ሙሽራይቱም “ና!” ይላሉ። የሚሰማም “ና!” ይበል። የተጠማም ይምጣ፤ የወደደም የሕይወትን ውሃ እንዲያው ይውሰድ። በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የትንቢት ቃል ለሚሰማ ሁሉ እኔ እመሰክራለሁ፤ ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር፥ እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል፤ ማንምም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ቢያጎድል፥ በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ዕድሉን ያጎድልበታል። ይህን የሚመሰክር “አዎን በቶሎ እመጣለሁ፤” ይላል። አሜን፤ ጌታ ኢየሱስ ሆይ!ጅ ና። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን።
ራእይ 22:1-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ በኋላ መልአኩ ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ መስተዋት የጠራውን የሕይወት ውሃ ወንዝ አሳየኝ፤ ወንዙም በከተማዪቱ አውራ መንገድ መካከል ይፈስስ ነበር። በወንዙ ግራና ቀኝ በየወሩ እያፈራ ዐሥራ ሁለት ጊዜ ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ የዛፉም ቅጠሎች ሕዝቦች የሚፈወሱባቸው ነበሩ። ከእንግዲህ ወዲህ ርግማን ከቶ አይኖርም፤ የእግዚአብሔርና የበጉ ዙፋን በከተማዪቱ ውስጥ ይሆናል፤ ባሮቹም ያመልኩታል፤ ፊቱን ያያሉ፤ ስሙም በግንባራቸው ላይ ይሆናል። ከእንግዲህ ወዲህ ሌሊት አይኖርም፤ ጌታ አምላክ ስለሚያበራላቸው የመብራት ወይም የፀሓይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ከዘላለም እስከ ዘላለምም ይነግሣሉ። መልአኩም፣ “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኞች ናቸው። የነቢያት መናፍስት ጌታ አምላክ በቅርብ የሚሆነውን ነገር ለባሮቹ እንዲያሳይ መልአኩን ልኳል” አለኝ። “እነሆ፤ ቶሎ እመጣለሁ፤ የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።” እነዚህን ነገሮች የሰማሁና ያየሁ እኔ ዮሐንስ ነኝ። እነዚህን ነገሮች በሰማሁና ባየሁ ጊዜ፣ እነዚህን ነገሮች ላሳየኝ መልአክ ልሰግድ በእግሩ ሥር ተደፋሁ፤ እርሱ ግን፣ “ተው፤ ይህን አታድርግ እኔ ከአንተና ከወንድሞችህ ከነቢያት እንዲሁም የዚህን መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁት ሁሉ ጋራ አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ” አለኝ። እንዲህም አለኝ፤ “ጊዜው ስለ ደረሰ፣ የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው፤ ዐመፀኛው በዐመፁ ይቀጥል፤ ርኩሱም ይርከስ፤ ጻድቁም ይጽደቅ፤ ቅዱሱም ይቀደስ።” “እነሆ፤ ቶሎ እመጣለሁ፤ ዋጋዬ በእኔ ዘንድ አለ፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍለዋለሁ። አልፋና ዖሜጋ፣ ፊተኛውና ኋለኛው፣ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። “ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስና በበሮቿም በኩል ወደ ከተማዪቱ ለመግባት መብት እንዲኖራቸው ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው። ውሾች፣ አስማተኞች፣ ሴሰኞች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ ውሸትን የሚወድዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ። “እኔ ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች እንዲመሰክር መልአኬን ለአብያተ ክርስቲያናት ልኬአለሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፣ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ።” መንፈስና ሙሽራዪቱ፣ “ና” ይላሉ፤ የሚሰማም፣ “ና” ይበል፤ የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግም ሁሉ የሕይወትን ውሃ በነጻ ይውሰድ። የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚሰማውን ሁሉ አስጠነቅቃለሁ፤ ማንም በዚህ ቃል ላይ አንዳች ቢጨምር፣ እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል፤ ማንም በዚህ የትንቢት መጽሐፍ ከተጻፈው ቃል አንዳች ቢያጐድል፣ እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ ዕድሉን ያጐድልበታል። እነዚህን ነገሮች የሚመሰክረው፣ “አዎ፣ ቶሎ እመጣለሁ” ይላል። አሜን፤ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ና። የጌታ የኢየሱስ ጸጋ ከሁሉ ጋራ ይሁን። አሜን።
ራእይ 22:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውኃ ወንዝ አሳየኝ። በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፥ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ። ከእንግዲህም ወዲህ መርገም ከቶ አይሆንም። የእግዚአብሔርና የበጉም ዙፋን በእርስዋ ውስጥ ይሆናል፥ ባሪያዎቹም ያመልኩታል፥ ፊቱንም ያያሉ፥ ስሙም በግምባሮቻቸው ይሆናል። ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይሆንም፥ ጌታ አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና የመብራት ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣሉ። እርሱም፦ እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፥ የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ። እነሆም፥ በቶሎ እመጣለሁ። የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው አለኝ። ይህንም ያየሁትና የሰማሁት እኔ ዮሐንስ ነኝ። በሰማሁትና ባየሁትም ጊዜ ይህን ባሳየኝ በመልአኩ እግር ፊት እሰግድ ዘንድ ተደፋሁ። እርሱም፦ እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ነቢያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ አለኝ። ለእኔም፦ ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው። ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ። እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱም እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው። ውሻዎችና አስማተኞች ሴሰኛዎችም ነፍሰ ገዳዮችም ጣዖትንም የሚያመልኩት ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ። እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልአኬን ላክሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፥ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ። መንፈሱና ሙሽራይቱም፦ ና ይላሉ። የሚሰማም፦ ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፥ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ። በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የትንቢት ቃል ለሚሰማ ሁሉ እኔ እመሰክራለሁ፤ ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል፤ ማንምም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ቢያጎድል፥ በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ዕድሉን ያጎድልበታል። ይህን የሚመሰክር፦ አዎን፥ በቶሎ እመጣለሁ ይላል። አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን።
ራእይ 22:1-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ መልአኩ ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብሩህ መስተዋት ጥርት ያለውን የሕይወት ውሃ ወንዝ አሳየኝ፤ ይህ ወንዝ በከተማይቱ ዋና መንገድ መካከል ሰንጥቆ ያልፋል፤ በወንዙ ግራና ቀኝ በየወሩ እያፈራ በዓመት ዐሥራ ሁለት ጊዜ ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ የዛፉም ቅጠሎች ሕዝቦችን ለመፈወስ ያገለግላሉ። ከእንግዲህም ወዲህ ምንም ዐይነት ርግማን አይኖርም፤ የእግዚአብሔርና የበጉ ዙፋን በከተማይቱ ውስጥ ይሆናል፤ አገልጋዮቹም ያመልኩታል። ፊቱን ያያሉ፤ ስሙም በየግምባራቸው ላይ ይሆናል። ከእንግዲህ ወዲህ ሌሊት አይኖርም፤ ጌታ አምላክ ስለሚያበራላቸው የመብራት ወይም የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይነግሣሉ። ከዚህ በኋላ መልአኩ እንዲህ አለኝ፦ “እነዚህ ቃላት የታመኑና እውነተኞች ናቸው፤ ነቢያትን የሚያናግር አምላክ በቅርብ ጊዜ የሚሆነውን ነገር ለአገልጋዮቹ ለመግለጥ መልአኩን ላከ።” ኢየሱስም “እነሆ! እኔ በቶሎ እመጣለሁ! የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚጠብቅ የተመሰገነ ነው!” አለ። እነዚህን ነገሮች የሰማሁና ያየሁ እኔ ዮሐንስ ነኝ፤ እነዚህን ነገሮች በሰማሁና ባየሁ ጊዜ እነዚህን ነገሮች ላሳየኝ መልአክ ልሰግድለት በእግሩ ሥር ወደቅኩ። መልአኩ ግን “ተው ይህን አታድርግ! እኔ ከአንተና ከወንድሞችህ ከነቢያት ጋር የዚህን መጽሐፍ ቃል ከሚፈጽሙ ሰዎች ጋር አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ!” አለኝ። ቀጥሎም እንዲህ አለኝ፤ “ጊዜው የቀረበ ስለ ሆነ የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው፤ ከእንግዲህ ወዲህ ዐመፀኛው ማመፁን ይቀጥል፤ ርኩሱም ይርከስ፤ ጻድቁም ይጽደቅ፤ ቅዱሱም ይቀደስ።” “እነሆ! እኔ በቶሎ እመጣለሁ! ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው የምሰጠውን ዋጋ ይዤአለሁ፤ አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።” ከሕይወት ዛፍ ፍሬ ለመብላትና በደጃፎችዋም ወደ ከተማይቱ ለመግባት መብት እንዲኖራቸው ልብሳቸውን ያጠቡ የተባረኩ ናቸው። እንደ ውሻ የሚልከፈከፉ፥ አስማተኞች፥ አመንዝሮች፥ ነፍሰ ገዳዮች፥ ጣዖት አምላኪዎች፥ ውሸትን የሚወዱና በሐሰት መንገድ የሚሄዱ ሁሉ ከከተማይቱ ውጪ ይሆናሉ። “እኔ ኢየሱስ ይህን ምስክርነት እንዲሰጣችሁ መልአኬን ለአብያተ ክርስቲያን ልኬአለሁ፤ እኔ የዳዊት የትውልድ ሐረግና ዘር ነኝ፤ የሚያበራ የንጋት ኮከብ ነኝ።” መንፈስ ቅዱስና ሙሽራይቱ “ና!” ይላሉ፤ የሚሰማም “ና!” ይበል፤ የተጠማም ይምጣ፤ የፈለገም የሕይወትን ውሃ ያለ ምንም ዋጋ በነጻ ይጠጣ። እነሆ፥ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የትንቢት ቃል የሚሰማውን ሁሉ አስጠነቅቃለሁ፤ ማንም በዚህ ቃል ላይ አንዳች ነገር ቢጨምር፥ በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች እግዚአብሔር ይጨምርበታል። ማንም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ነገር ቢያጐድል፥ በዚህ መጽሐፍ ከተነገሩት ከሕይወት ዛፍ ፍሬና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ድርሻውን ያጐድልበታል። የእነዚህ ነገሮች ምስክር የሆነው “በእርግጥ፥ በቶሎ እመጣለሁ!” ይላል። አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና! የጌታ የኢየሱስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።
ራእይ 22:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውሃ ወንዝ አሳየኝ። በከተማው አደባባይዋም መካከል፥ በወንዙም ወዲያና ወዲህ፥ በየወሩ እያፈራ ዐሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝቦች መፈወሻ ነበሩ። ከእንግዲህም ወዲህ መርገም ከቶ አይሆንም። የእግዚአብሔርና የበጉም ዙፋን በእርሷ ውስጥ ይሆናል፤ ባርያዎቹም ያመልኩታል፤ ፊቱንም ያያሉ፤ ስሙም በግምባሮቻቸው ይኖራል። ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይሆንም፤ ጌታ አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና የመብራት ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ከዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ይነግሣሉ። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፤ የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባርያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ።” እነሆም “በቶሎ እመጣለሁ። የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።” ይህንም ያየሁትና የሰማሁት እኔ ዮሐንስ ነኝ። በሰማሁትና ባየሁትም ጊዜ ይህን ባሳየኝ በመልአኩ እግር ፊት ለመስገድ ተደፋሁ። እርሱም “እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር፥ ከወንድሞችህም ነቢያት ጋር፥ የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤” አለኝ። እንዲሀም አለኝ፦ “ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው። ዐመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፤ ርኩሱም ወደ ፊት ይርከስ፤ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፤ ቅዱሱም ወደ ፊት ይቀደስ፤” አለ። “እነሆ በቶሎ እመጣለሁ፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።” ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው፥ በደጆችዋም ወደ ከተማይቱም እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው። ውሻዎችና አስማተኞች፥ ሴሰኛዎችም፥ ነፍሰ ገዳዮችም፥ ጣዖት አምላኪዎችም፥ ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ ይቀራሉ። “እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልአኬን ላክሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፤ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ።” መንፈሱና ሙሽራይቱም “ና!” ይላሉ። የሚሰማም “ና!” ይበል። የተጠማም ይምጣ፤ የወደደም የሕይወትን ውሃ በነጻ ይውሰድ። በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የትንቢት ቃል ለሚሰማ ሁሉ እኔ እመሰክራለሁ፤ ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር፥ እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል፤ ማንምም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ቢያጎድል፥ በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ድርሻውን ያጎድልበታል። ይህን የሚመሰክር “አዎን በቶሎ እመጣለሁ፤” ይላል። አሜን፤ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን።